ጥፍረ መጥምጥ፡ “ጥፍሬን ስለማፍርበት እደብቀዋለሁ”

ወይዘሪት ጊፍቲ አሰፋ መምህር ናት።

ከአስራ አምስት ዓመት በፊት የጀመራት ህመም አሁንም አልለቀቃትም።

መጀመሪያ የእጇ ጣቶች ጥፍር አካባቢ ያሳክካት ነበር። ከዚያ በኋላ ጥፍሯ ላይ የማይጠፋ ምልክት ማየት ጀመረች።

በዚህ የተነሳ የአውራ ጣቷን በሌሎች ጣቶቿ ትሸፍን ነበር።

“ከላይ ያለው ቅርፊት ይነሳል። ከቅርፊቱ ስር እንደ ብናኝ ዓይነት ይበናል” ትለላች ጊፍቲ ስለ ህመሟ ስታስረዳ።

ድንገት ጣቷን ያዩ ሰዎች ይህ ምንድን ነው? ሲሏት ታፍራለች።

“ጥሩነቱ ችግሩ ያለው አንደኛ ጥፍሬ ላይ ብቻ ስለሆነ የአውራ ጣቴን በሌሎቹ ጣቶቼ እደብቃለሁ።”

ወዳጆቿ ጥፍሯን የጥፍር ቀለም እና ሌሎች ነገሮችን እንድትቀባ ይመክሯታል። ግን መፍትሔ አልሆነላትም።

ዶ/ር ባሸና መሬሳ በወለጋ ዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል የቆዳ እና የአባላዘር በሽታዎች ሐኪም ናቸው።

ጥፍራችን ላይ የሚወጡ ነገሮች በሙሉ መንስዔያቸው ፈንገስ ነው ማለት ባይሆንም ዋናው ምክንያት ግን ፈንገስ ነው ይላሉ።

ለዚህም መንስዔው ሰዎች በእግር ጣታቸው መካከል የሚገኝን ፈንገስ (tinea pedis fungus) ሳይታከሙ ከቆዩ እንዲሁም የጋራ መታጠቢያ ቦታዎችን የሚጠቀሙ ከሆነ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው ይተላለፋል ይላሉ።

ያ የፈንገስ ኢንፌክሽን የእግር ጣት ጥፍርን ከያዘ በኋላ ወደ እጅ ጣት ጥፍርም እንደሚተላለፍ የቆዳ ሕክምና ባለሙያው ያስረዳሉ።

ብዙ እቃ እና ልብስ በማጠብ ረዥም ጊዜ ውሃ ውስጥ የሚያሳልፉ ሰዎች ይህ ችግር በጥፍራቸው ላይ እንደሚከሰትም ጨምረው አስረድተዋል።

የጥፍር ፈንገስ ዓይነት አለው የሚሉት ዶ/ር ባሸና፣ ጥፍር ከተወጋ ወይንም ችግር ከገጠመው ለፈንገስ ጥቃት አመቺ ሁኔታን ስለሚፈጥር የፈንገስ ኢንፌክሽን ሊፈጥር እንደሚችል ይገልጻሉ።

ለብዙ ጊዜ እርጥበት ባለው እና ሞቃታማ በሆነ ጫማ ውስጥ እግር ከቆየ፣ በፈንገስ ለመያዝ ምቹ ሁኔታ ይመቻቻል።

የጥፍር ጤና

ጥፍር የተለያየ ጥቅም አለው የሚሉት ዶ/ር ባሸና፣ ዋነኛው እና የመጀመሪያው የእጅ እና የእግር ጣቶቻችንን ከአደጋ መጠበቅ መሆኑን ያስረዳሉ።

የሰው ልጅ ውበቱን ከሚገልጽባቸው ነገሮች መካከል አንዱም ጥፍር ነው።

ከዚህ ባሻገር ደግሞ የአካላችንን ሙቀት በመቆጣጠር ላይም ድርሻ አለው።

ታዲያ ይህንን የተለያየ ጥቅም ያለውን የሰውነታችንን ክፍል ጤና ለመጠበቅ ብዙ ትኩረት ስንሰጥ አይታይም።

ለዚህም ነው በዓለም ላይ ከ10 እስከ 14 በመቶ ያሉ ሰዎች የጥፍር ፈንገስ ያለባቸው።

በፈንገስ ተይዘው ወደ ሕክምና ተቋም የሚመጡ ሰዎች “ጥፍር ቀለም ሳይቀቡ እና መድኃኒት ሳይወስዱ” ቢመጡ መልካም መሆኑን ባለሙያው ይመክራሉ።

