የሕዝባቸውን ቁጥር ለመጨመር ልጆች ለሚወልዱ ዜጎች ማበረታቻ የሚሰጡ አገራት

የሕዝብ ቁጥር ማሽቆልቆል እና የወሊድ ምጣኔ መቀነስ ለበርካታ አገራት አሳሳቢ ሆኗል።

አዲስ የሚተካ ትውልድ ቁጥር እየተመናመነ ነው። በአንዳንድ አገራት አረጋውያን ጧሪ አጥተው ፊታቸውን ወደ ሮቦቶች እስከ መዘርጋት ደርሰዋል።

ትኩስ የሠራተኛ ኃይል እጥረትም አጋጥሟቸዋል።

ይህም በምጣኔ ሃብታቸው ላይ ተፅዕኖ እያደረሰ እንደሆነ ጥናቶች እያመለከቱ ነው።

ይህንን ስጋት ለመቀልበስ ታዲያ “እባካችሁ ውለዱ!” የሚል ተማፅኖን ጨምሮ ሌሎች የማበረታቻ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው።

ቻይና በስድስት አስርት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ ብዛቷ መቀነሱን አስታውቃለች።

የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳም የወሊድ መጠን መቀነስ አገራቸውን አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንደጣላት በመግለጽ፣ የአረጋውያን መብዛት “አስቸኳይ መፍትሔ የሚሻ አደጋ ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም “ጃፓን እንደ ማኅበረሰብ እንቅስቃሴ የምታቆምበት አፋፍ ላይ ትገኛለች” ብለዋል።

በአገሪቷ ያለው የወሊድ መጠን አዲስ ክብረ ወሰን በሆነ መጠን መቀነሱን ተከትሎም የቶክዮ ባለሥልጣናት፣ ዜጎቻቸው ልጆችን እንዲወልዱ ለማበረታታት ከሕጻናት ጋር የተያያዙ ፕሮግራሞች ላይ የሚያወጡትን ገንዘብ በእጥፍ እንደሚጨምሩ አስታውቀዋል።

ይሁን እንጂ ይህ ችግር እያሳሰባቸው ያለው ጃፓን እና ቻይናን ብቻ አይደለም።

ሌሎች አገራትም የወሊድ መጠንን ለማሳደግ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው። የተወሰኑትን እንመልከት፦

ረጅም የወሊድ ፈቃድ ለእናቶች

የ33 ዓመቷ ቦረያና አንድሪቫ ግራማቲኮቫ፣ ልጇን በቡልጋሪያ ከወለደች በኋላ ለ12 ወራት ያህል በየወሩ ሙሉ በሚባል ደረጃ ደመወዟ ተከፍሏታል።

“ለመጀመሪያው ዓመት የወሊድ ፈቃድ የደመወዟ 90 በመቶ ይከፈላል። ከዚያ ለሁለተኛው ዓመት ደግሞ ከዚህ አነስ ያለ ክፍያ ይሰጣል” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

እንደ የዓለም ባንክ ከሆነ፣ ቡልጋሪያ ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸው በርካታ አረጋውያን ካሉባቸው የአውሮፓ ኅብረት አገራት መካከል አንዷ ናት።

ቡልጋሪያ 22 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧም ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ነው።

ይህንንም ለመቀልበስ በዓለም ላይ በሙሉ ክፍያ ረጅም የተባለ የወሊድ ፍቃድ ለእናቶች ትሰጣለች።

በዓለም አቀፉ የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ሪፖርት ውስጥ ከተካተቱ ያደጉ አገራት መካከል ለእናቶች ከሙሉ የደሞዝ ክፍያ ጋር ቢያንስ የ6 ወር የወሊድ ፈቃድ የሚሰጡት ግማሽ የሚሆኑት ብቻ ናቸው።

በዚህ ሪፖርት ኢስቶኒያ ለ85 ሳምንታት ከሙሉ ክፍያ ጋር ለእናቶች ረጅሙን የወሊድ ፍቃድ የምትሰጥ ሲሆን፣ አሜሪካ ግን ብሔራዊ የክፍያ ፈቃድ ፖሊሲ የላትም።

ግራማቲኮቫ “ልጅ ለማሳደግ ቢያንስ ሁለት ዓመት የሥራ እረፍት ከክፍያ ጋር ማግኘት ደኅንነት እንዲሰማን ያደርጋል” ትላለች።

“ከልጅሽ ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ ዕድል ታገኛለሽ። ልክ እንደእኔ ልጅ ታማሚ ከሆኑም ከጎናቸው መሆን የግድ ነው። ከእርሱ ጋር መቆየት እንደምትችይ ማሰብ የአዕምሮ ሰላም ይሰጣል። ወደ ሥራሽ መመለስም ትችያለሽ” ትላለች።

