ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“በካርቱም ባዶ ቤት ውስጥ የሞተች አያቴን መቅበር አልቻልኩም”
አዝሀር ሾልጋሚ የአያቷን ግብዐተ መሬት ለመፈጸም እየሞከረች ነው።
አያቷ ከሞቱ ቀናት ተቆጥረዋል። በትክክል የሞቱበትን ቀን ማንም አያውቅም።
በሱዳን ጀነራሎች ውጊያ መካከል ብቻቸውን ካርቱም ያለ ቤታቸው ውስጥ ነው ያረፉት።
አዝሀር አሁን ኒው ዮርክ ናት። አያቷን ለማዳን ጥረት ስታደርግ ነበር። አሁን ግን ጥረቷ አያቷን መቅበር ነው።
አዝሀር ብቻ ሳትሆን ብዙዎች ወዳጅ ዘመዶቻቸውን መቅበር አልቻሉም።
ተዋጊዎቹ ጀነራሎች ጅዳ የደረሰቡበት ስምምነት ሰብአዊ እርዳታ ሰጭዎች የሞቱ ሰዎችን እንዲቀብሩና እንዲመዘግቡ ዕድል መስጠትን ይጨምራል።
የቀይ መስቀል የአፍሪካ ቀጠናዊ ኃላፊ ፓትሪክ ዩሴፍ “አስክሬኖች በየመንገዱ እናያለን። ሆስፒታሎች አይሠሩም። አዲሱ ስምምነት ለሰብአዊ እርዳታ በር ይከፍታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ይላሉ።
ስምምነቱ እስካሁን ለሰብአዊ ድጋፍ መንገድ አልከፈተም። ተዋጊዎቹ የተኩስ አቁም ላይ መድረሳቸውን መፈራረም አለባቸው።
የአዝሀር አያቶች አብደላ ሾልጋሚ እና አላወያ ረሽዋን በጦርነቱ ምክንያት መውጣት አልቻሉም።
ካርቱም ውስጥ ባላዲያ በተባለ አካባቢ ነበር የሚኖሩት።
ይህም በዩኬ ኤምባሲና የአገሪቱ ወታደራዊ መቀመጫ አቅራቢያ ነው። ወንድ አያቷ የዩኬ ዜጋ ናቸው። ሦስት ጊዜ ተተኩሶባቸዋል።
የአካል ጉዳተኛ ባለቤታቸው ብቻቸውን የቀሩትም ለዚህ ነበር።
ይኖሩበት የነበረው ሰፈር የጦር ቀጠና ሆኗል።
የአዝሀር ወንድ አያት በተአምር ነው ከሞት የተረፉት። ሴት አያቷ ግን ባዶ ቤት ሞተዋል።
ቤተሰቡ ወንድ አያቷን ከሱዳን ለማስወጣት እየሞከረ ነው።
ቤተሰቡ ለቀናት ለአላወያ በተደጋጋሚ ቢደውልም ምላሽ አላገኘም። ወደ ዩኬ ኤምባሲ ቢደውሉም መልስ አልተገኘም።
ዩኬ ዜጎቿን ከካርቱም ስታስወጣ አያቶቿ መካተት አልቻሉም።
የአያቶቿ ቤት አቅራቢያ ከሚገኘው የቱርክ ኤምባሲ ስልክ የተደወለላት ከቀናት በፊት ነበር።
አያቷ መሞታቸውን አረዷት። ማመን አልፈለገችም።
“መልሼ ደውዬ ምናልባት ኮማ ውስጥ ትሆናለች። የደም ዝውውሯን ፈትሹ፣ ትንፋሽ እንዳላት አጣሩ፣ ልቧ ይመታ እንደሆነ አረጋግጡ አልኳቸው። ሰውነቷ እየረገፈ እንደሆነ ነገሩኝ” ትላለች።
“ብቻዋን መሞቷን ሳስብ ያመኛል። መብራት የለም። በዛ ላይ ሱዳን ያለው ሙቀት ከባድ ነው” ስትል ሐዘኗን ትገልጻለች።
ቢቢሲ ያነጋገራት ሌላ ሰው አጎቷ አሕመድ በዛው አካባቢ እንደሚኖር ትናገራለች።
የአሕመድ ቤተሰብ አብረው አገሪቱን ጥለው ለመውጣት ተሰብስበው ነበር። አሕመድ የግል ሰነዶቹን ረስቶ ወደ ቤት ተመለሰ።
ከስድስት ቀን በኋላ እነ አሕመድ ቤት አቅራቢያ ያለ ሰው ስልክ ደውሎ ሞቱን አረዳቸው።
አሕመድ ቤቱ ሲመለስ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል ወታደሮችን ቤት አግኝቷቸው ነገሮች ተካረሩ።
አሕመድን ገድለው ቤቱን ዘርፈው ሄዱ።
የአሕመድ ጎረቤቶች አስክሬኑን በፕላስቲክ ጠቅልለው የእርዳታ ሰጭዎችን እየጠበቁ ነበር።
እዛው ሊቀብሩት ቢፈልጉም ቤተሰቡ ግን ጎዳና ዳር እንዲቀበር አልፈቀደም። እናም አሁንም አስክሬኑ ከፕላስቲኩ አልወጣም።
አዝሀር የአያቷን አስከሬን የሚወስድላት ሰው እየፈለገች ነው።
“ከአያቴ ጋር እንቀራረብ ነበር። ወደ ኒው ዮርክ ከመሄዴ በፊት መጨረሻ ላይ ያለችኝ ነበር ‘ብቻዬን ትተይኛለሽ ብዬ እፈራለሁ’ ነው። እኔም መቼም አልተውሽም ብዬ ሳቅኩባት። ምንም ቢሆን ሁሌም ካንቺ ጋር ነኝ ብያት ነበር። ግን አልሆነም። እንዳሳዘንኳት ይሰማኛል” ትላለች።