አሜሪካ እና ጀርመን ዩክሬንን ዘመናዊ ታንኮች ሊያስታጥቁ ነው፣ ሩሲያ ፀብ ጫሪነት ነው አለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ እና ጀርመን ወደ ዩክሬን ለመላክ አሻፈረኝ ሲሉት የነበረውን እና በጦር ሜዳዎች የሚኖርን ውጤት ይቀይራሉ የተባሉ ዘመናዊ ታናኮችን ኪዬቭን ለማስታጠቅ እንደተዘጋጁ ተሰምቷል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ቢያንስ 30 ‘ኤም1 ኤብራምስ’ የተባሉትን ታንኮችን ለዩክሬን መላክን በተመለከተ እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል።
የጀርመኑ መርሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ‘ሊዎፓርድ 2’ የተሰኘውን ታንክ ቢያንስ 14 ለዩክሬን ለመስጥ ውሳኔ አሳልፈዋል ተብሏል።
የዚህን ዜና መሰማት ተከትሎ በአሜሪካ የሩሲያ አምባሳደር በሰጡት አስተያት “ሌላ ጸብ አጫሪ” ውሳኔ ብለውታል።
የዩክሬን ባለሥልጣናት ደግሞ ይህንን አይነት መሳሪያ ማግኘታችን በሩሲያ የተወሰዱብንን ግዛቶች መልሶ ለመቆጣጠር ሊረዳን ይችላል ብለዋል።
እስካሁን ድረስ አሜሪካ እና ጀርመን በውጫዊ እና ውስጣዊ ጫናዎች ምክንያት ታንኮችን ወደ ዩክሬን ለመላክ አሻፈረኝ ብለዋል።
አሜሪካ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የታገዙት ‘ኤብራምስ’ ታንኮች እጅግ ከፍ ያለ ሥልጠና እና የጥገና አቅም የሚፈልጉ ናቸው በማለት ለኪዬቭ ለመስጠት እያመነታች ነው።
ጀርመን በበኩሏ ታንኮችን ለዩክሬን ከሰጠች ኔቶ ከሩሲያ ጋር በቀጥታ ጦርነት ውስጥ እንደገባ ይቆጠራል የሚል ምክንያት በማቅረብ ነው ለውሳኔው የዘገየችው።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን በስም ያልጠቀሱትን ምንጭ በመጥቀስ ‘ኤብራምስ’ ታንኮች ወደ ዩክሬን መላክን በመለከተ ዛሬ መግለጫ ሊሰጥ እንደሚችል ዘግበዋል።
መገናኛ ብዙኃኑ ነገሩን ያሏቸው ምንጮች ቢያንስ 30 ታንኮች ወደ ዩክሬን እንደሚመላኩ ገልጸዋል።
ሆኖም ታንኮቹ ዩክሬን የሚደርሱበት ጊዜ ገልጽ አይደለም። ምናልባት የጦርነት አውድማዎች ላይ እስኪደርሱ ወራትን ካልሆንም ዓመታትን ሊፈጅ ይችላል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ ጀርመን ‘ሊዎፓርድ 2’ የተሰኘውን ታንክ ወደ ዩክሬን ለመላክ የተስማማችው አሜሪካ ‘ኤም1 ኤብራምስ’ የተባለውን ታንክ ስትልክ ብቻ ነው።
የባይደን አጋር የሆኑት ዲሞክራት የአሜሪካ ምክር ቤት አባል ለመገናኛ ብዘኃን ሲናገሩ “ጀርመን ሊዎፓርድ የምልከው አሜሪካ ኤብራምስ የተሰኘውን ታንክ ስትልክ ነው የሚል ቅድመ ሁኔታ ካስቀመጠች ኤብራምስን መላክ አለብን” ብለዋል።
ብሪታኒያ በበኩሏ ‘ቻሌንጀር 2’ የተሰኘውን ታንክ ለዩክሬ እንደምትልክ ቀደም ብላ አስታውቃለች።
በዚህ ሳምንት ፖላንድ ከጀርመን ይሁንታ ከሰጠች ጀርመን ሰራሽ የሆኑትን ሊዎፓርድ 2 ታንኮችን ወደ ዩክሬን የመላክ ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች።

በዓለም አቀፉ ስታራቴጂክ ጥናት ተቋም መሠረት ቢያንስ 16 የአውሮፓ እና የኔቶ አገራት ሊዎፓርድ 2 የታባሉት ታንኮች አሏቸው።
ሁሉም ለዩክሬን ይላካሉ ማለት ባይሆነም የጀርመኑ መራሄ መንግሥት ውሳኔ ታንኩን ወደ ዩክሬን መላክ የፈለጉ አገራት መላክ የችላሉ ማለት ሊሆን ይችላል።
ሊዎፓርድ ታንኮችን ወደ ኪዮቭ መላክን በተመለከተ እስካሁን ከጀርመን መንግሥት በይፋ የተባለ ነገር የለም። ዛሬ መራሄ መንግሥት ሾልዝ ፓርላማ ተገኝተው ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ሆኖም በፓርላማ ውስጥ የመከላከያ ጉዳዮችን የሚመለከተው ኮሚቴ ሊቀ መንበር የሆኑት የኤዲኤፍ ፓርቲ አባል ማሬይ አግነስ ስታርክ የታንኮቹን መላክ በተመለከተ የተሰማውን ሪፖርት አድንቀዋል።
“ውሳኔው ከባድ ነው። ረጅም ጊዜን ወስዷል። ሆኖም በመጨረሻ ግን መቅረት የማይችል ሆኗል” ያሉት ሊቀመንበሯ ይህ ውሳኔ “ለተጎዱት እና ለጀግኖቹ” የዩክሬን ሕዝቦች እፎይታ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
የጀርመን መንግሥት ታናኮቹን ለመላክ ፍቃደኛ ባለመሆኑ አጋር አገራት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቅሬታ ገብቷቸው ነበር።
የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ቦሪስ ፒስቶሪያስ ቀደም ብለው አገራቸው ዩክሬናውያን ‘ሊዎፓርድ 2’ን ለመጠቅም የሚያስችለውን ሥልጠና ሌሎች አገራት እንዲሰጡ ትፈቅዳለች፣ ሆኖም የራሷን ባለሙያዎች ለመላክ ቃል አትገባም ብለዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አንድሪ ዬርማርክ ማክሰኞ በሰጡት አስተያየት የሩሲያን “ክንድ ለመስበር” ምዕራባውያን አገራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ታንኮችን ሊሰጡን ይገባል ብለዋል።
ጀርመን አዲስ ውሳኔ ልታሳልፍ መሆኑ ከተሰማ በኋላ ኃላፊው በቴሌግራም ገጻቸው በሳፈሩት አስተያየት “ታንኮች ዩክሬን ወደ ቀድሟ ድንበሯ እንድትመለስ ከሚያግዙ መሳሪያዎች አንዱ ነው” ብለዋል።
በሌላ በኩል በዋሽንግተን የሩሲያ አምባሳደር በቴሌግራም አማካኝነት ባስተላለፉት መልዕክት “አሜሪካ ታንክ ለማቅረብ ከወሰነች እንዲህ አይነት ተግባር ለመፈጸም ‘ራሳን የመከላከያ መሳሪያ ነው የማቀርበው’ የሚለው ምክንያት ዋጋ ያጣል” ያሉ ሲሆን “ይህ በሩሲያ ፌዴሬሽን ላይ የሚደረግ ግለጽ ጸብ አጫሪነት ነው” ሲሉ አክለዋል።