ምንም እንኳን ቡልጋሪያ ለጋስ የሆነ ፖሊሲ ቢኖራትም፣ እንደ አውሮፓውያኑ በ2050 ከሃያ በመቶ በላይ የሕዝቧ መጠን እንደሚቀንስ የተባበሩት መንግሥታት ትንበያ አመልክቷል።

በቡልጋሪያ የእናቶች የወሊድ ፈቃድ ረጅም ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ አገሪቷ ለወላጆች ምቹ አይደለችም።

“ሌሎች በርካታ ችግሮች አሉ። በባለሙያ የታገዘ የሕጻናት እንክብካቤ አለመኖር፣ ዝቅተኛ ደመወዝ፣ የኑሮ ውድነት፣ የቤት ዋጋ መወደድ፣ በሴቶች እና በወንዶች መካከል ያለው የክፍያ ልዩነት ከባድ ናቸው” ትላለች ግራማቲኮቫ።

ለወጣት እናቶች ዳጎስ ያለ ክፍያ

ቡልጋሪያ ዝቅተኛ የወሊድ መጠንን ለማሳደግ ረጅም የወሊድ ፈቃድ ስትሰጥ፣ ደቡብ ኮሪያ ደግሞ ሌላ መፍትሔ እየሞከረች ነው።

ገንዘብ መስጠት ለእርሷ የተሻለ ሆኖ አግኝተዋለች።

በደቡብ ኮሪያ ከዚህ ዓመት ጀምሮ አዲስ የተወለደ ልጅ ያለው ማንኛውም ቤተሰብ በወር ወደ 745 ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መውሰድ ይችላል።

ምክንያቱ ቀላል ነው።

እንደ አገሪቱ ብሔራዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ከሆነ በሁለት ዓመት ውስጥ ከአምስት ሰዎች አንዳቸው ከ65 ዓመት በላይ እንደሚሆናቸው ይገመታል።

በመሆኑም ልክ እንደ ሌሎች አገራት ሁሉ ደቡብ ኮሪያም የጤና እና የማኅበራዊ ሥርዓቷ ለአረጋውያን ምቹ መሆኑን ለማረጋገጥ እየጣረች ነው።

ነገር ግን ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የአገሪቱ ዜጎች የወሊድ መጠን (ፈርቲሊቲ ሬት) ከዓለም ዝቅተኛ ሆኖ መመዝገቡ ችግሩን አግዝፎባታል።

ለዚህም ነው መንግሥት “የሕጻን ክፍያ” በሚል የሚሰጠውን ገንዘብ በሦስት እጥፍ ያሳደገው።

በዚህ ፖሊሲ መሠረትም ሕጻናቱ አንድ ዓመት እስከሚሆናቸው ድረስ ሙሉ ክፍያ የሚሰጥ ሲሆን፣ አንድ ዓመት ሲሞላቸው ደግሞ ክፍያው በግማሽ ይቀንሳል። በዚህ መልኩም የሚሰጠው ክፍያ እየቀነሰ ይሄዳል።

ፖሊሲ አውጪዎቹ ክፍያው አገሪቷ እያለፈችበት ባለው የሥነ ሕዝብ ሁኔታ ላይ አስደናቂ ለውጥ ያመጣል ብለው ተስፋ አድርገዋል።

ይሁን እንጂ በኮሪያ የጤና እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ተቋም አጥኚ የሆኑት ሊ ሳንግ ሪም “በ20 ዓመታት ውስጥ ደቡብ ኮሪያ ከጃፓን በመብለጥ የዓለማችን የአረጋውያን አገር ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል” ሲሉ ባለፈው ዓመት ለቢቢሲ ኮሪያ ተናግረዋል።

ሠራተኛ ሮቦቶች

ጃፓን አረጋውያን ሕዝቦቿን ለማገዝ ፊቷን ወደ ሮቦቶች አዙራለች።

በእርግጥ እጅግ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማምረት እና በመጠቀም ለምትታወቀው ጃፓን ይህ አስገራሚ አይደለም።

እንደ የዓለም ባንክ ከሆነ በአገሪቷ ያለው የአረጋውያን ሠራተኛ ኃይል የጃፓንን ምጣኔ ሃብት እንዲያሽቆለቁል አድርጎታል።

በመሆኑም ከሕጻናት ጋር ተያይዞ ያላትን ፖሊሲዎች ለመተግበር የምታውለውን በጀት በእጥፍ ለማሳደግ እና አዳዲስ የመንግሥት ኤጀንሲዎችን ለማቋቋም አቅዳለች።

