በአሜሪካ የኢምግሬሽን መኮንኖች አንዲትን ሴት ተኩሰው መግደላቸው ቁጣ ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የኢምግሬሽን መኮንን ረቡዕ በሚኒያፖሊስ ከተማ አንዲትን የ37 ዓመት ሴት በጥይት ተኩሶ መግደሉ ተሰማ።
ከግድያው ይልቅ ለግድያው ያደረሰው ሁኔታ ዝርዝር የፌደራል እና የአካባቢውን አስተዳደር ባለሥልጣናት እያከራከረ ነው።
የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ሪኔ ኒኮል ጉድ የተባለችው ሟች የኢሚግሬሽን እና የጉሙሩክ መኮንኖችን በተሽከርካሪዋ ለመግጨት የሞከረች "ጠብ ጫሪ አመፀኛ" እንደነበረች እና መኮንኑ "ራሱን ለመከላከል" ጥይት እንደተኮሰ ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ የከተማዋ እና የግዛቲቱ መሪዎች እንዲሁም የዲሞክራት ፓርቲ ወኪሎች ይህ መረጃ ከእውነት የራቀ ነው እያሉ ናቸው።
የሚኒያፖሊስ ከተማ ከንቲባ ጄኮብ ፍራይ "ሰው እንዲሞት ያደረገው ኃይሉን በግዴለሽነት የተወጣ መኮንን ነው" ሲሉ ክስተቱን የገለፁት ሲሆን፤ የኢምግሬሽን እና ጉሙሩክ አስከባሪዎች ከከተማዋ እንዲወጡም ጠይቀዋል።
በአካባቢው በነበሩ የዓይን እማኞች የተቀረፁ በርካታ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ጥይቱ የተተኮሰበትን ቅፅበት ያሳያሉ።
በአካባቢው የእግረኛ መንገድ ላይ ተቃዋሚዎች የሚታዩ ሲሆን፤ የኢምግሬሽን መኮንኖች ከተሽከርካሪዎቻቸው በመውጣት መኪናዋ ውስጥ ተቀምጣ የነበረችውን ሴት እንድትወጣ ሲጠይቋት እና በኃይል በሩን ለመክፈት ሲሞክሩ ይታያሉ።
አሽከርካሪዋ ለመንዳት ሙከራ ስታደርግ ጥይት ተተኩሶባታል።
ሦስት የተኩስ ድምፅ የሚሰማ ሲሆን፤ ተሽከርካሪው ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ በአቅራቢያው ቆሞ ከነበረ ከሌላ ተሽከርካሪ ጋር ተጋጭቷል።
ድርጊቱ የተከሰተው የትራምፕ አስተዳደር በሚኒያፖሊስ ከተማ ትልቅ ዘመቻ እያደረገ ባለበት ጊዜ ነው።
የአሜሪካ አገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር ክርስቲ ኖም የሟቿ ሴት እንቅስቃሴ እንደ "የአገር ውስጥ ሽብር" እንደሚታይ ገልፀው፤ የኢምግሬሽን ተቋሙ ተልዕኮ በከተማው እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትሩዝ ማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው አንድ የኢምግሬሽን እና ጉሙሩክ መኮንን "በጭካኔ" ተገጭቷል ብለዋል።
"በሕይወት መትረፉ ለማመን ያዳግታል። አሁን በሆስፒታል ክትትል እየተደረገለት ነው" ሲሉ አክለዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም "አክራሪ ግራ ዘመሞች" በየቀኑ "በሕግ አስከባሪዎቻችን እና በኢምግሬሽን እና ጉሙሩክ መኮንኖቻችንን በማነጣጠር፣ ዛቻ በማድረስ እና በማጥቃት" ወቅሰዋል።
የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር ክርስቲ ኖም ያለፈውን የሰው ሕይወት "መከላከል" ይቻል እንደነበር ለጋዜጠⶉች የተናገሩ ሲሆን፤ የኢምግሬሽን መኮንኑ ራሱን ለመከላከል ጥይቱን እንደተኮሰ እና ሟቿ ተሽከርካሪዋን "አደገኛ መሣሪያ" አድርጋ መጠቀሟን ተናግረዋል።
የአሜሪካ ፌደራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) በዝርዝሩ ዙሪያ ምርመራ እያደረገ ነው ብለዋል።
የትራምፕ አስተዳደር የማጭበርበር ክሶች መቅረባቸውን ተከትሎ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በሚኒያፕለስ ከተማ ሁለት ሺህ ተጨማሪ የፌደራል መኮንኖችን ማሰማራቱን ምንጮች የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ተናግረዋል።
እሁድ እለት የጀመረው የተጨማሪ የመኮንኖች መሰማራት በቅርብ ዓመታት ውስጥ በአንድ ከተማ ይህን ያህል የአገር ውስጥ ደኅንነት ሠራተኞች በመሰባሰብ ግዙፉ ነው ተብሏል።















