ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩሲያ ግዙፍ ጦር የዩክሬንን ቁልፍ ከተማ ለመያዝ እየተዋጋ መሆኑን የኪዬቭ ወታደራዊ አዛዥ አመኑ
የዩክሬን ከፍተኛ የጦር አዛዥ ፖክሮቪስክ የተባለችውን ቁልፍ የምሥራቅ ግንባር ከተማ ብዛት ካላቸው የሩሲያ ኃይሎች ለመከላከል ወታደሮቻቸው "ከባድ ሁኔታ" እንደገጠማቸው አምነዋል።
ጂን ኦሌክሳነድር ሲይረስኪ የዩክሬን ወታደሮች "በርካታ ሺህዎች ጠላት" ፊት ለፊት መግጠማቸውን ተናግረው ሩሲያ ተከበዋል አሊያም መፈናፈኛ አጥተዋል ማለቷን አስተባብለዋል።
ምንጮች በሩሲያ ጥይት እየዘነበበት ነው ያሉትን ቁልፍ የአቅርቦት መስመር ለመጠበቅ የዩክሬን ልዩ ኃይል መሰማራቱን የጦር አዛዡ አረጋግጠዋል።
የሞስኮ መከላከያ ሚኒስቴር የዩክሬን ወታደሮች እጅ እየሰጡ መሆኑን እና 11 የልዩ ኃይሉ አባላት በሂልኮፕተር ከደረሱ በኋላ መገደላቸውን አስታውቋል።
ኪዬቭ ይህን መግለጫ ውድቅ አድርጋለች።
ቅዳሜ ዕለት የጦር አዛዡ በቴሌግራም ባሳፈሩት ጽሑፍ በምሥራቅ ዶኔትስክ ክልል ከወታደራዊ አዛዦች በአካል ሪፖርት ለማድመጥ "ወደ ግንባር ተመልሻለሁ" ብለዋል።
ይፋ ባደረጉት አጭር ተንቀሳቃሽ ምስል ሲይረስኪ የጦርነት ካርታዎችን የዩክሬን ወታደራዊ ደኅንነት ኃላፊ ካይሪይሎ ቡዳኖቭን ጨምሮ ከጦር አዛዦች ጋር ሲያጠኑ ይታያሉ።
ይህ ምስል መቼ እና የት እንደተቀረፀ ግልፅ አይደለም።
የዩክሬን መገናኛ ብዙኃን ከሰሞኑን ቡዳኖቭ የልዩ ኃይሎችን ተልዕኮ ለመከታተል በአካባቢው እንደነበሩ ዘግበዋል።
የልዩ ኃይሎች መዝመት የኪዬቭ ባለሥልጣናት ሩሲያ ከአንድ ዓመት በላይ ለመቆጣጠር እየሞከረች ያለችውን ከተማዋን ላለመልቀቅ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት ነው።
የዩክሬን 7ተኛ ፈጥኖ ደራሽ ቅዳሜ ዕለት የዩክሬን ወታደሮች በፖክሮቨስክ "ያላቸውን የታክቲካል ቦታ አሻሽለዋል" ያለ ሲሆን፤ ነገር ግን ሁኔታው "አስቸጋሪ እና ተለዋዋጭ" ነው ብሏል።
አርብ ዕለት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ፖክሮቨስክን መካላከል "ቅድሚያ የሚሰጠው" እንደሆነ በአፅንኦት ተናግረዋል።
በስልታዊቷ ከተማ ሩሲያ እየገሰገሰች ነው የሚሉ ሰፊ ሪፖርቶች አሉ።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር የዩክሬን ወታደራዊ ደኅንነት ልዩ ኃይል በከተማዋ ሰሜን ምዕራብ አካባቢ ለመሰማራት ሲንቀሳቀስ መመለሱን እና 11 ወታደሮችን መግደሉን አስታውቋል።
'ዲፕስቴት' የተባለ የዩክሬን መረጃ ተከታታይ ቡድን የከተማዋ ግማሽ ክፍል "ግራጫ ዞን" እንደሆነ እና ሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች ሙሉ ለሙሉ እንዳልተቆጣጠሩት ጠቁሟል።
በዶኔትስክ የሚገኙ የቢቢሲ ወታደራዊ ምንጮች የዩክሬን ወታደሮች እንዳልተከበቡ ነገር ግን ግብዓት ማመላለሻ መስመሮች በሩሲያ ወታደሮች ጥቃት እየዘነበባቸው ነው ብለዋል።
ሞስኮ ኪዬቭ ዶኔትስክ እና ሉሃንስክ የተባሉ ክልሎችን (አንድ ላይ ዶንባስ ተብለው የሚጠሩ) በሰላም ስምምነት አካል አድርጋ እንድትሰጣት ትሻለች።
ሩሲያ ጥር 2015 ዓ.ም. ዩክሬን ላይ ሙሉ ለሙሉ ወረራ የፈፀመች ሰሆን ከአስር ዓመት በፊት የገነጠለቻትን ክሬሚያን ጨምሮ አሁን ላይ የዩክሬንን 20 በመቶ ግዛት ትቆጣጠራለች።
ፖክሮቨስክ ቁልፍ የትራንስፖርት እና የግብዓት ማዕከል ስትሆን የሚቆጣጠራት አካል ሩሲያ ክልሉን ለመቆጣጠር ለምታደርገው ጥረት ወሳኝ እንደሚሆን ይታመናል።