የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ግምት፡ አርሰናል ከቶተንሃም - ማን ያሸንፋል? የሌሎች ጨዋታዎች ግምትስ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቶተንሃም በአርሰናል ሜዳ ተጫውቶ ካለፉት 17 ግጥሚያዎች 1 ብቻ ነው ያሸነፈው። ነገር ግን ይህ እሑድ በሚካሄደው የሰሜን ለንደን ደርቢ ሊቀየር ይችላል።
ስድስተኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ሲቀጥል አርሰናል ከቶተንሃምን ጨምሮ ሌሎች ተጠባቂ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ሱቶን እንደተለመደው የጨዋታዎቹን ውጤት ግምት እንዲህ አስቀምጧል።
ቅዳሜ
ክሪስታል ፓላስ ከፉልሀም
ሁለቱ ቡድኖች በያዝነው የውድድር ዓመት ተመሳሳይ አጀማመር አላቸው። ሁለት ጊዜ አሸንፈዋል፤ ሁለቴ ተሸንፈዋል፤ አንድ ጊዜ አቻ ወጥተዋል።
ለዚህ ነው ይህ ጨዋታ አቻ አቻ ይሸታል የምለው ይላል ሱቶን።
ባለፈው ሳምንት በሕመም ምክንያት ጨዋታ ያመለጣቸው የክሪስታል ፓላሱ ጉምቱ አሠልጣኝ ሮይ ሆጅሰን ተሽሏቸው ይመለሱ ይሆናል።
ነገር ግን የዚህ ጨዋታ ግምቴ አንድ አቻ ነው ሲል ሐሳቡን ይሰጣል።
ግምት፡ 1 - 1

ሉቶን ከዎልቭስ
ሉቶን የመጀመሪያ ድላቸውን ለማግኘት በጣም ጓጉተዋል። አንድ ነጥብም ቢሆን ትልቅ ነገር ነው።
ዎልቭስ ደግሞ የውድድር ዘመኑን የጀመሩበት መንገድ መልካም የሚባል አይደለም። ባለፈው ሳምንት ቅድሚያ ጎል አግብተው በሊቨርፑል መረታታቸው ዕድል-ቢስ መሆናቸውን ያሳያል።
ምንም እንኳ ሉቶን ከዚህ ጨዋታ አንድ ነገር ለማግኘት የሚፋለሙ ቢሆንም ዎልቭስ በጠባብ ጎል ያሸንፋል የሚል እምነት አለኝ ይላል ሱቶን።
ግምት፡ 0 - 1

ማንቸስተር ሲቲ ከኖቲንግሃም ፎሬስት
የማንቸስተር ሲቲ የቡድን ስብስብ በጉዳት ምክንያት ቢሳሳም ፔፕ ጉዋርዲዮላ የጨዋታው ስልታቸውን ይቀይራሉ ብዬ አላምንም ባይ ነው ሱቶን።
ሲቲ በቅርቡ ያስፈረመው ቤልጂየማዊው ጄሬሚ ዶኩ ባለፈው ሳምንት ዌስት ሃም ላይ ጎል ከማስቆጠሩም በላይ ለቡድኑ ትልቅ አስተዋፅዖ እያደረገ ነው።
ሲቲ ከዌስት ሃምና በቻምፒዮንስ ሊግ ከሬድ ስታር ቤልግሬድ ጋር በነበረው ጨዋታ በጎል ቢመራም ድል ከማጣጣም አላገደውም።
ሱቶን እንደሚለው ሲቲ የጎል ዕድል የመፍጠር ችግር ያለበት ቡድን አለመሆኑ ጠቅሞታል።
ኖቲንግሃም ፎረስት ባለፈው የውድድር ዘመን ከሜዳቸው ውጭ በጣም ደካም ነበሩ። ዘንድሮ ግን ቼልሲን በሜዳው ሲረቱ፤ ከአርሰናልና ዩናይትድ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ቀላል ተጋጣሚ አልነበሩም።
ነገር ግን በሲቲ ሜዳ ይህ ነው የሚባል ውጤት ያመጣሉ ብዬ አልገምትም የሚለው ሱቶን ግምቱን አስቀምጧል።
ግምት፡ 4 - 0

