ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ በሁለት የሩሲያ ነዳጅ አምራች ድርጅቶች ላይ አዲስ ማዕቀብ ጣለች
አሜሪካ በሁለት የሩሲያ ነዳጅ አምራች ድርጅቶች ላይ አዲስ ማዕቀብ መጣሏ ተገለጸ።
በሁለቱ ግዙፍ ነዳጅ አምራቾች ሮስኔፍት እና ሉክኦይል ላይ ማዕቀብ የተጣለው ሩሲያ የዩክሬንን ጦርነት ለማቆም ከስምምነት እንድትደርስ ጫና ለማሳደር ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩቴ ጋር ከተወያዩ በኋላ "ከፑቲን ጋር ጥሩ ንግግሮችን ባደርግም ውጤት አያመጡም" ብለዋል።
ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በቡዳፔስት ሊያደርጉ አቅደው የነበረውን ውይይት አራዝመዋል።
ሩሲያ ትናንት በፈጸመችው ድብደባ ሕጻናትን ጨምሮ ሰባት ሰዎች ተገድለዋል።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ጸሐፊ ስኮት ባሴት፤ አዲስ ማዕቀብ መጣል ያስፈለገው "ፑቲን ትርጉም አልባው ጦርነት እንዲገታ ስላልተስማሙ ነው" ብለዋል።
ነዳጅ አምራች ድርጅቶቹን የክሬምሊን "የጦር መሣሪያ" ሲሉ ገልጸዋቸዋል። በአፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈረምም አሳስበዋል።
ፑቲን ለሰላም ስምምነት ዝግጁ አይደሉም ሲሉ ትራምፕ ተችተዋል። ማዕቀቡ በፑቲን ላይ ጫና እንደሚያሳድርም ይጠብቃሉ።
"ረዥም ጊዜ ጠብቀናል፤ አሁን ግን [በማዕቀብ ጫና ለማሳደር] ጊዜው ደርሷል" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ "በጣም ትልቅ" ያሉት ማዕቀብ ፑቲን ጦርነቱን ለማቆም ከተስማሙ የሚቀለበስ ይሆናል።
የአሜሪካ እና የሩሲያ የሰላም ዕቅድ ሰፊ ልዩነት እንዳለው ለማወቅ ተችሏል።
ሞስኮ ጦርነቱን ለማቆም አለመፍቀዷ ዋና ልዩነታቸው እንደሆነ አሜሪካ አስታውቃለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ማርኮ ሩቢዮ አሁንም ቢሆን ከሩሲያ ጋር ለመነጋገር አገራቸው ፈቃደኛ መሆኗን ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት ዩናይትድ ኪንግደም በሁለቱ ግዙፍ ነዳጅ አምራቾች ሮስኔፍት እና ሉክኦይል ላይ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።
በዩኬ የሩሲያ ኤምባሲ፤ ማዕቀቡ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያን ያናጋል ብሏል።
ኤምባሲው ባወጣው መግለጫ "በታዳጊ አገራት የኃይል አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ጫና ለማሳደር መሞከር የሰላም ንግግሩን የሚያሰናክል እና ውጥረቱን የሚያባብስ ነው" ብሏል።
ሁለቱ የሩሲያ ነዳጅ አምራቾች በየቀኑ 3.1 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ወደ ውጭ አገራት ይልካሉ።
ሮስኔፍት ከሩሲያ የነዳጅ አቅርቦት ግማሹን ይሸፍናል። ከዓለም አቀፍ ገበያው ደግሞ 6% ድርሻ አለው።
ቻይና፣ ሕንድ እና ቱርክ ዋነኛ የሩሲያ ነዳጅ ተጠቃሚዎች ናቸው። የአገሪቱ ከፍተኛ ገቢ የሚገኘውም ከነዳጅ ሽያጭ ነው።
ሌሎች አገራትም የሩሲያ ነዳጅ ላይ ማዕቀብ በመጣል ጫና እንዲያሳድሩ ትራምፕ ጠይቀዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኧርሰላ ቮን ደር ሊይን "ሩሲያ ለሰላም ስምምነት ቁርጠኛ አይደለችም" ብለዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ትናንት ሩሲያ ላይ ማዕቀብ መጣሉም ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።
እአአ በ2025 መባቻ ላይ አሜሪካ እና ዩኬ ጋዝፕሮም እና ሰርጉትኔፍትጋዝ በተባሉ የሩሲያ የነዳጅ ድርጅቶች ላይ ማዕቀብ ጥለዋል።
አሜሪካ ከዩክሬን እንዲሁም ከአውሮፓ እና ከኔቶ አጋሮቿ ጋር 12 ነጥብ ያለው የሰላም ዕቅድ ላይ ለመወያየት አቅዳ ነበር።
ጦርነቱ አሁን ባለበት የውጊያ መስመር ላይ እንዲቆም፣ የታገቱ ልጆች እንዲመለሱ እና ሁለቱ አገራት እስረኛ እንዲለዋወጡ የድርድር ነጥቦች ቀርበዋል።
ለዩክሬን መልሶ ግንባታ ገንዘብ መመደብ እና ዩክሬን ወደ የአውሮፓ ኅብረት የምትቀላቀልበትን መንገድ ማመቻቸት በዕቅዱ ተካተዋል።
ትራምፕ በቡዳፔስት ከፑቲን ጋር ተገናኝተው "ፍሬ አልባ ውይይት" ማካሄድ እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ሁለቱ መሪዎች በአላስካ ቢገናኙም ውይይታቸው የተጠበቀውን ውጤት አላመጣም።
መሪዎቹ ለሁለተኛ ጊዜ በቡዳፔስት ከመገናኘታቸው በፊት የውጭ ጉዳይ ኃላፊዎቻቸው እንዲነጋገሩ ዕቅድ ቢያዝም፤ ውይይቱ ተራዝሟል።
የሩሲያ ወታደሮች አሁን ባሉበት ቦታ ሆነው ጦርነቱ እንዲቋጭ አሜሪካ ብትፈልግም፤ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ እንዳሉት የዩክሬን ወታደሮች ከዶንባስ መውጣት አለባቸው።