እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ከ30 ሺህ ማለፉን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ

እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ባለው የማያባራ ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ከ30 ሺህ በላይ መድረሱን በሃማስ አስተዳደር ስር ያለው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከተገደሉት መካከል አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውንም ከጤና ሚኒስትሩ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

ከመስከረም መጨረሻ በኋላ የተገደሉት ፍልስጤማውያን ቁጥር ጋዛ ካላት 2.3 ሚሊዮን ያህል ህዝብ 1.3 በመቶው ነው ተብሏል።

የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ጦርነቱ ምን ያህል አስከፊ መሆኑንም አመላካች ነው ተብሏል።

የተገደሉት ሰዎች አኃዝ ምን ያህሉ ሰላማዊ ዜጎች ምን ያህሉ ታጋዮች እንደሆኑ አይገልጽም።

ሚኒስቴሩ በባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 81 ሰዎች መገደላቸውን ገልጾ በአጠቃላይም የተገደሉ ሰዎችን ቁጥርም 30 ሺህ 35 እንደደረሰ በዛሬው ዕለት አስታውቋል።

አጋዙ ሆስፒታል ሳይደርሱ ህይወታቸው ያለፉ ፍልስጤማውያንን ያላካተተ በመሆኑም የተገደሉ ሰዎች ቁጥር እጅግ ከዚህ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል። ከነዚህም ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩት እስራኤል በአየር ጥቃቶቿ ወደ ፍርስራሽነት በቀየረቻቸው ህንጻዎች ስር ተቀብረው ይገኛሉ።

በጥቃቱ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች መጎዳታቸውንም የጋዛ የጤና ሚኒስቴር መዝግቧል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት መረጃዎችን የሚያገኙት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ከጋዛ አስተዳዳሪ ጋር “የረጅም ጊዜ ትብብር” እንዳለው እንዲሁም “በመረጃ አሰባሰብ ወይም ትንተና የዳበረ አቅም” እንዳለው ተናግሯል። አስተዳደሩ ቀደም ሲል ሲያቀርበው የነበሩ ሪፖርቶች በተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች ተዓማኒነት ያለው እና በደንብ የተጠናከረ ነው ተብሎም ይታሰባል።

የዓለም ጤና ድርጅት በባለፉት የጋዛ ጦርነቶች ውስጥ የተገደሉ ፍልስጤማውያንን መረጃ ሲያወዳድርም በአሁኑ የህጻናት እና ሴቶች ሞት ከፍተኛ ከመሆኑም ጋር ተያይዞ በጦርነቱ የተገደሉ የሰላማዊ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑንም ያሳያል ብሏል።

በጋዛ ስለተገደሉ ሰላማዊ ዜጎች እና ታጋዮች የተጠየቀው የእስራኤል ጦር በበኩሉ “10 ሺህ ያህል ገደማ አሸባሪዎች ተገድለዋል” ሲል ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቷል።

የፍልስጤማውያን ሞት በጋዛ የሚመዘገበው አስከሬን ወይም የአስከሬን አካል በህክምና ባለሙያዎች/ በሆስፒታል ሰራተኞች ሲታይ ነው።

በእያንዳንዱ ቀን መጨረሻ ላይ ሆስፒታሎች የሁሉንም ሟቾች ዝርዝሮችን የሚታወቁ ከሆነ ከስማቸው ጋር፣ የመታወቂያ ቁጥር፣ ጥቃት የደረሰባቸው ወይም የሞቱበት ቀን፣ እና የጉዳታቸውንም ሁኔታ ለጤና ሚኒስቴሩ ይልካሉ። የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ለነዚህም መረጃዎች የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል።