የመከላከያ እና የፖሊስ አዛዦች ከአማራ ተወላጆች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ምን ምን ጉዳዮች ተነሱ?

የስብሰባው ተሳታፊዎች

የፎቶው ባለመብት, Defense Force/FB

የምስሉ መግለጫ, የስብሰባው ተሳታፊዎች

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አዛዦች “ከአማራ ተወላጆች” ጋር “በአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ እና የሰላምና ጉዳይ” ላይ ሐሙስ ሰኔ 13/2016 ዓ.ም. መወያየታቸው ተዘግቧል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት በጠራው በዚህ ዝግ ስብሰባ በከተማዋ የሚኖሩና የተለያዩ የማኅረሰብ ክፍሎችን የወከሉ የአማራ ተወላጆች መታደማቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ስብሰባውን ከአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተረክበው የመሩት የክልሉ ተወላጆች ናቸው የተባሉት የመከላከያ እና የፖሊስ አዛዦች ናቸው።

የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ የመከላከያ ሠራዊት የዘመቻ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል በላይ ስዩም እና የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግሥቴ ስብሰባውን ስለመምራታቸው ተገልጿል።

ጠዋት ሦስት ሰዓት አካባቢ በአዲሱ የአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ትልቁ የስብሰባ አዳራሽ የተጀመረው ስብሰባው ከ200 በላይ ይሆናሉ ተብለው የተገመቱ “ተደማጭ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ” ባለሀብቶች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች መሳተፋቸውን ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የስብሰባው ታዳሚ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጠዋት ጀምሮ እስከ ምሽት ድረስ ዘልቋል በተባለው በዚህ ስብሰባ የአማራ ክልል እና የአዲስ አበባ የሰላም ጉዳይ በዋናነት መነሳቱን ተሳታፊው ገልጸዋል።

“አማራ በማንነቱ ይታሰራል፣ ይዋከባል፣ ያለ ሕግ [ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ] ቤቱ ይፈተሻል፣ ተጠልፎ ይሰወራል፣ ከመሰወር በኋላ ለማስለቀቅ የገንዘብ ድርድር ይቀርብበታለ. . . የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች ተነስተዋል።”

እነዚህ ጉዳዮችም በዋናነት በአዲስ አበባ ከተማ እና በፌደራል ፖሊስ ላይ ያተኮሩ የነበረ ሲሆን፣ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴም የስብሰባው አንደኛው መሪ ስለነበሩ “እነዚህን ነገሮች ታውቃላችሁ ወይ?” ተነስቶላቸው እንደነበር ማንነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ሌላ ተሳታፊ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአማራ ክልል ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ስለሚዋጋው የፋኖ ታጣቂ እሴት እና መሠረትም ጥያቄዎች እንደቀረቡ ያነሱት የስብሰባው ታዳሚ፤ “የነበሩ ጥያቄዎች ባለመመለሳቸው እና ሕዝቡ የህልውና አደጋ ስለተጋረጠበት እሱን ለመመከት ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው። ስለዚህ በዚህ ልክ ልትረዱት ይገባል” የሚል ሀሳብ ከታዳሚው መነሳቱንም ጠቅሰዋል።

በመንግሥት ኃይሎች ተፈጸሙ የተባሉ የንጹሃን ግድያዎች ጉዳይም በስብሰባው ላይ መነሳቱ የተናገሩት ታዳሚው፤ ለአብነት ባለፈው ሳምንት እሁድ በምዕራብ ጎጃም ዞን ጂጋ ከተማ የተፈጸመው ግድያ ከታዳሚዎች መካከል ተጠቅሶ ጥያቄ እንደነበረ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በክልሉ የተሰማራው ሠራዊት ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር በሚያካሂደው ግጭት ወቅት “ስትጠቁ ሕዝብ በበቀል እንደሚጎዳ እንሰማለን፤ እናያለን፤ ማስረጃዎችም አሉን። ይህንን ትከታተሉታላችሁ ወይ?” በማለት አንድ ተሳታፊ ለጦር ኃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹሙ ጥያቄ አንስተዋል ብለዋል ታዳሚው።

የመከላከያ አዛዦች “‘ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኳችንን በሕግ ነው እያስፈጸምን ያለነው። እዚህ አገር ሥልጣን የሚያዘው በምርጫ ነው። ስለዚህ የተመረጠ መንግሥት አለ። ያን የተመረጠ መንግሥት ለማገልገል እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን [ለማስከበር] የውስጥም የውጭም ጠላት ሲመጣ ሕግ ማስከበር ነው ኃላፊነታችን፤ እሱን ነው እየሠራን ያለነው” የሚል ጥቅል ምላሽ ለተነሱ ጥያቄዎች እንደሰጡም ተናግረዋል።

