ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ኪየቭ በሩሲያ የተወሰዱባትን ግዛቶች በሙሉ ታስመልሳለች አሉ
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ዩክሬን የተወሰዱባትን ግዛቶቿን በሙሉ መልሳ ማግኘት ትችላለች" አሉ።
ይህ የፕሬዚዳንቱ አስተያየት ከዚህ ቀደም ከሩሲያ ጋር እየተደረገ ስላላው ጦርነት የነበራቸው አቋም መቀየሩን ያመላከተ ነው ተብሏል።
በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በለጠፉት መልዕክት አውሮፓ እና ኔቶ በሩሲያ ምጣኔ ኃብት ላይ ጫና በመፍጠር በሚያደርጉት ድጋፍ "ዩክሬን ጦርነቱ ሲጀመር የነበሯትን ድንበሮች መልሳ ማግኘት ትችላለለች" ብለዋል።
ትራምፕ ይህንን አስተያየት የሰጡት ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር በተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ላይ ማክሰኞ ዕለት ተገናኝተው ከተነጋገሩ በኋላ ነው።
ትራምፕ በተደጋጋሚ ጦርነቱ እንዲያበቃ ያላቸውን ፍላጎት ሲገልጹ ቆይተዋል።
ነገር ግን ያንን ለማድረግ ዩክሬን የተወሰኑ ግዛቶቿን ለመስጠት ፈቃደኛ መሆን አንዳለባት የገለፁ ቢሆንም ዜሌንስኪ ግን በምላሹ ሃሳቡን ውድቅ ሲያደርጉት ቆይተዋል።
ትራምፕ በዚሁ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው ላይ ዩክሬን "ከዚያም በላይ ልትሄድ ትችላለች" ያሉ ቢሆንም ይህን ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ አላብራሩም።
ሩሲያ እአአ በ2014 ወደ ራሷ ስለጠቀለለቻት ክሬሚያ ምንም ያሉት ነገር የለም።
ሩሲያ ዩክሬንን የወረረችው እአአ በ2022 ነበር።
ትራምፕ አቋማቸውን የቀየሩት "የዩክሬንን እና ሩሲያን ጦር እንዲሁም የምጣኔ ኃብት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ካወቁ እና ከተረዱ በኋላ" መሆኑን ገልፀዋል።
ሩሲያን "የወረቀት ላይ ነብር" ሲሉ የወረፉት ፕሬዚዳንቱ "ፑቲን እና ሩሲያ ግዙፍ የሆኖ የኢኮኖሚ ማጥ ውስጥ ናቸው እንዲሁም አሁን ጊዜው ዩክሬን እርምጃ የምትወስድበት ነው" ብለዋል።
ዜሌንስኪ ይህንን የፕሬዚዳንት ትራምፕ አቋም "ትልቅ ለውጥ" ብለው ያደነቁ ሲሆን በመንግሥታቱ ድርጅት ለጋጠኞች ዩናይትድ ስቴትስ ለአገራቸው "ጦርነቱ ካበቃ በኋላ" የደህንንት ዋስትና ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኗን መረዳታቸውን ተናግረዋል።
ይህ ምን ማለት እንደሆነ የተጠየቁት ዜሌንስኪ "መዋሸት አልፈልግም፥ ዝርዝሩ ገና የለንም" በማለት የጦር መሣሪያ፣ የአየር መከላከያ እና የድሮን ድጋፍ እንደሚሆን ግን ተናግረዋል።
ዜሌንስኪ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቃለመጠይቅ ወቅት ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ስለ ዩክሬን የተናገሩት እንዳስደነቃቸው ገልፀው ይህንንም ትራምፕ እና ዩኤስ "ጦርነቱን ለማስቆም ከእኛ ጋር መሆናቸውን" እና "እንደ አዎንታዊ ምልክት" እወስደዋለሁ ብለዋል።
"ፑቲን በተደጋጋሚ ትራምፕን መዋሸታቸው በእኛ መካከል ልዩነት የፈጠረ ይመስለኛል" ሲሉ ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።
ትራምፕ በተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር የኔቶ አባል አገራት የአየር ክልላቸውን ጥሰው የሚገቡ የሩሲያን አውሮፕላኖች መትተው እንዲጥሉ ተናግረዋል።
የሩሲያ ጄቶች እና ድሮኖች በተደጋጋሚ የጎረቤት አገራትን የአየር ክልል ጥሰው መግባታቸው ሲገለጽ ቆይቷል።
ባለፈው ሳምንት ኢስቶኒያ እና ፖላንድ ሩሲያ የአየር ክልላቸውን ጥሳ መግባቷን ተከትሎ የኔቶ አባል አገራትን ድጋፍ የጠየቁ ሲሆን ሌላዋ የኔቶ አባል አገር የሆነችው ሮማኒያ የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች የአየር ክልሏን ጥሰው መግባታቸውን አስታውቃለች።
ሩሲያ የኢስቶኒያን አየር ክልል ጥሳለች መባሉን አስተባብላ የፖላንድን ግን ሆን ተብሎ የተደረገ አለመሆኑን ገልጻለች።
ሮማኒያ ስላቀረበችው ውንጀላ ግን ምንም ያለችው ነገር የለም።
ትራምፕ አሜሪካ የኔቶ አባል አገራት የሩሲያን አውሮፕላኖች መትተው ቢጥሉ ትደግፋለች ወይ ተብለው ተጠይቀው "እንደ ሁኔታው ይወሰናል" በማለት አባል አገራቱ የመከላከያ ወጪያቸውን ከፍ በማድረጋቸው አድንቀዋል።
የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን አባል አገራት እአአ በ2035 የመከላከያ ወጪያቸውን ወደ 5 በመቶ ከፍ ለማድረግ መስማማታቸውን በመጥቀስ "ኔቶ ተሻሽሏል" ብለዋል።
ትራምፕ በመንግሥታቱ ድርጅት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር የኔቶ አባል አገራት የሩሲያን ኢነርጂ መግዛት ባለማቋረጣቸው "በራሳቸው ላይ የሚደረግን ጦርነት በገንዘብ እየደገፉ ነው" ሲሉ ተችተዋል።