ትራምፕ ከፑቲን ጋር "ያለፍሬ የሚጠናቀቅ ስብሰባ" ማድረግ እንደማይፈልጉ ተናገሩ

ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያው አቻቸው ጋር በዩክሬን ጦርነት ላይ ተገናኝተው ለመነጋገር የያዙት ቀጠሮ እንዲዘገይ ከተደረገ በኋላ "ያለ ፍሬ የሚጠናቀቅ ስብሰባ" እንዲሆን እንደማይፈልጉ ተናገሩ።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ለሁለቱ አገራት የተኩስ አቁም ንግግር አጣብቂኝ የሆነው ሩሲያ ውግያ እያካሄደች በምትገኝበት ግንባር ተኩስ ለማቆም ፈቃደኛ አለመሆኗ እንደሆነ ማክሰኞ ዕለት በዋይት ሐውስ ተናግረዋል።

ቀደም ብሎ የዋይት ሐውስ ባለሥልጣን በቅርብ ጊዜ ትራምፕ እና ፑቲን እንዲገናኙ "ምንም ዕቅድ የለም" ብለዋል።

ሁለቱ መሪዎች በቡዳፔስት በሁለት ሳምንት ውስጥ ተገናኝተው እንደሚነጋገሩ የተገለፀው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት ነበር።

በዚህ ሳምንት በአሜሪካ እና በሩሲያ የሰላም ምክረ ሃሳቦች መካከል ያለው ልዩነት ግልጽ የሆነ ይመስላል።

ይህም ይካሄዳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረውን ስብሰባ ያስቀረ ሆኗል።

ትራምፕ እና ፑቲን ለመጨረሻ ጊዜ ፊት ለፊት የተገናኙት በነሐሴ ወር በአላስካ ነበር።

ይህ የሁለቱ መሪዎች ውይይት የዩክሬንን ጦርነት መቋጫ በመፈለግ ረገድ ተጨባጭ የሆነ ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል።

ዋይት ሐውስ የሁለቱ መሪዎችን ስብሰባ ላልተወሰነ ጊዜ ማዘግየት የመረጠበት አንዱ ምክንያት ተመሳሳይ የሆነ ስኬት አልባ ውይይትን ለማስቀረት በማሰብ ይመስላል።

አንድ ከፍተኛ አውሮፓ ዲፕሎማት ለሮይተርስ የዜና ወኪል "ሩሲያ ፍላጎቷ ብዙ ይመስለኛል፤ እንዲሁም አሜሪካ ትራምፕ በፑዳፔስት በሚያካሄዱት ስብሰባ ላይ ስምምነት መድረስ አንዳማይቻል ግልጽ የሆነላቸው ይመስለኛል" ብለዋል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚነሲትር ማርኮ ሩቢዮ እና የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በዚህ ሳምንት ተገናኝተው በዝግጅቱ ላይ ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር።

ዋይት ሐውስ ግን ሁለቱ ባለሥልጣናት "ውጤታማ" የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጾ ስብሰባው ከአሁን በኋላ "አስፈላጊ አይደለም" ብሏል።

ሰኞ ዕለት ትራምፕ ኪየቭ እና የአውሮፓ መሪዎች በውግያ ግንባሮች የተኩስ አቁም እንዲደረግ ያቀረቡትን ምክረ ሃሳብ ተቀብለውት ነበር።

"አሁን ባለበት እንዲቆም ይሁን" ካሉ በኋላ "እኔ የምለው በውግያ ግንባር ያለውን አቁሙ። ወደ የቤታችሁ ሂዱ። ውግያ ይቁም፤ ሰዎች መሞታቸው ይቁም ነው።"

ሩሲያ በተደጋጋሚ በግንባሮች የሚካሄደው ጦርነት ይቁም የሚለውን ሀሳብ ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በተደጋጋሚ ሃሳቡ ለሩሲያ ቢቀርብም "የሩሲያ ወጥ አቋም አልተቀየረም" ብለዋል።

ሞስኮ ውግያ ከሚካሄድባቸው የምሥራቃዊ ግዛቶች የዩክሬን ጦር ሙሉ በሙሉ ለቅቆ እንዲወጣ ትጠይቃለች።

ሞስኮ ፍላጎት ያላት "ዘላቂ፣ አስተማማኝ ሰላም ላይ" ብቻ ነው ያሉት ሰርጌይ ላቭሮቭ ውግያ በሚካሄድባቸው ግንባሮች ተኩስ ማቆም ጊዜያዊ መፍትሄ ብቻ እንደሚያመጣ ጠቅሰዋል።

የግጭቱ መሠረታዊ ምክንያት ላይ ማተኮር ያስፍለጋል ያሉት ላቭሮቭ፣ ክሬምሊን ዶንባስ የሩሲያ ሉዓላዊ ግዛት መሆኗ እውቅና እንዲሰጥ እንዲሁም ከዩክሬን ወታደራዊ ኃይል ነጻ እንዲሆን ጠይቀዋል።

ይህ ደግሞ ለኪየቭ እና ለአውሮፓ አጋሮቿ ተቀባይነት የሌለው ጥያቄ ነው።

የአውሮፓ መሪዎች ከዜሌንስኪ ጋር በመሆን ማክሰኞ ዕለት ባወጡት መግለጫ በዩክሬን የሚካሄደውን ጦርነት የሚያስቆም የትኛውም ንግግር በጦር ግንባር የሚካሄደውን ውጊያ ባለበት የሚያስቆም መሆን አለበት ብለዋል።

አክለውም ሩሲያ ለሰላም ቁርጠኝነት የላትም ሲሉ ወንጅለዋታል።