እስራኤል እየፈጸመችው ባለው ጥቃት በጋዛ የታገቱባት ሰባት ሰዎች መገደላቸውን ሐማስ አስታወቀ

እስራኤል እየፈጸመችው ባለው ጥቃት በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ታግተው ያሉ ሰባት ታጋቾቿ መሞታቸውን ሐማስ አስታወቀ።

ቡድኑ ለተገደሉት ሰዎች ሞት ምክንያት እስራኤል እየፈጸመችው ያለው የአየር ድብደባ እንደሆነ ገልጾ፣ በርካታ ተዋጊዎቹም ሞተዋል ብሏል።

ሐማስ አርብ ዕለት እንዳስታወቀው እስካሁን እየተካሄደ ባለው የእስራኤል ጥቃት የተገደሉት ታጋቾች ቁጥር ከ70 በላይ ሊሆን እንደሚችል ነው።

ቢቢሲ ይህንን አሃዝ በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻለም።

በአሁኑ ወቅት ሞተዋል የተባሉት ሰባት ሰዎች እስራኤል ከዚህ ቀደም እንደሞቱ ከገለጸቻቸው 31 ታጋቾች መካከል ይካተቱበት እንደሆነ እስካሁን ግልጽ አይደለም።

እስራኤል ሞተዋል በተባሉት ታጋቾቿ ዙሪያ የሰጠችው አስተያየት የሌለ ሲሆን፣ ሐማስም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ማስረጃ አልሰጠም።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ ደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች ተገድለዋል፤ በተጨማሪም 253 ሰዎችንም አግቶ ወደ ጋዛ ወስዷል።

እስራኤል ምላሽ ነው ባለችው አጸፋዊ የማያባራ የተቀናጀ ጥቃት ከ30 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከተገደሉት መካከል አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ካለው የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያስረዳል።

እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ የረሃብ አደጋ እያንዣበበ ስለመሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስጠንቅቋል።

ሐማስ እና እስራኤል በኅዳር ወር በደረሱት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እፎይታ 105 ታጋቾች እንደተለቀቁ ይታወሳል።

እስራኤልም በልውውጡ 240 ሴቶች እና ህጻናት እስረኞችን ፈታለች። እስራኤል አሁንም ከ100 በላይ ታጋቾች በጋዛ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጻለች።

አሁን መሞታቸው የተገለጸው ታጋቾች ሕይወት ያለፈው መቼ እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም።

የሐማስ ታጣቂ ክንፍ ቃሳም ብርጌድ ቃለ አቀባይ አቡ ኦቤይዳ በቴሌግራም ባወጣው መግለጫ ቡድኑ አሁንም ቢሆን ታጋቾችን ለመልቀቅ እና በምላሹ እስራኤል እስረኞችን እንድትፈታ ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል።

በኳታር ለወራት ሲካሄድ የቆየው የተኩስ አቁም ውይይት ዋነኛው ነጥብ ከታጋቾች መለቀቅ ጋር የተያያዘ ነው።

እነዚህ ውይይቶችም ለአጭር ጊዜ የሚዘልቅ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ተደርሶ ታጋቾች እንዲለቀቁ የሚያደርግ ነው። በልውውጡም እስራኤል በእስር ቤቶቿ ውስጥ ካሉት በሺዎች ከሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን የተወሰኑትን ትፈታለች።

ይሁን እንጂ የታጋቾች ሞት እንዲሁም በጋዛ እርዳታ እየተጠባበቁ ከነበሩ መካከል 112 ሰዎች መገደላቸው ውይይቶቹን ሊያደናቅፍ ይችላል የሚል ስጋትን ጭሯል።

እስራኤል በእርዳታ ጠባቂዎች ላይ ተኩስ በመክፈት ንጹሃንን መግደሏን ሐማስ ሲያስታውቅ፣ እስራኤል ግን የማስጠንቀቂያ ጥይት መተኮሷን ተከትሎ በተፈጠረ መረጋገጥ ሕይወታቸው አልፏል ብላለች።