ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጋና አንድ ሩሲያዊ ከሴቶች ጋር የነበረውን ወሲባዊ ግንኙነት በድብቅ በመቅረፅ ተወነጀለ
ጋና ወሲባዊ ግንኙነቱን በድብቅ በመቅረፅ እና ምስሉን ያለ ሴቶቹ ፈቃድ በድረ ገፅ አጋርቷል የተባለው ሩሲያዊ ተላልፎ እንዲሰጣት ልትጠይቅ ነው።
የአፍሪካ እና የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን የግለሰቡን ማንነት የለዩ ሲሆን የድረ ገፅ ጦማሪ የሆነው በ30ዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ግለሰብ ወደ ጋና ተጉዞ ከሴቶች ጋር የነበረውን ግንኙነት በድብቅ መቅረፁን ዘግበዋል።
የጋና እና ሩሲያ መገናኛዎች ግለሰቡ ካሜራ የተገጠመለትን መነፅር በመጠቀም ከሴቶች ጋር የነበረውን ግንኙነት መቅረፁን እና በማኅበራዊ የትስስር ገፆች ማሰራጨቱን የዘገቡ ሲሆን፤ ባለሥልጣናት ግን ይህን አላረጋገጡም።
የጋና የቴክኖሎጂ ሚኒስትር ቅዳሜ ዕለት ለጋዜጠኞች ክስተቱን በሚመለከት የሩሲያን አምባሳደር ጋብዘው እንደሚያነጋግሩ ገልፀዋል።
ከዚህ አስቀድሞ የጋና የስርዓተ ፆታ፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጥበቃ ሚኒስቴር የቅድመ ምርመራ ውጤቱ ተጠርጣሪው አገሪቱን ለቅቆ መውጣቱ እንዳመላከተ ተናግሯል።
"ተፈፅሟል በተባለው ድርጊት ክብደትም ሆነ ተጠያቂነትን ለማስፈን አገሪቱ ኃላፊነቷን አልዘነጋችም" ሲልም አክሏል።
የቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ሳም ጆርጅ ለተጎጂዎች ፍትህ ለመስጠት የሞስኮን ትብብር ለመጠየቅ የሩሲያን አምበሳደር በዋና ከተማዋ አክራ እንደጠሩ አስታውቀዋል።
ይሁን እንጂ ሩሲያ ከባድ ሁኔታዎች ውጪ ዜጎቿን ለሌላ አገር አሳልፋ አትሰጥም።
ሚኒስትሩ ለቢቢሲ "የሩሲያው ዜጋ ድርጊት የሳይበር ሕጋችንን የጣሰ ነው። ይፋዊ አቋማችንን ለአምበሳደሩ በይፋ አሳውቃቸዋለሁ" ብለዋል።
ሚኒስትሩ ቀደም ብለው ለጋዜጠኞች ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል ከኢንተርፖል ጋር በመሆን ሁሉንም አቅማችንን እንጠቀማለን ብለዋል።
"የሩሲያን ባለሥልጣናት እንጠይቃለን፤ ለዚህም ነው ከአገራችን ሕግ አስከባሪዎች ጋር ለመስራት የሩሲያውን አምባሳደር የጋበዝኳቸው።
"ግለሰቡ ወደ ጋና እንዲመለስ፤ ሕጋችንን እንዲጋፈጥ ለጋና ተላልፎ እንዲሰጥ እንፈልጋለን" ብለዋል።
የቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ግለሰቡን ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ካልተሳካ በሌለበት የፍርድ ሂደቱ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
የጋና የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኸን ይህ ግለሰብ በተመሳሳይ ሕገ ወጥ ድርጊት ኬንያ ውስጥ ተሳትፎ እንደነበር ዘገበዋል።
በጋና የሳይበር ደኅንነት ሕግ ያለ ፈቃድ የሕፃናት እና የአዋቂዎችን የእርቃን ምስሎች የሚያትሙ ሰዎች እስከ 25 ዓመት እስር ይጠብቃቸዋል።
የጋና ባለሥልጣናት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወሲባዊ እና የፍቅር ማጭበርበሮችን ጨምሮ በኢንተርኔት የሚፈፀሙ ጥሰቶች ላይ ትኩረታቸው ጨምሯል።
በቅርብ ዓመታት ውስጥ በእነዚህ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ሰዎች የእስር ቁጥር ጨምሯል።
እ.አ.አ በ2022 የስልክ ጠጋኝ የሆነው ሰሎሞን ዶጋ የእርቃን ምስል በማጋራት የ14 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።