የፓፕዋ ኒው ጊኒ ሚኒስትር በንጉሥ ቻርልስ በዓለ ሲመት ገንዘብ በማባከናቸው ሥራ አቆሙ

የፓፕዋ ኒው ጊኒ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በንጉሥ ቻርልስ በዓለ ሲመት ወቅት ገንዘብ አባክነዋል የሚል ውዝግብ መነሳቱን ተከትሎ ሥራ አቆሙ።

አገሪቱ ሚኒስትሩን በይፋ ለበዓለ ሲመቱ በላከችበት ገንዘብ ማባከናቸው ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጀስቲን ታካቺንኮ ከልጃቸው ሳቫና ጋር ነበር ለበዓለ ሲመቱ የተጓዙት። ልጃቸው የመጀመሪያ ደረጃ የአውሮፕላን በረራቸውንና በሲንጋፖር ያደረጉትን ግብይት በቲክቶክ ገጿ ስታጋራ ነበር።

ልጅቷን የተቹ ሰዎችን ሚኒስትሩ “ኋላ ቀር እንስሳት” ብለዋቸዋል።

ንግግራቸውን ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቶም ነበር።

ፓፕዋ ኒው ጊኒ ከኮመንዌልዝ አገራት አንዷ ናት።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ጄምስ ማራፔ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ “ከሥራ ለመልቀቅ” እንደተስማሙ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ንሬንድራ ሞዲ ወደ አገሪቱ ጉብኝት ሲያደርጉ ውዝግቡ እክል እንዳይፈጥር ሥራ እንደለቀቁ ተናግረዋል።

“ስለ ጉዳዩ የተነዛው ሐሰተኛ ወሬ እንደጠራም ለማሳወቅ እወዳለሁ” ብለዋል።

የአገሪቱ ጋዜጣ እንደዘገበው ወደ አንድ ሚሊዮን ዶላር በሚጠጋ ወጭ ሚኒስትሩ ከ10 ባለሥልጣኖች ጋር በበዓለ ሲመቱ ተገኝተዋል።

የመንግሥት ቃል አቀባይ ቢል ቶራሶ 10 ባለሥልጣኖች ከ10 እንግዶች ጋር ወደ ለንደን እንደተጓዙ ለሮይተርስ አረጋግጠዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ልጅ በለቀቀችውና አሁን ከገጿ በጠፋው ቪድዮ ቅንጡ የፋሽን መደብሮች ስትገባ ይታያል።

ለሕዝብ አገልግሎት መዋል ያለበት ገንዘብ እየባከነ ነው በሚልም ቁጣ ተነስቷል።

አባቷ ግን “በእነዚህ ሰዎች ልጄ ተጎድታለች። ቅናት መጥፎ ነው። እነዚህ ሰዎች ለአገራቸው የሚያገለግሉ ሰዎችን ከማጠልሸት ይልቅ ሥራ የላቸውም” ብለዋል።

ይህንን ንግግር ካደረጉ በኋላ መልሰው ለንግግራቸው ይቅርታ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው ሕዝቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ይቅርታ እንዲቀበል ጠይቀዋል።