ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን የስዊድንን የኔቶ አባልነት ጥያቄን አገራቸው ልታግድ እንደምትችል ገለጹ
የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን አገራቸው ቱርክ፤ ስዊድን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እንድትቀላቀል እንደማትደግፍ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን የስዊድን ጎረቤት የሆነችው ፊንላንድ ግን ድርጅቱን እንድትቀላቅል ቱርክ ልትደግፍ እንደምትችል አመልክተዋል።
ኤርዶዋን ስዊድን ከኩርድ ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት ያላቸውን በርካታ ሰዎች አሳልፋ አልሰጠችም ሲሉ ይከሳሉ።
“ኔቶን መቀላቀል ከፈለጋችሁ፤ እነዚህን አሸባሪዎች ታስረክቡናላችሁ” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ኤርዶዋን ይህን አስተያየት የሰጡት ሁለቱን አገራት የኔቶ አባል አድርጎ ለመቀበል የተሰየመውን ንግግር ቱርክ ካገደች በኋላ ነው።
ሰዊድን እና ፊንላንድ የኔቶ አባል እንዳይሆኑ ቱርክ እንቅፋት መሆኗ ያበሳጫቸው የስዊድን ዜጎች ቁጣቸውን ለመግለጽ በስቶኮልም አደባባይ ወጥተው ነበር።
ፊንላንድ እና ስዊዲን በጦርነት ወቅት ከየትኛውም ወገን ጎን ላለመቆም እና ማንኛውንም ወታደራዊ ጥምረትን ያለመቀላቀል ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪክ ነበራቸው።
ይሁን እንጂ ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟ የደኅንነት ስጋት የፈጠረባቸው ሁለቱ አገራት፤ ኔቶን የመቀላቀል ጥያቄ ያቀረቡት ከወራት በፊት ነበር።
ሩሲያ ይህንን ውሳኔ አጥብቃ ተቃውማለች። ሞስኮ የምዕራባውያን የጦር ጥምረት የሆነው የኔቶ መስፋፋት ዩክሬንን ለመውረሯ እንደ አንድ ምክንያት አድርጋ አቅርባለች።
የሁለቱ አገራት የአባልነት ጥያቄ በሁሉም የኔቶ አባላት ድጋፍ ማግኘት የሚኖርበት ቢሆንም፣ ቱርክ እና ሃንጋሪ ግን የአገራቱን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል።
ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን በንግግራቸው ቱርክ “ምናልባት አሁን ላይ ፊንላንድን በተመለከተ የተለየ ምላሽ ልትሰጥ ትችላለች” ካሉ በኋላ የቱርክ ውሳኔ ለስዊድን ድንጋጤን የሚፈጥር እንደሚሆን ተናግረዋል።
ኤርዶዋን “ለስዊድን የ120 ሰዎች ዝርዝርን ሰጥተን እነዚህን አሸባሪዎች አሳልፈው እንዲሰጡ ነግረናቸዋል” ካሉ በኋላ፤ “አሳልፋችሁ የማትሰጡ ከሆነ አዝናለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።
ስዊድን ከፊንላንድ በላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኩርድ ዳያስፖራ አባላት አላት።
ቱርክ አሸባሪ ብላ ከሰየመችው የኩርዲስታን ሠራተኞች ፓርቲ (ፒኬኬ) ስዊድን እራሷን እንድታርቅ በተደጋጋሚ ስታጠነቅቅ ቆይታለች።
ሁለቱ የኖርዲክ አገራት ከቱርክ ጋር ያላቸው ግንኙነት መሻከር ከጀመረ ሰነባብቷል። እአአ 2019 ላይ ቱርክ በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት መሳተፍ መጀመሯን ተከትሎ ስዊድን እና ፊንላንድ ለቱርክ የጦር መሳሪያ ሽያጭ እንዳይደርግ እግድ ጥለዋል።
ኔቶ ማነው?
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት እአአ በ1949 አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይን ጨምሮ በ12 አገራት የተመሰረተ ነው።
ከአባል አገራት አንዳቸው ወታደራዊ ጥቃት ሲደርስባቸው ሌሎች ድጋፍ የሚያደርጉበት ነው።
ሲመሰረት ዓላማው የድኅረ ጦርነት ሩሲያን መስፋፋት ለመከላከል ነበር።
እአአ በ1995 ሶቪየት ሕብረት ደግሞ የራሷን የጦር ጥምረት መሠረተች፤ የምሥራቅ አውሮፓ አገራት ያሉበትን የዋርሶው ስምምነት የተባለውን።
እአአ በ1991 የሶቪየት ሕብረት መፈራረስን ተከትሎ የቀድሞው የዋርሶው ስምምነት አባል አገራት ተገልብጠው የኔቶ አባል ሆኑ። ኔቶ አሁን 30 አባል አገራትን አካቷል።