ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያዊቷ መሠረት እና የሌሎች አረጋውያን ሕይወት በኑሮ ውድነት ዘመን
የወ/ሮ መሠረት አዲስ ድምጽ በጣም የደከመና የሚንቀጠቀጥ ነው። የ83 ዓመታቸው ሲሆን አብዛኛውን ጊዜያቸውን አልጋ ላይ ነው የሚያሳልፉት።
በአፍንጫቸው በኩል በገባላቸው ለመተንፈስ በሚረዳቸው ቱቦ በኩል ነው አየር ወደ ሰውነታቸው የሚያስገቡት።
“መሰቃየት አልፈለግም፤ መራብ አልፍለግም፤ እንዲበርደኝም አልፈልግም” ይላሉ ወ/ሮ መሠረት።
አዲስ አበባ ውስጥ በምትገኝ ትንሽዬ ቤታቸው ውስጥ ከሦስት የልጃቸው ልጆች ጋር ነው የሚኖሩት። ባሏ የሞተባለት ሴት ልጃቸው ልጆቿን ወ/ሮ መሠረት ላይ ጥላ የሞተችው በስኳር ህመም ምክንያት ነው።
ልጆቹ ቁርስ እና ምሳ ትምህርት ቤታቸው ውስጥ ስለሚቀርብላቸው እዚያ ይመገባሉ፣ ወ/ሮ መሠረትም ያለቻቸውን ትንሽ ነገር ቀራርመው እራት ይሰጧቸዋል። እሳቸው ደግሞ ከልጆቹ የሚተርፈውን በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ይመገባሉ፣ እሱም ከተገኘ።
“ቆሎ ብቻ በልተን ውሃ ጠጥተን ነው የምንተኛው። እሱም ካልተገኘ የምንበላው አይኖርም፣ ሳንበላ የምንተኛበትም ጊዜ አለ። ምንም ማድረግ አንችልም።”
ይህ ታሪክ የወ/ሮ መሠረት አዲስ ብቻ ታሪክ አይደለም።
ችላ የተባሉት አረጋውያን
ቢቢሲ የዋጋ ግሽበት በዓለም ዙሪያ ያስከተለውን ቀውስ በተመለከተ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ በዕድሜ የገፉ አዛውን ሴቶችን እና ወንዶችን አናግሯል።
ይህም ለከባድ ችግር መጋለጣቸውን፣ በሌሎች እርዳታ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ጥገኛ መሆናቸውን እንዲሁም መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ፈተና እንደገጠማቸው የሰጡት ምስክርነት ያሳያል።
“አረጋውያንን በተመለከተ ያለው መረጃ ሙሉ ለሙሉ ተዘንግቷል” የሚሉት በተባበሩት መንግሥታት የአረጋውያን ሰብአዊ መብቶች ገለልተኛ ባለሙያ የሆኑት ክላውዲያ ማህለር ናቸው።
“ከዕይታ ውጪ ስለሆኑ፣ ካሉት የድጋፍ ሥርዓቶች አንጻር ችላ ተብለዋል” በማለት ድምጻቸው በሚሰማ በሌሎች ቡድኖች ተሸፍነዋል ሲሉ ባለሙያው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአረጋውያን ላይ የሚሰራው ሄልፕኤጅ በ10 አገራት ውስጥ ባደረገው ጥናት፣ በችግር ምክንያት በዕድሜ የገፉ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ልመናን እና በሆስፒታል ውስጥ የሚሰጥ ህክምናን መተውን የመሳሰሉ “ከባድ እርምጃዎችን” ለመውሰድ መገደዳቸውን አመልክቷል።
በቀዝቃዛው የመኝታ ክፍላቸው ውስጥ የተለበሱትን ብርድ ልብስ እየሳቡ ወ/ሮ መሠረት አዲስ “እንደምታዩኝ ታምሜ አልጋ ላይ ነኝ። የሚረዳኝ ካላገኘሁ፣ ሞትን ብቻ ነው መጠበቅ የምችለው” ይላሉ።
ከአዲስ አበባ ከ4,000 ኪሎ ሜትር በላይ ርቃ በምትገኘው በሊባኖሷ ዋና ከተማ ቤይሩት ውስጥ ባለ አልጋ ላይ ተኝተው የሚገኙት 67 ዓመቷ አሊስ ቾባኒያንም ተመሳሳይ አሳዛኝ ነገር ነው የሚናገሩት።
“እራሴን ለማጥፋት ስለሞከርኩባቸው በርካታ ጊዜያት ለመናገር አልፈልግም” ይላሉ።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ይህ ዓለም አቀፋዊ ቀውስ በዕድሜ በገፉ ሰዎች ላይ የሚያሳድረው የአእምሮ ጤና ተጽእኖ ቀላል የሚባል አይደለም።
“የሚያጋጥማቸው ድብታ በአግባቡ ትኩረት አያገኝም። ‘ከዕድሜ ጋር የተያያዘ’ ነገር ተደርጎ ነው የሚወሰደው። ነገር ግን ይህ በአጠቃላይ ችላ የተባለ ከባድ ጉዳይ ነው” ይላሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያዋ ክላውዲያ ማህለር።
