ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጋርዲዮላ አሁን ዋንጫው በእጃችን ነው አሉ
የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ቡድናቸው የሊጉ መሪ የሆነውን አርሰናልን አሳማኝ በሆነ ጨዋታ እና ውጤት ካሸነፈ በኋላ አሁን ዋንጫው በእጃችን ነው አሉ።
ፔፕ ጋርዲዮላ ቡድናቸው “ከማሸነፍ ውጪ ሌላ አማራጭ በማይኖርበት ወቅት" ማሸነፍ የሚችል ቡድን መሆኑን አረጋግጧል ብለዋል።
አርሰናል አሁንም የሊጉ መሪ ቢሆንም ሲቲ ሁለት ቀሪ ጨዋታ እያለው ከአርሰናል ያለው የነጥብ ልዩነት 2 ብቻ ነው።
ሲቲ ሁለቱን ቀሪ ጨዋታዎቹን ሲያሸንፍ አርሰናልን በ3 ነጥብ በልጦ የሊጉ መሪነትን መያዝ ይችላል።
“ትኩረታችንን ማጣት የለብንም። አሁን በእጃችን ያለው [ዋንጫው] ነው” ብለዋል ጋርዲዮላ፣ አርሰናል ላይ ከተቀዳጁት ድል በኋላ በሰጡት አስተያየት።
“ቀጣይ ሦስት ጨዋታዎች ማድረግ የምንፈልገውን ማሳካት የምንችል መሆኑን ይወስናሉ። እውነታው አሁንም ከአርሰናል በታች ነን። ቀላል አይሆንም፤ ግን አንድ በአንድ፤ ጨዋታ በጨዋታ ምን እንደሚሆን እናያለን። በእጃችን ሲሆን እድሉን መጠቀም አለብን” ብለዋል።
ትናንት ምሽት በኢትሃድ ስታዲየም አርሰናልን 4-1 ያሸነፈው ሲቲ የፊታችን እሑድ ወደ ፉልሃም የሚያቀና ሲሆን ከዛ በኋላ ሰማያዊዎቹ በሜዳቸው ዌስት ሃም እና ሊድስን ያስተናግዳሉ።
አርሰናል ከአራት ሳምንታት በፊት ከሲቲ የነበረው ልዩነት 8 ነጥብ ነበር።
መድፈኞቹ በሦስተ ተከታታይ ጨዋታ ማለትም ከሊቨርፑል፣ ዌስት ሃም እና ሳውዝሃምፕተን አቻ መለያየታቸው ልዩነታቸውን ማስጠበቅ የሚችሉበትን ወሳኝ ነጥቦች አጥተዋል።
ሲቲ የትናንት ምሽቱን ጨዋታ ማሸነፉን ተከትሎ የዘንድሮውን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ የማንሳት እድሉ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
የጋርዲዮላ ቡድን ከፕሪሚየር ሊጉ በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ዋንጫዎችን የማንሳት እድል አለው።
በቻምፒየንስ ሊጉ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ያለፈ ሲሆን ለኤፍኤ ዋንጫ ደግሞ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ለፍጻሜ ደርሷል።
የቀድሞ የባርሴሎና እና የባየርን ሙኒክ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ የቡድን አባላቶቻቸው እያንዳንዱን ጨዋታ ማሸነፍ እንደሚችሉ አምነው ወደ ሜዳ እየገቡ እንደሆነ ተናግረዋል።
“ከማሸነፍ ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ አስቦ ወደ ሜጋ መግባት ጥሩ የአእምሮ ዝግጅት ነው። ተጫዋቾቹ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ አስመስክረዋል” ብለዋል።
በትናንት ምሽቱ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ኮከብ ሆኖ ያመሸው የሲቲ አምበል ኬቪን ደ ብረወይና ሲቲ ዋንጫ የማንሳት ሰፊ እድል እንዳለው ቢገለጽም በሂሳባዊ ስሌት እስኪረጋገጥ ድረስ ከዋንጫው ትኩረታቸውን አናነሳም ሲል ተናግሯል።