ስለ ፋኖ በተሰጠ ምላሽ ‘[ፋኖ] ዘራፊ ነው፤ ጨፍጫፊ ነው፤ የራሱን ሕዝብ ነው የሚገድለው፤ የራሱን የልማት አውታር ነው የሚያወድመው። ስለዚህ እናንተ የምትሉትን [ፋኖ] አይደለም እኛ የምናውቀው’ ማለታቸውን የስብሰባው ተሳታፊ የቢቢሲ ምንጭ ገልጸዋል።

“‘በጉልበት ሥልጣን ስለማይያዝ፤ በፉከራ አራት ኪሎ ግባ ስለተባለ ስለማይገባ፤ እኛም እያለን ስለማንፈቅድ [ታጣቂዎችን] ተዉ በሏቸው፤ ለሰላም እጃቸውን ይዘርጉ’” የሚል መልዕክት ለፋኖ እንዲያስተላልፉ በስብሰባው መሪዎች እንደተነገራቸው ተሳታፊው ጠቅሰዋል።

አንድ ዓመት ሊሞላው በተቃረበው የአማራ ክልል ቀውስ በተለያዩ ጊዜያት በነበሩ ግጭቶች ሰበብ ጥቂት የማይባሉ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የመገናኛ ብዙኃን እና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ሪፖርት ቢያደርጉም የስብሰባው መሪዎች ግን የተለየ ሃሳብ መሰንዘራቸውን የስብሰባው ታዳሚ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በክልሉ ውስጥ ስላጋጠሙት የንጹሃን ነዋሪዎች ግድያን በሚመለከት ግድያዎቹን ‘ተጋነዋል’ የሚል ድፍን ያለ ምላሽ በመስጠት ነው ለማስተባበል የሞከሩት።

“እንደሚባለው አይደለም፤ ዝም ብሎ ይጋነናል። የዩቲዩበር ወሬ ነው፤ የማኅበራዊ ሚዲያ ወሬ ነው፤ ተልዕኳችን እሱን አይፈቅድም፤ ስምሪታችንም አይፈቅድም፤ ሥልጠናችንም ይሄ አይደለም፤ ለሕዝብ መስዋዕት ሆኖ መቆም ነው። የሚል የተለመደ መልስ ነው የተሰጠው” ሲሉ ተሳታፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የስብሰባውን ይዘት እና ግብ የገመገሙት ከምሁራን የሕብረተሰብ ክፍል የተወከሉት የስብሰባው ተካፋይ፤ “ስብሰባው የሚፈለገውን ግብ የመታ አይመስለኝም” ብለዋል።

“[የስብሰባው መግቢያ ላይ] ‘እንደ አገር፤ እንደ ሕዝብ ስለታመምን ለዚህ ፈውስ የሚሆን ሀሳብ እናዋጣ፤ ለሰላም በራችንን እንከፍት እና ካለገደብ ሀሳባችሁን አውጡ፤ እንወያይ፤ እንምከር፤ ከሰማይ በታች ከምድር በላይ ያለውን ሁሉ አንሱ እንወያይ ነበር።’ ነገር ግን መጨረሻ ላይ ከሁለቱም ጄኔራሎች የተሰጠው መልስ ከዚያ [በስብሰባው መግቢያ ካሉት] እውነት ያፈነገጠ ነበር” ሲሉ ሰብሳቢዎቹ የራሳቸውን አቋም እና ሀሳብ ብቻ ለማስረጽ መሞከራቸውን ተናግረዋል።

“የሁሉም ችግር መነሻ መድረሻው ራሳችን ነን፤ ራሱ ሕዝቡ ነው፤ ከፍ ሲልም የአማራ ሊሂቅ ነው። ማንም አልደረሰበትም። ስለዚህ ራሳችን ሰላም አጥተን፣ አገር ሰላም እያሳጣን ነው” የሚል ክስ ከሰብሳቢዎቹ አንዱ ማቅረባቸውን በመተቸት ተሳታፊው ለቢቢሲ የታዘቡትን ገልጸዋል።

የስብሰባው ታዳሚዎች ስልክ ይዘው እንዳይገቡ በተደረገበት በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ጋዜጠኞች ስለመገኘታቸው እግርጠኛ ያልሆኑት ቢቢሲ ያናገራቸው ታዳሚዎች ስለ ውይይቱ በመንግሥት መገናኛ ላይ በዝርዝር አለመዘገቡን ተናግረዋል።

በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ በውይይቱ ላይ የተነሱ ጥያቄዎች ለክልል እና ለፌደራል መንግሥት እንደሚቀርቡ እንዲሁም ከታዳሚዎቹ መካከል በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር ይካሄዳል ለተባለ “የሰላም ጉባኤ” ወኪሎች እንደተመረጡም ምንጩ ጠቁመዋል።

አንድ ዓመት ሊሞላው በተቃረበው የአማራ ክልል አለመረጋጋት በሰላም መፍትሄ እንዲያገኝ የፌደራሉ መንግሥትም ሆነ የክልሉ አስተዳደር ፍላጎት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ቢገልጹም፣ እስካሁን በይፋ የሚታወቅ እንቅስቃሴ የለም።