ወ/ሮ ቾባኒያን ቤይሩት ውስጥ ያለችውን ትንሽዬዋን የመኝታ ክፍላቸውን፣ በቅርቡ ከባሎቻቸው ጋር ከተፋቱት ሁለት ሴት ልጆቻቸው እና ከስምንት የልጅ ልጆቻቸው ጋር በአጠቃላይ ከአስር ሰዎች ጋር ይጋሯታል።
እንደሚሉት ባለፉት ሦስት ዓመታት የቤተሰባቸው የገቢ ሁኔታ እየከፋ በመሄድ “ከዚህ በፊት ከነበረው ሁኔታ እጅግ ከብዶ አሁን ላይ ደርሷል።”
ተደራራቢ ቀውሶች
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንደሚለው በአውሮፓውያኑ 2019 እጅግ የከፋ የምግብ ዋስትና ችግር የነበረባቸው ሰዎች ቁጥር 135 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፣ ይህ አሃዝ በ2022 ወደ 345 ሚሊዮን ከፍ ብሏል።
በኮቪድ ወረርሽኝ እና በአየር ፀባይ ለውጥ ላይ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችው ወረራ ተደምሮ የምግብ፣ የኃይል እና የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለትን በማወኩ የዋጋ ግሽበቱ ሰማይ እንዲደርስ አድርጎታል።
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ቀውስ ውስጥ የገባችው ሊባኖስ ውስጥ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት የምግብ ዋጋ ግሽበቱ 372.8 በመቶ ደርሶ ነበር።
“ሴቶቹ የልጆቼ ልጆች የዶሮ ሥጋ መዐዛን ለማሽተት ሲሉ ብቻ፣ ወደ ሥጋ ቤቶቹ አካባቢ በእግራቸው ወዲያ ወዲህ ብለው ይመለሳሉ” ይላሉ ወ/ሮ ቾባኒያን።
“ትናንት እንደራባቸው ነገሩኝ። የምሰጣቸው ምንም ነገር አልነበረኝም፣ እናም ‘የዶሮ ሥጋ በህልማችን ስንበላ ለማየት ተስፋ አድርገን እንተኛ’ አሉ።”
አረጋዊ ሴቶች ላይ የጠናው ችግር
እንደ ወ/ሮ መሠረት እና ቾባኒያን ያሉ በዕድሜ የገፉ ሴቶች “የዚህን ቀውስ መራራውን ጽዋ ይጎነጫሉ” ይላሉ ባለሙያዎች።
“የምግብ ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ ማኅበራዊው ደንብ ሴቶች ምግባቸውን በመተው ለሌሎች የቤተሰባቸው አባላት እንዲሰጡ ያደርጋል። በተጨማሪም በሰፈነው የጾታ እኩልነት መጓደል ምክንያት ሴቶች የራሳቸውን ገቢ አያገኙም” ይላሉ የሄልፕኤጅ የገቢ ዋስትና ኃላፊው ቦብ ባባጃኒያን።
ሴቶች ቤት ውስጥ ውለው ገቢ በሚያስገኝ ሥራ ላይ የመሰማራት ዕድላቸው መጥበቡ፣ የሚያገኙት ገቢም አነሳ መሆን፣ የተሻለ የትምህርት ዕድል አለማግኘታቸው እንዲሁም በጡረታ እና በዕለት ክፍያ ከወንዶች ዕኩል በቂ ድጋፍ አለማግኘታቸው ችግራቸውን ያባብሰዋል።
ነገር ግን በዕድሜ የገፉ ወንዶችም ተመሳሳይ ከባድ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል።
ፓኪስታን ኢዝላማባድ ውስጥ የመኪና ማጠቢያ ድርጅት ባለቤት የሆኑት ዛዩዲን ኺልጂ ባለቤታቸው ለሰባት ዓመታት የኩላሊት እጥበት ሲደረግላቸው ቆይተው ያረፉት ባለፈው ወር ላይ ነው።
ዛዩዲን ኺልጂ 68 ዓመታቸው ቢሆንም የጡረታ ገቢ ስለሌላቸው መኪና የማጠብ ሥራቸውን መቀጠል አለባቸው። ነገር ግን ካለፈው ዓመት ወዲህ አብዛኞቹ ደንበኞቻቸው መምጣት ትተዋል።
በአቧራ የተሸፈነ አንድ ማሽንን እያሳዩም “በፊት በሥራ ብዛት ፋታ አልነበረንም። አሁን ግን ከጠዋት ጀምሮ ያገኘሁት ሥራ ይህ ብቻ ነው” ብለዋል።
ባለፈው የካቲት በፓኪስታን ውስጥ ያለው የዋጋ ንረት ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ከታየው በእጅጉ ከፍተኛ ነው የተባለው ተመዝግቧል።
ዛዩዲን ኺልጂ የሚኖሩት በሥራ ቦታቸው ሲሆን፣ አሁን የኪራይ ዋጋው በእጥፍ ጨምሮባቸዋል። ለሚስታቸው ህክምና የወሰዱት ብድር በጨመረው የወለድ መጠን ምክንያት ዕዳቸው ከፍ ብሏል።
“የስኳር ህመምተኛ ነኝ፣ የልብ ችግርም አለብኝ። ኩላሊቴንም ያመኛል። የምወስዳቸው መድኃኒቶች በአሁኑ ወቅት በጣም ተወደዋል። አንዳንድ ጊዜም መድኃኒት አልወስድም። መግዛት ስችል ነው የምወስዳቸው። ታዲያ ምን ማድረግ እችላለሁ?”
