የቴይለር ስዊፊት የሙዚቃ ድግስ ታዳሚዎች የመሬት መንቀጥቀጥ ፈጠሩ

አሜሪካዊቷ አቀንቃኝ ቴይለር ስዊፍት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አሜሪካዊቷ አቀንቃኝ ቴይለር ስዊፍት

በአሜሪካዊቷ አቀንቃኝ ቴይለር ስዊፍት የሙዚቃ ድግስ ላይ የተፈጠረው ንቅናቄ የመሬት መንቀጥቀጥ መፍጠሩን ባለሙያዎች ገለጹ።

ቴይለር ስዊፍት በአሜሪካዋ ዋሽንግተን ግዛት ሲያትል ከተማ ባደረገችው የሙዚቃ ድግስ በሬክተር ስኬል 2.3 የተመዘገበ አነስተኛ ርዕደ መሬት ተከስቷል።

የምድር ሳይንስ ባለሙያዋ ጃኪ ካፕላን-ኦርባች ይህ ትንሽ መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ የተፈጠረው በቴይለር ሰዊፍት አድናቂዎች ወይም በድምጽ ስርዓቱ ነው ብለዋል።

በሙዚቃ ድግሱ ላይ የተፈጠረው የመሬት ንዝረት ከዚህ ቀደም በሲያትል እአአ 2011 ላይ የተመዘገበውን ክብረ ወሰን ሰብሯል።

‘ቢስት ኩዌክ’ ተብሎ በሚጠረው ክስተት እአአ 2011 ላይ ሲያትል በነበረ የራግቢ ግጥሚያ ባለሜዳዎቹ ነጥብ ሲያስመዘግቡ አድናቂዎች ደስታቸውን ሲገልጹ 2 ነጥብ የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ፈጥረው ነበር።

በዌስተርን ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የምድር ሳይንስ ባለሙያዋ ዶ/ር ጃኪ ካፕላን-ኦርባች ለሲኤንኤን ሲናገሩ በስፖርታዊ ውድድሩ እና በሙዚቃ ድግሱ የተፈጠረው የመሬት መንቀጥቀጥ ልዩነት 0.3 ብቻ ቢሆንም በሙዚቃ ድግሱ የነበረው ጠንካራ ሰሜት ፈጥሯል ብለዋል።

“ንቅናቄው በእጥፍ ጠንካራ ነበር። ከሁለቱም ምሽቶች የተገኙ መረጃዎችን ስመለከት በፍጥነት የተረዳሁት ሁለቱም አመጣጣቸው ተመሳሳይ መሆናቸውን ነው” ብለዋል ባለሙያዋ።

ስዊፍት በሲያትል የሙዚቃ ድግሷን ያቀረበችው 144ሺህ ገደማ ከሚሆኑ አድናቂዎቿ ፊት ለፊት ለሁለት ተከታታይ ምሽቶች ነበር።

ከዝግጅቱ በኋላ ቴይለር ሰዊፍት በኢንስታግራም ገጿ “በሲያትል ያሳለፍኩት የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት እጅግ በጣም ከምወዳቸው ግዚያት መካከል ነበሩ። ለሁሉም ነገር አመሰግናለሁ” ብላለች።

ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ሁኔታ ስፖርታዊ ክንውኖች እና በሙዚቃ ድግሶች ላይ አስተኛ የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ ያጋጥም ነበር።

እአአ 2011 ላይ በኒው ዚላንድ በነበረ የሙዚቃ ድግስ ላይ የ50ሺህ ሰዎች ዝላይ የመሬት መንቀጥቀጥ አስመዝግቦ ነበር።

በእንግሊዝ ደግሞ እአአ 2016 ላይ የሌስተር ሲቲ ደጋፊዎች ቡድናቸው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቀናቃኛቸው ላይ ባስቆጠራት ጎል ደስታቸውን ሲገልጹ እንዲሁ መጠኑ አስተኛ የሆነ የመሬት ንዝረት ተመዝግቧል።