በናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሐሰተኛ ፊርማ 6 ሚሊዮን ዶላር እንዳጭበረበሩ የተጠረጠሩ ሰዎች እየታደኑ ነው

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES
የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ቡሃሪ ፊርማን በማስመሰል 6.2 ሚሊዮን ዶላር ከብሄራዊ ባንክ እንዳጭበረበሩ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለመያዝ ናይጄሪያ የዓለም አቀፉን ፖሊስ ተቋም ወይም ኢንተር ፖልን እገዛ እየጠየቀች ነው።
ተጠርጣሪዎቹ ይህንን ወንጀል የፈጸሙት ከቀድሞው የሀገሪቱ ብሄራዊ ባንክ ገዢ ጎድዊን ኤምፊሌ ጋር በመመሳጠር ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል።
የቀድሞው ገዢ የ6.2 ሚሊዮን ዶላሩን ጉዳይ ጨምሮ 20 ክሶች ተመስርቶባቸው ታስረው ነበር።
ባለፈው ሰኔ አዲሱ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኒቡ ስልጣን ከያዙ ወዲህ ከፍ ያለ ስም ያለው ሰው በሙስና ተጠርጥሮ ሲያዝ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የናይጄሪያ መንግስት ጠቅላይ አቃቤ ህጎች የቀድሞው የማዕከላዊ ባንክ ገዢ ከህግ በተጻረረ መልኩ ከሚመሩት ባንክ ቋት ገንዘብ እንዲወጣ ፈቅደዋል ሲሉ ከሰዋል።
ሰውዬው ባለፈው ታህሳስ ወር የቀረበባቸውን ክስ አስመልክቶ ባወጡት መግለጫ “ሰይጣናዊ አጀንዳቸውን ለማሳካት በኔ ላይ ያለምንም እፍረት ያቀረቡት ክስ ነው” ያሉ ሲሆን ግልጽነት የተሞላበት ምርመራ እንዲኖርም ጠይቀዋል።
የማዕከላዊ ባንኩ ሰራተኞች የነበሩት አዳሙ አቡበከር፣ ኢማን አቡበከር እና ኦዶ ኦችሜ የባንኩ ገዢ የነበሩት ኤምፊሌ የወንጀል ተባባሪ በመሆን እንደተጠረጠሩ የናይጄሪያ መንግስት በባለቤትነት የያዘው የዜና ወኪል ዘግቧል።
ተጠርጣሪዎቹ ናይጄሪያን ጥለው እንደኮበለሉ የሚገመት ሲሆን እነሱን አድኖ ለመያዝ እና ለፍርድ ለማቅረብ የሀገሪቱ ባለስልጣናት የኢንተርፖል እርዳታ እንደሚፈልጉ ተገልጿል።
ሶስቱም ተጠርጣሪዎች ስለቀረበባቸው ክስ በይፋ ያሉት ነገር የለም።
የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ቡሃሪ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩት ቦስ ሙስጠፋ፣ የቀድሞው የማዕከላዊ ባንክ ገዢው ችሎት ላይ ባለፈው ማክሰኞ ተገኝተው ምስክርነታቸን ከሰጡ በኋላ ሶስቱ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መንግሥት አዝዟል።
ሙስጠፋ፣ እሳቸውም ይሁኑ አለቃቸው ሞሃመድ ቦሃሪ 6.2 ሚሊዮን ዶላሩን እንዲያወጡ በፊርማቸው አለማጽደቃቸውን ለችሎቱ አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
ጨምረውም “ፊርማውን ስመለከተው፣ ያለበቂ ዝግጅት [የቀድሞው] የፕሬዝዳንት ቡሃሪን ፊርማ ለማመሳሰል የተደረገ ነው” ስለማለታቸው የሀገሪቱ ብሄራዊ ጋዜጣ ዘግቧል።
ገንዘቡ እንዲወጣ ጸድቋል የተባለበትን ሰነድ እንዲመለከቱ የተደረጉት ሙስጠፋ “ከፕሬዝዳንቱ ቢሮ የወጣ አይደለም” ብለዋል።
6̀.2 ሚሊዮን ዶላሩ፣ ባለፈው ዓመት ጥር ወር የቦሃሪ የስልጣን ዘመን ከማብቃቱ ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ በጥሬ ገንዘብ መልክ እንደወጣ ተመላክቷል።
የቀድሞ የባንክ ገዢ ገንዘቡ ምርጫውን ለሚታዘቡ የውጪ ሀገር ዜጎች ወጪ እንዲሆን ፕሬዝዳንቱ እንዳዘዙ ተደርጎ እንደወጣ አቃቤ ህጎች ገልጸዋል።
የቀድሞው የናይጄሪያ ብሄራዊ ባንክ ገዢ ጎድዊን ኤምፊሌ እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ስሌት በ2014 በያኔው ፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታን ነበር የተሾሙት።
ቀጥሎም በቦሃሪ ዘመን በዚያው ስልጣን እንዲቆዩ በ2019 ዳግም የተሾሙ ሲሆን አዲሱ ፕሬዝዳንት ወደ ስልጣን እስከመጡ ኃላፊነት ላይ ነበሩ።












