በጋዛ እርዳታ ለማግኘት በተሽከርካሪዎች ዙሪያ የተሰባሰቡ ከ100 በላይ ሰዎች ተገደሉ

በጋዛ እርዳታ ለማግኘት በተሽከርካሪዎች ዙሪያ ተሰባስበው የነበሩ ቢያንስ 112 ፍልስጤማውያን ሲገደሉ፣ 760 የሚሆኑት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ።

ሐሙስ ዕለት በርካቶች የተገደሉበት ክስተት ያጋጠመው በምግብ እጦት የተሰቃዩት ሰዎች በጋዛ በስተደቡብ ምዕራብ በሚገኘው የባህር ዳርቻ መንገድ ላይ በእስራኤል ታንኮች ታጅበው እየተጓዙ ከነበሩ ተሽከርካሪዎች እርዳታ ለማውረድ ሲሞክሩ ነበር።

የእስራኤል ጦር፣ታንክ የተተኮሰው ለማስጠንቀቂያ እንደሆነና የእርዳታ ተሽከርካሪዎቹን እንዳልመታ ገልጿል።

ሆኖም አንዳንድ ፍልስጤማውያን የእስራኤል ወታደሮች ቀጥታ ወደ እነሱ እንደተኮሱባቸው ተናግረዋል።

አንድ ፍልስጤማዊ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አብዛኞቹ ሰዎች የሞቱት እርዳታ የጫኑት መኪኖች አሽከርካሪዎች ወደ ፊት ለመጓዝ በሚሞክሩበት ወቅት ተገጭተው ነው።

የግብፅን እርዳታ የጫኑ 30 ተሽከርካሪዎች በሰላማዊ ሰዎች የተከበቡት የእስራኤል መከላከያ ኃይል “የእርዳታ ማስተላለፊያ ኮሪደር” ባለው ቦታ እየተጓዙ ሳለ ነበር።

ይህ ክስተት ያጋጠመው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር በእስራኤል እና ሐማስ መካከል ግጭት ከተከሰተ አንስቶ 21 ሺህ ሕጻናትና ሴቶችን ጨምሮ ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን ካስታወቀ ከሰዓታት በኋላ ነው።

ሚኒስቴሩ ሰባት ሺህ የሚሆኑ ሰዎች እንደጠፉ እና 70 ሺህ 450 የሚሆኑት ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸውም አክሏል።

ከላይ ሆነው የተነሱ የእስራኤል ምስሎች በተሽከርካሪዎቹ ዙሪያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተሰባስበው ያሳያሉ። በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋሩ ምስሎች ደግሞ ባዶ የእርዳታ መኪናዎች እና የአህያ ጋሪዎች ላይ የተጫኑ አስክሬኖችን አሳይተዋል።

በዚህ ክስተት 112 ሰዎች መገደላቸውንና 760 መጎዳታቸውን የገለጸው በሐማስ የሚተዳደረው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እስራኤልን “ በጅምላ ጭፍጨፋ” ከሷል።

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤትም በዚህ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር አስቸኳይ ዝግ ስብሰባ ለማካሄድ እቅድ ይዟል።

ፈረንሳይም የእስራኤል ወታደሮች ምግብ ለማግኘት የተሰባሰቡ ሰላማዊ ሰዎች ላይ መተኮሳቸው ፍትሐዊ አይደለም ብላለች።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በበኩላቸው ይህ ክስተት በእስራኤል እና ሐማስ መካከል ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እንዲደረግ በአደራዳሪዎች እየተደረገ ያለውን ጥረት ያወሳስባል ብለዋል።

ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) ክስተቱን “ አሰቃቂ” ያለው ሲሆን አስቸኳይ እና ዘላቂነት ያለው የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።

የፍልስጤም ፕሬዚደንት ሞሃሙድ አባስም “አስከፊ ጭፍጨፋ” በመፈፀም የእስራኤልን ኃይሎች ከሰዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ድርጊቱን አውግዘው አስቸኳይ ሰብዓዊ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ያለቅድመ ሁኔታ የእስራኤል ታጋቾች እንዲለቀቁ በድጋሜ ጥሪ አቅርበዋል።

ሰሜን ጋዛ እስራኤል በመጀመሪያው ምዕራፍ ባካሄደችው መጠነ ሰፊ የምድር ጥቃት ውድመት የደረሰበት ሲሆን ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ሥፍራው መድረስ ከቆመ በርካታ ወራት ተቆጥረዋል።

ባለፈው ሳምንት የዓለም ምግብ ፕሮግራም እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎቹ በእስራኤል ፍተሻ ጣቢያ አቅራቢያ በተራቡ ሰዎች በመከበቡ ወደ አካባቢው የሚያደርሰውን እርዳታ ለማቋረጥ መገደዱን ገልጿል።

ማክሰኞ ዕለት የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ባለሥልጣን በጋዛ ሰርጥ ካለው ሕዝብ ሩብ የሚያህለው [576 ሺህ ሰዎች] አስከፊ ለሆነ የምግብ እጥረት መዳረጋቸውን እና ከሁለት ዓመት በታች ከሆኑ ስድስት ሕጻናት አንዱ በከፍተኛ የምግብ እጥረት መጋለጡን በመግለጽ አስጠንቅቀዋል።

በቅርብ ቀናትም በሰሜን ጋዛ በሚገኝ ሆስፒታል አስር ሕጻናት በምግብ እጥረት መሞታቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ተመድ ወደ 300 ሺህ የሚገመቱ ሰዎች በተጠለሉባትና በቂ ምግብ እና ንጹህ ውሃ በሌለባት የጋዛ ሰሜናዊ ግዛት ረሃብ እያንዣበበ እንደሆነ አስጠንቅቋል።

የእስራኤል ጦር ሐማስን ለማጥፋት በሚል በምድር እና በአየር መጠነ ሰፊ ጥቃት የከፈተው ባለፈው ጥቅምት ወር የሐማስ ታጣቂዎች የእስራኤልን ድንበር ዘልቀው በመግባት 1 ሺህ 200 የሚሆኑ ሰዎችን ከገደሉ እና 250 ሰዎችን አግተው ከወሰዱ በኋላ ነበር።