ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በርካታ ሴቶችን የሚያሰቃየውን የወር አበባ ህመም የሚያስታግሰው አዲሱ ቴክኖሎጂ
ለበርካታ ሴቶች በየወሩ ያለው ከሦስት እስከ አምስት የሚደርሱ የወር አበባ ቀናት የስቃይ እና የመከራ የሚባሉ ናቸው።
የማያስቀምጥ እና የማያስተኛ ሆድ ቁርጠት፣ ማቅለሽለሽ፣ ራስ ህመም፣ የጀርባ ህመም. . . ሌላም ሌላም።
ዓለም የወር አበባ ህመምን ከባድነት ለመረዳት ዘመናትን ፈጅቶበታል።
የህክምና ባለሙያዎች በመጨረሻም የወር አበባ ቁርጠትን ከልብ ድካም ህመም ጋር ሊወዳደር የሚችል እንደሆነም በቅርቡ ይፋ አድርገዋል።
የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች የወር አበባ ህመም እንደ የልብ ድካም የከፋ ነው ብለውታል።
ለዚህም ነው አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች እና ትምህርት ቤቶች ለሴቶች የወር አበባ እረፍት መስጠት የጀመሩት።
በርካታ ተቋማት የሴቶችን ህመም ባለመረዳት በርካቶች ይህንን ህመም ለማቅለል ትኩስ መጠጦችን መጠጣት፣ ሙቅ ውሃ ሆድ ላይ መያዝ፣ መድኃኒት መውሰድ እና ሌሎች ማስታገሻዎችን ይጠቀማሉ።
በቅርቡ ግን ይህንን ህመም ያስታግሳል የተባለች አዲስ ቴክኖሎጂ ይፋ ሆኗል ብሏል።
የ33 ዓመቷ ፓውላ ፊሸር የወር አበባ ህመምን ለማስታገስ ስለሚረዳው በሰውነት ላይ ስለሚጠለቀው የልብስ ቴክኖሎጂ ለመጀመሪያ ጊዜ ስታነብ “ለመሞከር በጣም ጓጓች።”
እንደ በርካታ ሴቶች የወር አበባዋ በምታይበት ወቅት ከፍተኛ ህመም ያጋጥማታል። በየወሩም ህመም ማስታገሻ የምትወስድ ሲሆን፣ እነዚህ መድኃኒቶች ለጥቂት ሰዓታት ብቻ ከመሥራታቸው ጋር ተያይዞ ሌሎች አማራጭ መፍትሄዎችን ትፈልግ ነበር።
“የወር አበባዬ በሚመጣባቸው ቀናት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሰቃይ ህመም ይሰማኛል። ከሶፋዬ ተነስቼ ሥራዬን እንኳን መሥራት አልችልም” በማለት በሃንጋሪዋ መዲና ቡዳፔስት የምትኖረው ፓውላ ትናገራለች።
“ይህ ሁሉ ነገሬ ላይ ተጽእኖ ያሳርፋል፤ የሚሰማኝ ስሜት፣ የሥራ ተነሳሽነቴ፣ ሥራዬን የመከወን ችሎታዬ ሁሉ ያውከዋል” ትላለች።
ከሁለት ዓመት በፊት፣ የወር አበባ ህመምን ለመቀነስ የሚረዳ ቴክኖሎጂን በተመለከተ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አየች።
በሃንጋሪ የሚገኘው አልፋ ፌምቴክ የተሰኘው የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ነበር ሴቶች የሚለብሱት መተግበሪያ የሠራው፤ በወቅቱም ማበልጸግ እና ሙከራ ላይ ስለነበር በጎ ፈቃደኞች እየፈለገ ነበር።
