በካናዳ አየር ማረፊያ አውሮፕላን ተገልብጦ ሶስት ሰዎች ቢጎዱም የሞት አደጋ እንዳልተከሰተ ተዘገበ

በቶሮንቶ የተገለበጠው አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, John Nelson

በካናዳው ቶሮንቶ ፒርሰን አየር ማረፊያ አንድ አውሮፕላን በማረፍ ላይ ሳለ ባጋጠመው አደጋ ጥቂት መንገደኞች ላይ ጉዳት ቢደርስም አብዛኛዎቹ ተሳፋሪዎች መትረፋቸውን የአየር ማረፊያው ኃላፊ አስታወቁ።

"ምንም ዓይነት የሞት አደጋ ባለመኖሩ በጣም ደስተኞች ነን። ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው ጉዳት የደረሰባቸው" ሲሉ የግሬት ቶሮንቶ አየር ማረፊያ ባለሥጣን ኃላፊ ዴቦራህ ፍሊንት ተናግረዋል።

አንድ ሕፃን እና ሁለት አዋቂዎች ክፉኛ መጎዳታቸው የተነገረ ሲሆን ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተለጠፉ ምስሎች አውሮፕላን ተገልብጦ አሳይተዋል።

በተጨማሪ በተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ ተሳፋሪዎች ከተገለበጠው አውሮፕላን ውስጥ እየተሯሯጡ ሲወጡ እና የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አውሮፕላኑን በፎም ሲሸፍኑት ይታያሉ።

የአየር ማረፊያ መንደርደሪያ አስፋልት በበረዶ ብናኝ የተዋጠ ሲሆን የአውሮፕላኑ ሁለት ክንፎች በምስሎቹ ላይ አይታዩም።

ቶሮንቶ ፒርሰን አየር ማረፊያ በለቀቀው መግለጫ አደጋ ያጋጠመው አውሮፕላን ከሚኒያፖሊስ የተነሳ የዴልታ አየር መንገድ ንብረት የሆነ አውሮፕላን መሆኑን አሳውቋል።

አውሮፕላኑ 4 የበረራ ሠራተኞች እና 76 መንገደኞችን አሳፍሮ ነው የተነሳው።

በጠቅላላው 18 መንገደኞች ለሕክምና እርዳታ ወደ ሆስፒታል አቅንተዋል።

ክፉኛ አደጋ የገጠማቸው አንድ ሕፃን እና በ60ዎቹ ዕድሜ የሚገኙ አዛውንት እንዲሁም በ40ዎቹ ዕድሜ የምትገኝ መንገደኛ መሆናቸው ተዘግቧል።

የቶሮንቶ ፒርሰን አየር መንገድ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዴቦራህ ፍሊንት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን አመስግነው የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ትልቅ አስተዋፅዖ አድርገዋል ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ አቪየሽን ባለሥልጣን የአሜሪካው ዴልታ አየር መንገድ ንብረት የሆነው የበረራ ቁጥር 4819 አውሮፕላን አደጋ እንዳጋጠመው አሳውቋል።

ዴልታ አየር መንገድ ሲአርጄ900 የተባለው አውሮፕላን በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት 8፡15 አደጋ እንደደረሰበት ገልጿል።

22 ተሳፋሪዎች ካናዳዊያን ሲሆኑ የተቀሩት ከተለያዩ ሀገራት የመጡ መንገደኞች መሆናቸው ዴቦራህ ተናግረዋል።

በአደጋው ምክንያት አየር ማረፊያ ለጥቂት ሰዓታት ያክል ተዘግቶ ከቆየ በኋላ ከሰዓት 11፡00 ሥራ መጀመሩን ሥራ አስኪያጇ አስታውቀዋል።

የአየር ማረፊያው ባለሥልጣናት እንዲሁም የካናዳ የትራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ የአደጋውን መንስዔ ለማጣራት ምርመራ መጀመራቸው ተሰምቷል።

በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ እንደዘገበው አውሮፕላኑ በተገለበጠ ወቅት በአየር ማረፊያው አነስተኛ የሚባል የበረዶ ብናኝ እየወረደ ነበር።

በሰሜን አሜሪካ ባለፈው አንድ ወር ብቻ አራት ትላልቅ የሚባሉ የአውሮፕላን አደጋዎች ተከስተዋል።

በአሜሪካዋ ዋሺንግተን ዲሲ አንድ የመንገደኞች አውሮፕላን ከጦር ሄሊኮፕተር ጋር ተጋጭቶ 67 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።