በኢራን ሁለት ግለሰቦች የጸጥታ ኃይል አባልን ገድለዋል በሚል በስቅላት ተቀጡ

በኢራን ሁለት ግለሰቦች ባለፈው ዓመት መንግሥትን በመቃወም በመላ አገሪቷ ተቀስቅሶ በነበረው ተቃውሞ ወቅት የፀጥታ ኃይል አባልን በመግደል ወንጀል በስቅላት ተቀጡ።

ሞሐመድ ማህዲ ካራሚ እና ሰይድ ሞሐመድ ሆሴይኒ የተባሉት ግለሰቦች፣ ታኅሣሥ 2022 ላይ የሞት ፍርድ የተበየነባቸው ቢሆንም የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት ስቃይ ተፈፅሞብናል ካሉ በኋላ ይግባኝ ጠይቀው ነበር።

ይሁን እንጂ የኢራን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአምስት ቀናት በፊት ቅጣቱ እንዲፈፀም ብይን ሰጥቷል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀምስ ክሌቨርሊይ ቅጣቱን አጥብቀው ኮንነዋል።

በአገሪቷ ከተቃውሞው በኋላ መገደላቸው የታወቀ ተቃዋሚዎች ቁጥርም አራት ደርሷል።

ተቃውሞው የተቀሰቀሰው አንዲት ሴት ሒጃቧን በተገቢው መንገድ አልበሰችም በሚል በፖሊስ ተይዛ በፖሊስ ይዞታ ሥር ሳለች ሕይወቷ ማለፉን ተከትሎ ነበር።

የኢራን የፍትሕ ዜና ወኪል፣ ሚዛን ሁለቱ ግለሰቦች የጸጥታ አካል አባል የሆነውን ሩሆላህ አጃሚን በመግደል ዋነኛ ወንጀለኞች ናቸው ብሏል።

አቃቤ ሕግ በበኩሉ የጸጥታ አባሉ በቅርቡ ለተገደለው ሰላማዊ ሰልፈኛ ሃዘናቸውን ለመግለጽ በወጡ ሰልፈኞች እርቃኑን ተደርጎ መገደሉን ገልጿል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የፍርድ ሒደቱን እውነተኛ ያልሆነ ሲል አውግዞ የኢራን ባለሥልጣናት ቢያንስ በሌሎች 26 ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ እየጠየቁ ነው ብሏል።

በስቅላት ከተገደሉት ግለሰቦች አንዱ የሆነው የ22 ዓመቱ ካራሚ ቤተሰቦች ቅዳሜ እለት ከመገደሉ በፊት እንዲያገኙት እንዳልተፈቀደላቸው ተናግረዋል። ሕይወቱን እንዲያተርፉላቸውም የፍትሕ አካላትን ተማጽነው ነበር።

የካራሚ አባት “ከልጄ ላይ የሞት ቅጣቱን አንሱለት፣ ልለምናችሁ" ሲሉም ደጅ ጠንተው እንደነበርም ተናግረዋል።

የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀምስ፣ የኢራን ባለሥልጣናት በራሳቸው ዜጎች ላይ እየፈፀሙ ያሉትን ጥቃት እንዲያቆሙ አሳስበዋል።

የአውሮፓ ኅብረት በበኩሉ በተቃዋሚዎች ላይ የሞት ቅጣት መበየኑ "አስደንጋጭ ነው" ብሏል።

ተቀማጭነቱን ከኢራን ውጭ ካደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የዜና ወኪል የተገኘው አሃዝ እንደሚያሳየው በተቃውሞው ወቅት 70 ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 516 ተቃዋሚዎች የተገደሉ ሲሆን 19 ሺህ 262 የሚሆኑት ደግሞ ታስረዋል። 68 የሚሆኑ የጸጥታ አካላት መገደላቸውንም የዜና ወኪሉ ጠቅሷል።

ተቃውሞውን ተከትሎ ከታሰሩት መካከል አብዛኞቹ በግዳጅ እንዲሰወሩ፣ በማይታወቅ እስር ቤት እንዲቆዩ መደረጋቸው እንዲሁም ማሰቃየትና እንግልት እንደደረሰባቸው ተነግሯል።

የኢራን ባለሥልጣናት ተቃውሞውን "ሁከት" ሲሉ የገለጹት ሲሆን አለመረጋጋቱን አባብሰዋል ሲሉም የውጭ ኃይሎችን ከሰዋል።

በተመሳሳይ ክስ ሌሎች ሦስት ግለሰቦች የሞት ፍርድ የተላለፈባቸው ሲሆን ሌሎች 11ዱ ደግሞ የእስር ፍርድ ተቀብለዋል።

ባለፈው ወር በጸጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት ፈፅመዋል የተባሉ ሌሎች ሁለት ግለሰቦች ላይ የሞት ቅጣት መፈፀሙ ይታወሳል።