አመልካቾች የወር አበባ ዑደታቸውን በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን መሙላት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ከዚያም የሴቶች ጤና ዶክተር ተስማሚ ተሳታፊዎችን መረጡ። ፓውላ ልብሱን ለመሞከር እና በሙከራው ላይ ለመሳተፍ ከተመረጡ በጎ ፈቃደኞች አንዷ ነበረች።
የሚለበሰው ማሽን አርቴምስ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ በዚህ ዓመትም በዩናይትድ ኪንግደም እና በአውሮፓ ኅብረት ገበያዎች ላይ ይቀርባል። ማሽኑ እንደ ልብስ የሚለበስ እና የሙቀት ማስተላለፊያዎች እንዲሁም የሰውነት ነርቭን የሚያነቃቃ ፈሳሽ (ጄል) አለው።
ማሽኑ የተሰራበት የተወሰነው ክፍል አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች በወሊድ ጊዜ የሚጠቀሙባቸው ሲሆን የኤሌክትሪክ ምትም ወደ ሰውነት ይለቃሉ። እነዚህም የህመም ምልክቶች ወደ አዕምሮ እንዳይደርሱ ይከላከላሉ ተብሏል።
በልብስ ማሽኑ ላይ የተገጠሙት የሙቀት ማስተለላፊያዎች ማህጸን እና በዙሪያው ያሉት ጡንቻዎችን ያፍታታሉ። ልብሱ በብሉቱዝ ከተጠቃሚዎች ዘመናዊ ተንቀሳቀሽ ስልክ ላይ ካለ መተግበሪያ ጋር ይገናኛል፤ የሙቀት እና የኤሌክትሪክ ምቱንም በስልክ ማስተካከል ይቻላል።
ፓውላ በወር አበባዋ ወቅት ይህንን ቴክኖሎጂ ስትለብስም ፍጹም የተለየ ስሜት ነበር የተሰማት፤ ትንሽ የሚባል ወይም ምንም አይነት ህመም ሳይሰማት ቀረ። አርቴሚስ ልብስ ከበግ ፀጉር እና አርቲፊሻል ከሆነ ክር ጋር ተዋህዶ የተሠራ ሲሆን “ምቹ እና ለመልበስም ጥሩ ነው” ብላለች።
ፓውላ አጋጥሞኛል የምትለው ብቸኛ የጎንዮሸ ጉዳት የወር አበባዋ ከወትሮው የበለጠ መብዛቱ ነው።
“በጡንቻ አፍታች ውጤቶች ምክንያት እንደሆነ እገምታለሁ” ትላለች።
አርቴሚስ፣ የሚለበሱ በተለይም በወር አበባ ጤና ላይ ያተኮሩ የቴክኖሎጂ ልብሶች ላይ የዶክትሬት ዲግሪ ያላት የአልፋ ፌምቴክ ኩባንያ መሥራች አና ዘሶፊያ ኮርሞስ የፈጠራ ውጤት ነው።
ሌላኛው የኩባንያው መሥራች እና አጋሯ ዶራ ፔልዘር የማርኬቲንግ ባለሙያ ናት።
“350 ሴቶችን በወር አበባቸው ወቅት ስለሚያጋጥማቸው ሁኔታዎችን ያነጋገርን ሲሆን፣ በዚህም ለተጠቃሚዎች ምቹ የሆነ ምርት ለመሥራት ነው” ስትል ዶራ ገልጻለች።
በ240 ዶላር የሚሸጠው የወር አበባ ህመም ማስታገሻ ልብስ፣ ከህክምና መሳሪያ ይልቅ አዲስ ፋሽን ቲሸርትም እንዲመስል እንዳቀዱም ታስረዳለች።
በደብሊን ነዋሪ የሆነችው ሬቤካ ፓውደርሊ ከወር አበባ ህመም ስቃይ በተጨማሪ ኢንዶሜትሪዮሲስ የሚባል የጤና ችግርም አለባት።
