የትራምፕ አስተዳደር በመቶዎች የሚቆጠሩ የበረራ ደኅንነት ሠራተኞችን አባረረ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የትራምፕ አስተዳደር በመቶዎች የሚቆጠሩ የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር ሠራተኞች ማባረር መጀመሩን የሠራተኞች ማኅበር አስታወቀ።

ይህ የትራምፕ አስተዳደር እርምጃ ከመሰማቱ ሳምንታት ቀደም ብሎ በዋሽንግተን ዲሲ አየር ላይ አውሮፕላኖች ተጋጭተው በርካቶች መሞታቸው ይታወሳል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ እና በኤጀንሲው ከአንድ ዓመት በታች የሠሩ ሠራተኞች ውሳኔውን በኢሜል እንዲያውቁት መደረጉን ማኅበሩ አስታውቋል።

ይህ ሠራተኞችን የማባረር ውሳኔ በኢላን መስክ የሚመራው እና የአሜሪካ መንግስት ፌዴራል ተቋማትን ውጤታማ ለማድረግ በማለም የተቋቋመው መስሪያ ቤት የጀመረው የወጪ ቅንሳ ዕቅድ አካል ነው።

ዶጅ የተባለው የኢላን መስክ መሥሪያ ቤት በርካታ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች እንዲቀነሱ እና የመንግሥት ኤጀንሲ መሥሪያ ቤቶች እንዲዘጉ ምክንያት እየሆነ ነው።

የአቪዬሽን ሠራተኞች ማኅበር ሊቀ መንበር አሌክስ ስፔሮ ውሳኔውን የኮነኑ ሲሆን አሳፋሪ ሲሉ ጠርተውታል።

"ቀድሞም ቢሆን ሥራ ይበዛበት የነበረው የሰው ኃይል ላይ አዲስ ኃላፊነት በመጫን ጫናው እንዲበረታበት ያደርጋል" ሲሉም አክለዋል።

ሊቀመንበሩ በለቀቁት መግለጫ የሲስተም፣ የደኅንነት ቅኝት፣ የጥገና እና የአስተዳደር ባለሙያዎችን ጨምሮ በርካታ ባለሙያዎች መባረራቸውን ገልፀዋል።

"ተቋሙ ቀደም ብሎም በሠራተኞች እጥረት" እየተቸገረ እንደነበር ያነሱት ስፔሮ ባለፈው ወር 67 ሰዎች የሞቱበትን የዲሲው አደጋ ጨምሮ ለሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ሶስት አደጋዎች ከተከሰቱ በኋላ መሆኑ ውሳኔው ትክክል እንዳልሆነ ያሳያል ብለዋል።

አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በትራምፕ ውሳኔ ከሥራ ከተቀነሱት መካል አንዱ የሆነው ጄሰን ኪንግ የኤቬሽን ደኅንነት የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል በሚል ሥጋት እንደጫረበተት ገልጿል።

በአየር ትራንስፖረት ደኅንነት ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸውን ሠራተኞች ማባረር "በብሔራዊ የአየር ክልላችን ላይ ለሕዝብ ደኅንነት ሥጋት የሚፈጥር ነው" ሲል ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።

ኪንግ ጨምሮም ይህ ውሳኔ ለሕዝብ ደኅንነት ሥጋት እንደሆነ እና አደጋዎች እንዲበራከቱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ከገለጸ በኋላ "የአቪየሽን ደኅንነት ከበጀት ቅነሳ ጋር ተያይዞ ሊታይ አይገባውም" ሲል አክሏል።

የትራምፕ አስተዳደር የመንግስት ተቋማት በቅርቡ ተቀጥረው በሙከራ ላይ ያሉ እና እስካሁን ቅጥር ያላገኙ ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ያሉ ሠራተኞች እንዲባረሩ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ይህ ውሳኔ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሠዎች ላይ ተጽህኖ ሊፈጥር እንደሚችል ይታመናል።