ምሥጢራዊ ሰነዶችን ያወጣው ወጣት አሁንም የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ነው ተባለ

ምሥጢራዊ ሰነዶችን ይፋ በማድረግ የተከሰሰው ጃክ ቴሼራ አሁንም የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ነው ሲል የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ተናገረ።

ከ100 በላይ ገጾች ያሉትን ምሥጢራዊ ሰነዶች አደባባይ ያወጣው ወጣት አሁንም ቁልፍ የሚባሉ ሰነዶች በእጁ ሊኖሩ ይችላሉ ሲል ዐቃቤ ሕግ ስጋቱን ገልጿል።

በአሜሪካ አየር ኃይል ብሔራዊ ዘብ የዝቅተኛ እርከን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ የሆነው የ21 ዓመት ወጣት ከሳምንታት በፊት ምሥጢራዊ ሰነዶችን በማውጣቱ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ይታወሳል።

ቴሼራ ይፋ ባደረጋቸው ሰነዶች በዩክሬን እየተካሄደ ስላለው ጦርነት ምሥጢራዊ ጉዳዮችን ይፋ ከማድረጉም በላይ አሜሪካ በአጋሮቿ ላይ ስለላ ስለማድረጓ አጋልጧል።

ሰነዶቹ የምዕራባውያን አገራት ልዩ ኃይሎች በዩክሬን ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ስለመሆናቸው አሳይቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ሰነዶቹ የተባባሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጌቴሬዝ የሩሲያን ፍላጎት ለሟሟላት ፍላጎት አላቸው ብላ አሜሪካ እንደምታምን ሰነዶቹ አጋልጠዋል።

ዐቃቤ ሕግ የ21 ዓመቱ ወጣት ከእስር ቤት ከወጣት ከተጠያቂነን ለማምለጥ ሊሸሽ ስለሚችል ጉዳዩን በእስር ቤት ሆኖ መከታተል አለበት ብለዋል።

መርማሪዎች እስካሁን ድረስ ከፍተኛ አገራዊ ምሥጢሮች እንዴት ቴሼራ እጅ ገቡ የሚለውን ለመለየት እየሠሩ ነው።

የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ጃክ ቴሼራ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ በመኖሪያ ቤቱ እንዲወድሙ የተደረጉ እና ቆሻሻ መጣያ ውስጥ የተጣሉ ላፕቶፕ ኮምፒዩተር፣ ታብሌት እና ኤክስ ቦክስ ጌም መጫወቻ ተገኝቷል ብሏል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ወጣቱ ምሥጢራዊ ሰነዶቹን ሆነ ብሎ አደባባይ ማውጣቱን ቢናሩም፤ ጃክ ቴሼራ ሰነዶችን አሾልኮ ለማውጣት ምን እንዳነሳሳው ያሉት ነገር የለም።

ክስተቱን ተከትሎ በወጣትነት ዕድሜ እና በታችኛው እርከን ባለ ሠራተኛ እጅ እንዲህ አይነት አገራዊ የምሥጢር ሰነድ እንዴት ሊገባ ቻለ የሚሉ ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይተዋል።

የአሜሪካ አየር ኃይል ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የጃክ ቴሼራ ምድብ ውስጥ የበላይ አለቆች የሆኑ ሁለት ኮማንደሮች ከሥራ ታግደውም ምርመራ እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል።

ቴሼራ ምሥጢራዊ ሰነዶቹን በማውጣቱ እስከ 15 ዓመታት በእስር እንዲያሳልፍ ሊፈረድበት ይችላል።