ብሬንትፈርድ ከኤቨርተን
ይህ ለኤቨርተን በጣም ትልቅ ጨዋታ ነው። ከባድም ነው።
የሾን ዳይሽ ቡድን ባለፈው ሳምንት አርሰናል ላይ ቡጢ ማሳረፍ አልቻለም። ወደ ብሬንትፈርድ ሄደው የሆነ ነገር ማድረግ አለባቸው። ቢሆንም በመልሶ ማጥቃት አደገኛ የሆነውን ቡድን መፍራት አለባቸው።
ንቦቹ [ብሬንትፈርድ] ባለፈው ሳምንት ወደ ኒውካስል አቅንተው ዕድለ-ቢስ በሚያስብል መንገድ በፍፁም ቅጣት ምት ተሸንፈው ተመልሰዋል።
ይህ ጨዋታ ብሬንትፈርድ ከሽንፈታቸው የሚያገግሙበት ይሆናል የሚል እምነት አለኝ ይላል ሱቶን።
ግምት፡ 2 - 0

በርንሊ ከማንቸስተር ዩናይትድ
ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ለማንቸስተር ዩናይትድ ግድ ይለዋል። በተለይ ደግሞ ጫና እየበረታባቸው ያሉት አሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ከትችት ለመውጣት ወደ ውጤት መምጣት አለባቸው።
ዩናይትድ በያዝነው የውድድር ዓመት የሚጠብቅባቸውን ያክል ጨዋታም ሆነ ውጤት እያሳዩን አይደለም።
ዘንድሮ ለዩናይት ሁሉ ነገር ተቃራኒ የሆነ ይመስላል። ጥሩ ጨዋታ አሳይተው ይሸነፋሉ። ውጤቱ አይገባቸውም በተባለ ጨዋታ ደግሞ ያሸንፋሉ።
ወደ ተርፍ ሞር አቅንተው ሽንፈት ማስተናገድ ግን የሚታሰብ አይደለም። እንደውም ከማሸነፍ ውጭ አማራጭ ያላቸው አይመስለኝም።
በርንሊ እስካሁን ድል አልቀናቸውም። ባለፈው ሳምንት ወደ ኖቲንሀም አቅንተው አንድ ነጥብ ይዘው ተመልሰዋል።
ግምት፡ 1 - 2
እሑድ

አርሰናል ከቶተንሃም
በዚህ ጨዋታ ጎል የምናይ ይመስለኛል ይላል ሱቶን። በርካታ ጎል።
ይህ ጨዋታ ሩጫ የበዛበት እንደሚሆን እሙን ነው። የቶተንሃም አሠልጣኝ ፖስቴኮግሉ ወደ አርሰናል ሜዳ አቅንተው ቡጢ እንደሚገጥሙ አልጠራጠርም የሚለው ሱቶን ስፐርስ ለመድፈኞቹ ፈተና እንደሚሆኑ ይገምታል።
ነገር ግን አርሰናልም ቢሆን የስፐርስም የኋላ መስመር ከመፈተን እንደማይቦዝኑ ይናገራል።
የቶተንሃሙ አሠልጣኝ ይህ የመጀመሪያ ፈተናቸው ይሆናል፤ በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ ከሊቨርፑል ይጫወታሉ።
አሠልጣኙ ወደ አርሰናል ሜዳ ሄድው ውጤት ይዘው ቢመለሱ ትልቅ ዜና ቢሆንም ይህን ማድረግ ይከብዳቸዋል ይላል ሱቶን።
ግምት፡ 3 - 2