በዓለማችን ካሉ አስር ሴቶች አንዷን የሚያጠቃው ይህ ህመም በማህጸን መኖር ያለበት ሕዋስ ጋር የሚመሳሳል ሕዋስ በሌላ የሰውነት ክፍል ውስጥ ለምሳሌ በፊኛ ዙሪያ ሲበቅል ነው። እነዚህ ሕዋሳት ቁስለት እና ጠባሳ የሚፈጥሩ ሲሆን የከፋ ህመምም ያስከትላሉ።
ሬቤካ ህመሟን ለማስታገስ የሞቀ ውሃ በሆዷ ላይ ትይዝ ነበር። የ28 ዓመቷ ወጣት ከቤት በምሽት ስትወጣም የሞቀ ውሃ ሆዷ ላይ ይዛ በመራመዷም በርካቶች በእንግዳ መልኩ ተመልክተዋታል።
ነገር ግን ከመስከረም ጀምሮ የሞቀ ውሃውን ትታ ሌላ በሰውነት ላይ የሚለጠፍ ቴክኖሎጂን ማጥለቅ ጀምራለች።
ሌላው የወር አበባ ህመም ማስታገሻ ምዮቪ ተብሎ ይጠራል። ይህ ማሽን በተጠቃሚዎች ከእምብርት በታች ወይም በታችኛው ጀርባ ላይ የሚለጥፉት ነው። የቢራቢሮ ቅርጽ ያለው ይህ የሚለጠፍ ማሽን ቻርጅ ማድረጊያና መቆጣጠሪያም አለው። ለ20 እና ሰላሳ ጊዜ መጠቀምም ይቻላል።
“ልክ ይህንን ማሽን ሰውነቴ ላይ ስለጥፈው ወዲያውኑ ህመሙ ይጠፋል። በኢንዶሜትሪዮሲስ ምክንያት የሚሰማኝን የሚወጋ ህመም ሙሉ በሙሉ ባያጠፋውም፣ በተወሰነ መልኩ ይቀንሰዋል። በተለይም የወር አበባዬ በሚመጣበት ወቅት የሚያጋጥመኝ ከማያቋርጥ ሆድ ቁርጠት እፎይታ አግኝቻለሁ” ትላለች።
ምዮቪ ገበያ ላይ የቀረበችው ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ነው። ምርቱን የሠራው በማንችስተር ተቀማጭነቱን ያደረገው ምዮቪ የተሰኘ የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ኩባንያ ነው።
የጽንስ እና የማህጸን ሐኪምና የሞርተን የህክምና እርዳታ ሰጪ መሥራች ዶክተር ሞርተን ማሽኖቹ እንዴት እንደሚሰሩ ሲያስረዱ “ህመሙ ባለበት በአከርካሪ በኩል ማነቃቂያ በማድረጉ ህመሙ ወደ አዕምሮ እንዳይደርስ ያደርጉታል። ሙቀትም ተመሳሳይ ነገር ሊያደርግ ይችላል” ይላሉ።
ሆኖም የከፋ የወር አበባ ህመም ያለባቸውም ይሁኑ በሌላ የማህጸን ህመም የሚሰቃዩ ሴቶች በመጀመሪያ ወደ ህክምና ተቋማት ሄደው መመርመር እንዳለባቸው ያሳስባሉ።
የነርቭ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ስቲቭ አልደር በበኩላቸው ጥናቶችን ዋቢ አድርገው እነዚህ ማሽኖች ህመምን በመቀነስ ረገድ ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸው፣ በተደጋጋሚ መጠቀም ግን ችግሮችን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
የምዮቪ ኩባንያ ዶክተር ሃምዲ በበኩላቸው እነዚህ መሳሪያዎችን በተደጋጋሚ መጠቀም የጎንዮሽ ጉዳት እንደሌለው አጥብቀው ይናገራሉ።
የቡዳፔስቷ ፓውላ አርቴሚስ የወር አበባ ህመም ማስታገሻ ልብስ ገበያ ላይ የሚቀርብበትን ወቅት በጉጉት አየጠበቀች ትገኛለች።