የዜጎቿን የአመሻሽ ዕድሜ ሕይወታቸውን ለማቅለል በማሰብም ሮቦቶች ላይ መዋዕለ ነዋይዋን እያፈሰሰች ነው።

የጃፓን ድርጅቶች በመንግሥት ድጋፍ አረጋውያንን የሚንከባከቡ ሠራተኞችን ለመርዳት የሚችሉ ውሾችን ጨምሮ ራሳቸው እንክብካቤ የሚያደርጉ ሮቦቶችን እየሰሩ ነው።

ሮቦቶቹ የተሰሩት ተጧሪ አዛውንቶችን መከታተል፣ ማነጋገር እና በእንቅስቃሴ ወቅት መርዳት እንዲችሉ ተደርገው ነው።

የአንድ ልጅ (ዋን ቻይልድ) ፖሊሲ መቀልበስ

የቻይና መንግሥት እንደ አውሮፓውያኑ 2016 አነጋጋሪ የነበረውን የአንድ ልጅ (ዋን ቻይልድ) ፖሊሲን ካነሳ በኋላ የግብር እፎይታ እና የተሻለ የሕጻናት ጤና እንክብካቤ እየሰጠ ሲሆን፣ የተጋቡ ጥንዶችም ሁለት ልጆችን እንዲወልዱ ፈቅዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዢ ጂንፒንግ ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ላይ የወሊድ መጠንን ማሳደግ ቅድሚያ የሚሰጡት ተግባር እንደሆነ አሳውቀዋል። ይሁን እንጂ የወሊድ መጠንን ከመቀነስ ይልቅ መጨመር ፈታኝ ሆኗል።

በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት የቻይና የሕዝብ ብዛት በስልሳ ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀንሷል። ከአንድ ሺህ ሰዎች 6.77 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው የሚወልዱት።

ዢ ጂንፒንግ መንግሥታቸው እየጨመረ ለመጣው የአረጋውያን መብዛት ምላሽ ለመስጠት “ብሔራዊ ስትራቴጂ” እንደሚከተሉ ቃል ገብተዋል።

ይሁን እንጂ መጪው ጊዜ ብሩህ አይመስልም።

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ትንበያ ከሆነ በመቶ ዓመት ጊዜ ውስጥ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 64 የሚሆኑ ቻይናውያን ቁጥር ከ60 በመቶ በላይ እንደሚቀንስ አመልክቷል።

በዕድሜ የገፋ ሠራተኛ ኃይል መበራከትም የቻይና ግዙፍ ምጣኔ ሃብት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል የሚል ስጋት አለ።

ይህም በመላው ዓለም ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል።

የሕይወት ዘመን ትምህርት

በፍጥነት የአረጋውያን ዜጎች ቁጥር ከጨመረባት የዓለማችን አገራት መካከል ሌላኛዋ ሲንጋፖር ናት።

በመሆኑም በዕድሜ የገፋውን የሠራተኛ ኃይል ለማገዝ መንግሥት የሕይወት ዘመን ትምህርት ላይ እየሰራ ነው።

ይህም አረጋውያንን በሥራም፣ በአዕምሮም፣ በአካልም፣ በማኅበራዊ ግንኙነትም ንቁ አድርጎ ለማቆየት ያስችላል ተብሏል።

እንደ የዓለም ባንክ ከሆነ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ለቀድሞ ተመራቂ ተማሪዎቻቸው ከተመረቁበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 20 ዓመታት ድረስ የተመረጡ እና ከኢንደስትሪ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ትምህርቶች ይሰጣሉ።

ሌሎች ደግሞ ከአዳዲስ ክህሎቶች ጋር ለተያያዙ ትምህርቶች ድጋፍ ያደርጋሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የሲንጋፖር ዜጎች የጡረታ ሃብታቸውን ሊያሟጥጥ የሚችሉ አደጋዎች በመቀነስ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ወርሃዊ ክፍያ እንዲያገኙ የሚያስችላቸውን፣ ብሔራዊ የረዥም ጊዜ የመድን ዋስትና ፕሮግራምን መጠቀም ይችላሉ።

ይህ የመድን ዋስትና የሚደገፈው ከግለሰቦች በየወሩ ከሚቆረጥ ገንዘብ ሲሆን፣ ይህንን የሚጠቀም ግለሰብ ጡረታ በሚወጣበት ጊዜ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ በየወሩ ክፍያ ያገኛል።

መንግሥትም “ምንም ያህል ዓመት ኑሩ፣ በፍጹም እንዳትጨነቁ” ይላል።