በሞስኮ የተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች አየር ማረፊያ እንዲዘጋ አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዩክሬን በሩሲያ መዲና ሞስኮ የፈጸመቻቸው የድሮን ጥቃቶች በመዲናዋ በሚገኙ ሕንጻናዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን እና አንድ አየር ማረፊያ ለአጭር ጊዜ እንዲዘጋ ማድረጉን ሩሲያ አስታወቀች።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ጥቃቱን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ “የሽብር ሙከራው ተቀልብሷል” ብሏል።
መከላከያ ሚኒስቴሩ ከሞስኮ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ኦዲንትሶቮ ከተማ አንድ ድሮን ተመትቶ መውደቁን እና ሌሎች ሁለት ድሮኖች አየር ላይ ከተመቱ በኋላ ሕንጻ ላይ ወድቀው ንብረት ማውደማቸውን አስታውቋል።
የሩሲያ መንግሥታዊ ዜና ወኪል ታስ በክስተቱ አንድ ሰው መጎዳቱን ገልጿል። ከስፍራው የወጡ ምስሎች በርካታ የሕንጻዎች መስኮቶች ተጎድተው እና ስብርባሪያቸው መሬት ላይ ረግፈው አሳይተዋል።
ዩክሬን ፈጽመዋላቸው ስለተባለው የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት የኪዬቭ ባለስልጣናት እስካሁን ያሉት ነገር የለም። ከዚህ ቀደምም በሩስያ ውስጥ ስለሚፈጸሙ ጥቃቶች የዩክሬን ባለስልጣናት ማረጋገጫ አይሰጡም።
አንድ የዓይን እማኝ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ስትናገር፤ “ፍንዳታ ሰማን። ከባድ ድምጽ ነበር። ከዛ ከባድ ጭስ ነበር ምንም ማየት አይቻልም ነበር። ከላይ ደግሞ እሳት ይታይ ነበር” ብላለች።
በድሮን ጥቃቱ ምክንያት ከሞስኮ መሃል ከተማ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 28 ኪሎ ሜትር ላይ ርቆ የሚገኘው ቫኑኮቮ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ስራውን እንዲያቆም ተደርጎ ነበር።
ከአየር ማረፊያው የሚነሱ አውሮፕላኖች እንዲዘገዩ የተደረጉ ሲሆን ወደ አየር ማረፊያው እየበረሩ የነበሩ አውሮፕላኖች ደግሞ መዳረሻቸውን ወደ ሌሎች አየር ማረፊያዎች እንዲቀይሩ ተደርገዋል።
ከዩክሬን ድንበር 500 ኪሎ ሜትሮችን ርቃ የምትገኘው ሞስኮ ከዩክሬን ይህ ነው የሚባል ጥቃት ተሰንዝሮባት አያውቅም።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ወራት ወዲህ ሩሲያ በመዲናዬ ሞስኮ ላይ ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃት እየተፈጸመ ነው ስትል ዩክሬንን ስትከስ ቆይታለች።
ከአንድ ሳምንት በፊት ዩክሬን ሞስኮ ከተማ ላይ በፈጸመችው የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት በሁለት ሕንጻዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ሩሲያ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።
ግንቦት ወር አጋማሽ ላይ ደግሞ የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሕይወትን ለማጥፋት ዩክሬን ክሬምሊን ላይ የድሮን ጥቃት ሙከራ አድርጋለች ተብሎ ነበር።