ብራይተን ከቦርንመዝ
በያዝነው የውድድር ዘመን በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ብራይተንን መርታት የቻሉት ዌስት ሀም ብቻ ናቸው። ብራይተን ተጭነው መጫወት ይመርጣሉ።
የዚህ ጨዋታ ውጤት የሚወሰነው በቦርንመዝ አሠልጣኝ አንዶኒ ኢራኦላ ድፍረት ላይ ነው። ቦርንመዝ በድፍረት ወደ ብራይተን ጎል አቅንቶ ጎል ለማስቆጠር የሚጥር ከሆነ አደጋ ላይ ይወድቃል።
ብራይተን ሐሙስ ምሽት በአውሮፓ ሊግ መጫወታቸው ለቦርንመዝ መልካም ነገር ሊሆን ይችላል።
የሮቤርቶ ዲ ዘርቢ ቡድን አንድ እና አንድ ዓይነት አጨዋወት ነው የሚያውቀው። በጣም ማራኪ የሆነ አጨዋወት።
ግምት፡ 3 - 1

ቼልሲ ከአስተን ቪላ
አስተን ቪላ ባለፈው የውድድር ዘመን ያሳዩንን ዓይነት ጨዋታ እያሳዩን አይደለም። ነገር ግን አሁንም ቢሆንም ጥሩ አቋም ላይ ናቸው።
ባለፈው ሳምንት ከኋላ ተነስተው ክሪስታል ፓላስን መርታት ችለዋል። ከቼልሲ በተቃራኒ ኳስና መረብ ማገናኘት የሚከብዳቸው አይደሉም።
በያዝነው የውድድር ዘመን ቼልሲ ውጤት ይቀለብሳል እያልኩ ስገምት ነበር። ተሳስቻለሁ። ይህን ስህተት መድገም አልፈልግም ይላል ሱቶን።
ቪላ ቼልሲን ቢረታ አልገረምም የሚለው ሱቶን ጨዋታው አቻ ይሆናል የሚል ግምት አለው።
ግምት፡ 1 - 1

ሊቨርፑል ከዌስት ሃም
የዴቪድ ሞየስን የመከላከል ዲሲፕሊንን እጅግ እወደዋለሁ የሚለው ሱቶን አሠልጣኙ የቡድኑን ጠንካራ ጎን የሚያውቁ እንደሆኑ ይጠቅሳል።
መዶሻዎቹ ወደ ሊቨርፑል ሜዳ አቅንተው የዩርገን ክሎፕን ቡድን እንደሚፈትኑ የሚገምተው ሱቶን በመልሶ ማጥቃት አደጋ ሊሆኑ እንደሚችሉም አይክድም።
የዚህ ጨዋታ ውጤት የሚወሰነው በሊቨርፑል አጥቂዎች ላይ ነው። በርካታ አደገኛ አጥቂዎች አሏቸው።
ባለፈው ሳምንት ከመመራት ተነስቶ ዎልቭስን መርታት የቻለው ሊቨርፑል በዚህኛውም ጨዋታ ውጤት እንደሚቀናው የሱቶን ግምት ነው
ግምት፡ 2 - 0

ሼፊልድ ዩናይትድ ከኒውካስል
ሼፊልድ ባለፈው ሳምንት ከቶተንሃም በነበራቸው ጨዋታ እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ታግለዋል። ከማንቸስተር ሲቲም ጋር እንዲሁ ቢታገሉም በሁለቱም ጨዋታው ምንም ነጥብ ሳይዙ ወጠተዋል።
አሠልጣኝ ፖል ሄኪንግቦተም ከስፐርስ ጋር በነበረው ጨዋታ ጭማሪ ደቂቃ ከመጠን በላይ ነበር ሲሉ አማረዋል።
ኒውካስል በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ በሳምንቱ አጋማሽ ከተጫወቱ በኋላ ይህን ጨዋታው እንዴት ይወጡታል የሚለውን መመልከት ጉጉት ይፈጥራል።
ማክሰኞ ከኤሲ ሚላን የተጋጠሙት የኤዲ ሃው ልጆች አንድ ነጥብ ይዘው መምጣታቸው ዕድለኛ ናቸው የሚያስብል ነው።
ኒውካስል በያዝነው የውድድር ዘመን የአምናው ቁመናቸውን ያገኙ ባይመስሉም መመላሳቸው አይቀርም።
ቡድኑ ጥልቅ ስለሆነ አሠልጣኙ ተጫዋቾችን ቀያይረው ወደ ሼፊልድ ሜዳ በማቅናት በድል ይመለሳሉ ይላል ሱቶን።
ግምት፡ 0 - 1














