የዓለም ፍጻሜ ተቃርቧል በሚል ልጆቿን የገደለችው አሜሪካዊት እናት ጥፋተኛ ተባለች

የዓለም ፍጻሜ ተቃርቧል በሚል ሁለት ልጆቿን እና የባለቤቷን የቀድሞ ሚስት የገደለችው አሜሪካዊት እናት ጥፋተኛ ሆና ተገኘች።

በርካታ አሜሪካውያኖችን ባስደነገጠው በዚህ የግድያ ወንጀል ሎሪ ቫሎው እና ባለቤቷ ቻድ ዴይቤል በግድያ፣ በማሴር እና በዘረፋ ወንጀል ተከሰዋል።

የ49 ዓመቷ የውበት ባለሙያ በፈጸመቻቸው ወንጀሎች የእድሜ ልክ እስራት ይጠብቃታል።

የልጆቿ የሰባት ዓመቷ ታዳጊ ጆሹዋ ወይም ጄጄ ቫሎው እና የ16 ዓመቷ ታይሊ ራያን አስከሬን በባለቤቷ ቤት ዴይቤል ተቀብሮ የተገኘው ከሶስት ዓመታት በፊት ነበር።

ዳኞች ነፍስ በማጥፋት፣ በሴራ እና በዘረፋ በቀረቡት ስድስት ክሶች ጥፋተኛ ሆና ስለመገኘቷም ሲበይኑ ግለሰቧ ስሜት በሌለው ሁኔታ ከጠበቋቿ አጠገብ ተቀምጣ በችሎቱ ላይ ታይታለች።

ወደ አምስት ሳምንት የፈጀውን የችሎት ሂደት መዝጊያ የሆነውንም የዚህ ብያኔም የሰሙ ዘመዶቿ ክንድ ለክንድ ተያይዘውና በእንባም ተሞልተው ታይተዋል።

አቃቤ ህግ በግለሰቧ ክስ ላይ 60 ምስክሮችን ያቀረበ ሲሆን ታዳጊዎቹ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዴት እንደተገደሉና አስከሬናቸውም የተገኘበትንም ሁኔታ ግልጽ አድርጎ የሚያሳዩ ዝርዝር ማስረጃዎችን አቅርቧል።

በዚህ የፍርድ ሂደት ላይ የሎሪ ጠበቆች ምስክሮችን ያላቀረቡ ሲሆን ራሷም ጥፋቷን ተከላክላ ምስክርነት አልሰጠችም።

የባለቤቷ የቻድ ዴይቤል የፍርድ ሂደት ገና ወራቶች ይቀሩታል።

ዴይቤል በሞርሞን ሃይማኖታዊ አስተምህሮት ላይ የተመሰረቱ በርካታ የምጽዓት ልብወለዶችን የጻፈ ደራሲ ነው።

ጥንዶቹ ለዓለም ፍጻሜ መዘጋጀትን በሚያበረታታ እንቅስቃሴ ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ እንደተዋወቁ ይታመናል።

የሎሪ ጠበቃ ጂም አርኪባልድ ልጆቿን የምትወድ እናት እንደሆነችና በዚህ አስገራሚ የአምልኮ መሪ ፍቅር እንደወደቀች ገልጸው ደንበኛቸውን ከግድያ ጋር የሚያይዛት ምንም ዓይነት ማስረጃ እንደሌለም ተከራክረዋል።

ነገር ግን አቃብያነ ህጉ ሎሪ የልጆቿን እና የባለቤቷን የቀድሞ ሚስት አገዳደል ለማቀነባበር ካበለቤቷ ጋር እንዳሴረች የሚረብሹ መረጃዎች መገኘታቸውን አስታውቀዋል።

“ተከሳሿ ቻድ ዴይቤልን ብቻ በመፈለጓ ይህንንም ለማሳካት በመንገዷ ላይ ያለውን ማንኛውንም መሰናክል አስወገደች” ሲሉ የፍሪሞንት ካውንቲ አቃቤ ህግ ሊንዚ ብሌክ በችሎቱ ወቅት ተናግረዋል።

አክለውም “ተከሳሿ የምትፈልገውን ለማግኘት ገንዘብ፣ ስልጣን እና ወሲብ ተጠቅማለች” ብለዋል።