የእስራኤል ወታደሮች የቆሰለን ፍልስጤማዊ ተሸከርካሪ ላይ አስረው መውሰዳቸው ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእስራኤል ሠራዊት አባላት በተኩስ ልውውጥ የቆሰለን ፍልስጤማዊ የመኪናቸው የፊተኛው ክፍል ላይ አስረው ይዘው መሄዳቸው ቁጣን ቀሰቀሰ።
ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ወታደሮቹ ቁስለኛውን ፍልስጤማዊ ጂፕ በተባለው ወታደራዊ ተሸከርካሪ የፊተኛ ክፍል ላይ ከመኪናው ጋር ጠፍንገው አስረው ይዘው ሲጓዙ አሳይተዋል።
ይህን ተከትሎ የእስራኤል ጦር ክስተቱን አምኖ የሠራዊት አባላቱ ወታደራዊ ስነ-ስርዓት ጥሰዋል ሲል መግለጫ አውጥቷል።
ክስተቱ ያጋጠመው ቅዳሜ ሰኔ 15/2016 ዓ.ም. የእስራኤል ወታደሮች በዌስት ባንክ ጄኒን በተባለች ከተማ ላይ ድንገተኛ ዘመቻ ካደረጉ በኋላ ነው።
የእስራኤል ጦር ቁስለኛው ፍልስጤማዊ በሠራዊት አባላቱ ላይ ተኩስ መክፈቱን እና መቁሰሉን ገልጿል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል የአካባቢው ነዋሪዎች የሆኑ የዓይን እማኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው ሙሃጂድ አዝሚ የተባለው ፍልስጤማዊ የአካባቢው ነዋሪ መሆኑን እና የቤተሰቡ አባላት ለተጎዳው ፍልስጤማዊ አምቡላንስ እንዲጠራ ቢጠይቁም የእስራኤል ወታደሮች የመኪናው የፊተኛ ክፍል ላይ አስረው ወስደውታል።
የእስራኤል ጦር ቁስለኛው ሕክምና እንዲያገኝ ለቀይ ጨረቃ ተላልፎ መሰጠቱን ገልጾ ክስተቱን በተመለከተ ምርመራ አድርጋለሁ ብሏል።
የእስራኤል ጦር “ዛሬ ጠዋት (ቅዳሜ) በጸረ-ሽብር ዘመቻ ወዲ ቡርቂን በተባለ አካባቢ አሸባሪዎች በሠራዊት አባላት ላይ ተኩስ ከፍተዋል። በተኩስ ልውውጡ አንደ ተጠርጣሪ ቆስሎ ተይዟል” ካለ በኋላ፤ “ስርዓትን ባልተከተለ መንገድ ተጠርጣሪው መኪና ላይ ታስሮ ተወስዷል” ብሏል።
ጦሩ አክሎም የሠራዊት አባላቱ ተግባር የእስራኤል ጦር እሴቶችን አይወክልም በማለት ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።
ሐማስ እስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ በተጀመረው ጦርነት ወደ 40ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን በጋዛ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በዌስት ባንክ እንዲሁ የእስራኤል ጦር ወታደራዊ ኦፕሬሽኖችን ሲያካሂድ ቆይቷል።
የተባባሩት መንግሥት የተዋጊ ኃይሎችን፣ ጥቃት አድራሾችን እና ሰላማዊ ስዎችን ጨምሮ በዌስት ባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም ቢያንስ 480 ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ይላል።












