ኢራን ከሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የ23 ዓመት ወጣት በስቅላት ቀጣች

በኢራን አሁንም ያላባራው ሕዝባዊ ተቃውሞ የሞት ቅጣትን እያስከተለ ነው።

የኢራን ሚዲያዎች እንደዘገቡት ከሆነ ከተቃውሞ ጋር በተያያዘ የ23 ዓመት ወጣት በሕዝብ አደባባይ በስቅላት ተቀጥቷል።

መጂደሬዛ ራሕናቫርድ የተባለ ወጣት በስቅላት የተቀጣው ትናንት ሰኞ በማሽሀድ ከተማ ነው፥።

ፍርድ ቤት ወጣቱን ‘ከፈጣሪ ጋር በመጻረር” በሚል ጥፋተኛ ሲል በይኖበት ነበር።

ወጣቱ ሁለት የተጠባባቂ ሠራዊት አባላትን በስለት ወግቶ ገድሏል ሲል ዐቃቤ ሕግ ከስ መስርቶበት ነበር።

ራሕናቫርድ በቁጥጥር ሥር በዋለ በ23ኛ ቀኑ ነው በስቅላት የተቀጣው።

የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ቡድኖች ኢራን ተቃዋሚዎችን በይስሙላ ፍርድ በስቅላት እየቀጣች ነው ሲሉ ይከሳሉ።

በስቅላት የተቀጣው ወጣት ወላጅ እናት ፍርዱ ከተፈጸመ በኋላ ነው ስለ ልጃቸው በስቅላት መቀጣት የተነገራቸው።

ከኢራን የወጡ ዘገባዎች እንደሚሉት ቤተሰቡ በቅድሚያ የመቃብር ስፍራ ቁጥር እንዲነገራቸው ተደረገ። ከዚያ ሲደርሱ ለልጃቸው አስክሬን አፈር እየተማሰ ደረሱ።

ይህ ወጣት በስቅላት ሲቀጣ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች የተለቀቁ ሲሆን በነዚህ ምሥሎች በአንዱ አንድ ማንነቱ የማይለይ ሰው በፍርድኛው አንገት ሥር ሸምቀቆ ገመድ ሲያጠልቅ ይታያል።

ምን ያህል ሰዎች በዚህ ስቅላት ቅጣት ላይ እንደተገኙ ግልጽ አይደለም።በምሥሉም ላይ በግልጽ አይታይም።

ራሕናቫርድ በፍርድ ሂደቱ የራሱን ጠበቃ ለማቅረብ አልተፈቀደለትም ነበር።

ራሕናቫርድ ከሞት ቅጣቱ ቀደም ብሎ በኅዳር ወር ሁለት የተጠባባቂ ጦር ሠራዊት አባላትን በስለት በመውጋት እንደገደለ በኢራን የተለያዩ ሚዲያዎች ሲዘግቡ ነበር።

ባሲጅ የሚባሉት እኒህ የተጠባባቂ ሠራዊት አባላት ኢራን ብዙውን ጊዜ ተቃውሞዎች ሲነሱ የምታሰማራቸው ወታደሮች ናቸው።

አንድ በኖርዌይ መቀመጫውን ያደረገ የኢራን የመብት ተሟጋች ድርጅት ባልደረባ የሆኑት መሐሙድ አሚሪ ሙጋዳም በትዊተር ሰሌዳቸው እንዳሰፈሩት ራሕናቫርድ የተገደለው በግድ ያልፈጸመውን ፈጽሜያለሁ ብሎ እንዲናዘዝ ከተደረገ በኋላ ነው።

የፍርድ ሒደቱም ገለልተኛና ፍትሐዊ አልነበረም ብለዋል።

በኢራን ትኩስ ተቃውሞ የተቀሰቀሰው አንዲት ማሻ አሚኒ የምትባል የ22 ዓመት ወጣት በግብረ ገብ ፖሊሶች ድብደባ ደርሶባት ሞታለች በሚል ነው።

አሚኒ በኢራን የግብረ ገብ ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር ውላ የነበረው ሒጃብ በትክክል አልጠመጠምሽም በሚል ባለፈው በመስከረም ወር ነበር።

ከዚያን ጊዜ የጀመረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ዛሬም አላባራም።

አሁን በኢራን 161 ትንንሽ ከተሞችና 31 ወረዳዎች ተቃውሞ እየተካሄደ ነው።

እንደ አውሮጳዊያኑ በ1979 ከተደረገው ከኢራን ኢስላማዊ አብዮት ወዲህ እንዲህ ያለ መጠነ ሰፊ ሕዝባዊ ተቃውሞ በኢራን ታይቶም ተሰምቶም አያውቅም።

የኢራን ባለሥልጣናት ለዚህ ሕዝባዊ ተቃውሞ አሜሪካንና እስራኤልን ተጠያቂ ያደርጋሉ።