ጥፍር በፈንገስ ሲጎዳ ለሌላ ለበሽታ ሊያጋልጠን ይችላል የሚሉት ዶ/ር ባሸና፣ “ለምሳሌ በጥፍራችን ዙርያ ላሉ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ሊያጋልጡን ይችላሉ። ከዚያም አልፎ በመገጣጠሚያ እና በጥፍራችን ስር ያሉ አጥንቶችን ለበሽታ ሊያጋልጡ ይችላሉ። ግን እነዚህ ነገሮች አልፎ አልፎ ነው ሊከሰቱ የሚችሉት።”

ሰዎች የጥፍር ፈንገስ ከመያዛቸው በፊት ብዙ ጊዜ በእግሮቻቸው ጣቶች መካከል ፈንገስ ይገኝባቸዋል።

ይህንን በጊዜ መታከም እንደሚያስፈልግ ዶ/ር ባሸና ይናገራሉ።

“ጥፍራቸው መካከል ነጭ ሲሆን፣ የመፋቅ ባሕሪ መታየት ሲጀምር ወይንም ደግሞ ከዚህ በፊት ያልተለመደ ሽታ ካለው መታከም አለባቸው። ይህ ምልክት መታየት ከጀመረ በኋላ ክፍት ጫማ ቢያደርጉ ይመረጣል።”

ብዙ ጊዜ የሚጠቃው ማን ነው?

የጥፍር ፈንገስ ጥፍር እንዲወፍር፣ መልኩ እንዲጠፋ ወይንም ጥፍር እንዳይጠነክር ያደርጋል።

ለዚህ በሽታ የትኛውም ግለሰብ ሊገለጥ ይችላል።

ዶ/ር ባሸና እንደሚሉት እድሜያቸው የገፋ፣ ስኳር በሽታ ያለባቸው እና ኮሌስትሮል ያለባቸው ሰዎች በበለጠ ሁኔታ ለፈንገስ ይጋለጣሉ።

ጥፍራቸው በፈንገስ የሚጠቃ ደግሞ፣ በሽታ የመከላከል አቅማቸው የተዳከመ፣ በእግራቸው ዙሪያ የደም ዝውውራቸው ዝቅ ያለ መሆኑን ጨምረው ያስረዳሉ።

ብዙ ጊዜ ለዚህ በሽታ የሚጋለጡ ሰዎች አትሌቶች ናቸው የሚሉት ዶ/ር ባሸና፣ ምክንያቱን ሲገልጹም ብዙ ጊዜ ሽፍን ጫማ አድርገው ስለሚውሉ ነው ይላሉ።

ከዚህ በሽታ ራስን ለመጠበቅም የእጅ እና የእግር ንጽህናን መጠበቅ፣ የእጅ እና የእግር ጥፍሮችን መከርከም፣ ብዙ ሰዎች ገላቸውን የሚታጠቡበት ስፍራ አለመታጠብ፣ ጥፍር መቁረጫን በጋራ አለመጠቀም፣ የጥፍር የውበት ሳሎን ሲጠቀሙም ጽዳታቸው የተጠበቁትን መምረጥ ተገቢ ነው።

ለጥፍር የሚደረገው ሕክምና

የጥፍር ፈንገስ እንደሌሎች የፈንገስ ዓይነቶች መታከም የሚችለ መሆኑን ዶ/ር ባሸና ይናገራሉ።

ጥፍሩ በፈንገስ የተጠቃ አንድ ሰው ሐኪም ቤት ከሄደ በኋላ መጀመሪያ ፈንገሱ መመርመር አለበት።

የሕክምና ባለሙያዎች ይህንን ከለዩ በኋላ አስፈላጊውን መድኃኒት ይሰጣሉ።

“የሚወሰደው መድኃኒት የእጅ ጥፍር ከሆነ እስከ ሦስት ወር ወይንም ከዚያ በላይ ሊወሰድ ይችላል። የእግር ጥፍር ከሆነ ከሦስት ወር እስከ ስድስት ወር ሊወሰድ ይችላል። ጥፍራችን አዲስ ለመብቀል ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት ሊፈጅ ይችላል።”

ከሚዋጥ መድኃኒት ውጪ የሚቀባ መድኃኒትም መኖሩን የሚናገሩት ዶ/ር ባሸና፣ ነገር ግን በሚቀባው መድኃኒት ብዙ ጊዜ ለውጥ እንደማይታይ ይገልጻሉ።

ለዚህም ምክንያቱ ፈንገሱ የሚያጠቃው ጥፍርን እና የጥፍር እድገት ከሚጀምረው ቦታ መሆኑ ነው።

“አልፎ አልፎ ግን የሚቀቡ መድኃኒቶች ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ። አንዳንዴ ፀረ ፈንገስ መድኃኒቶች ለውጥ ላያመጡ ይችላሉ። ያኔ ሌላ አማራጭ አለ። ያንን ፈንገስ ሊያነሱ የሚችሉ ሌሎች ኬሚካሎች አሉ።”