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዋ ወ/ሮ መሠረት አዲስም ለሳምባቸው የሚያስፈልጓቸውን አብዛኞቹን ወሳኝ መድኃኒቶችን ገዝተው መውሰድ አቁመዋል።
የኢትዮጵያዊቷ እና የፓኪስታናዊው አረጋውያን ያሉበት ሁኔታ ሄልፕኤጅ ያደረገውን ጥናት የሚደግፍ ነው። በዓለም ዙሪያ ያጋጠመው የዋጋ ንረት አረጋውያንን ከህክምና አገልግሎት እና ከመድኃኒቶች አቅርቦት እንዲርቁ እንዳደረጋቸው ጥናቱ ይገልጻል።
እርዳታ ጠባቂ መሆን
ዓለምን ያጋጠመው የዋጋ ንረት ቀውስ በአረጋውያን ላይ ያስከተለው ጫና ኢትዮጵያን፣ ሊባኖስን እና ፓኪስታንን በመሳሰሉ በማደግ ላይ ካሉ አገራት ባሻገር፣ በባለፀጋዋ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥም ይስተዋላል።
ጡረተኛዋ ነርስ የ74 ዓመቷ ታባኒ ሲቶሌ በደቡባዊ ለንደን ውስጥ ነው ነዋሪነታቸው። የዕለት ጉርሳቸውን በማኅበረሰብ ከሚመራው ‘የምግብ ባንክ’ ያገኛሉ።
“ሁሉ ነገር መልካም ስለነበረ በሕይወቴ ከምግብ ባንክ የምግብ እርዳታ እወስዳለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም። ትንሽዬ ቁጠባ ስለነበረኝ ‘እነዚህ ሰዎች ለምን የምግብ ባንኮችን ምግብ ይጠቀማሉ?’ ብዬ አስብ ነበር” ይላሉ አሁን እራሳቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን እየገለጹ።
ከሦስት ዓመታት በፊት ጡረታ ሲወጡ “ቀሪ ሕይወታቸውን ማጣጣም ሊጀምሩ መሆኑን” አስበው ነበር። ነገር ግን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የኑሮ ውድነት ማጋጠሙ ሁሉን ነገር ለውጦታል።
“አንዳንድ ጊዜ የሆነ ነገር ያምረኛል። ነገር ግን አሁን የሚያሳስበኝ አምሮቴን መወጣት ሳይሆን፣ ምግብ በልቶ ማደር ነው፣ በቂ ምግብ ማግኘት።”
ወ/ሮ ሲቶሌ ሴት ልጃቸው የሁለት ወር ጨቅላ ሳለች ነበር ባለቤታቸውን በሞት ያጡት። አሁን ከብቸኛ ልጃቸው ጋር ይኖራሉ።
“ቢያንስ ልጄ አጠገቤ አለች። ስዚህም ነው የሚያስፈልገኝን ማግኘት የቻልኩት።”
ምንም እንኳን የተለመደ ቢሆንም በዕድሜ የሚገፉ ሰዎች አሃዝ እየጨመረ ሲሄድ በቤተሰብ አባል ላይ ጥገኛ መሆን ብዙም አዛላቂ አይሆንም።
በለንደኑ ኪንግስ ኮሌጅ በዕድሜ መግፋት ዙሪያ ጥናት የሚያደርገው ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ዊ ያንግ “በቀጣዩቹ ጥቂት አስርታት በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ዕድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቁጥር በሁለት ወይም በሦስት ዕጥፍ ይጨምራል።
“ሁሉም በእርጅና ዘመን የሚደግፋቸው ወጣት የቤተሰብ አባል ይኖራቸዋል ማለት ስለማይቻል፣ መንግሥታት አረጋውያንን በዘላቂነት የሚደግፉበት እና የሚንከባከቡበትን ዘዴ መቀየስ ይኖርባቸዋል” ብለዋል ዶ/ር ያንግ።