ጠ/ሚ ዐቢይ ለሚሾሙት ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት የትግራይ ህዝብ ዕጩዎችን እንዲጠቁም ጥሪ አቀረቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እርሳቸው ለሚሾሙት ጊዜያዊ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት የክልሉ ህዝብ ዕጩዎችን እንዲጠቁማቸው ረቡዕ፣ መጋቢት 17/ 2017 ዓ.ም በኤክስ ገፃቸው ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁለት ዓመት ቆይታው የተጠናቀቀው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ለቀጣዩ አንድ ዓመት እንደሚቀጥል እና "በግለሰቦች ረገድ ለውጥ ሊደረግ እንደሚችል" በቅርቡ ለፓርላማው ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ነው ይህንን የፕሬዚዳንት ዕጩ ጥቆማ ጥሪ በትግርኛ ቋንቋ ያስተላለፉት።

በዚሁ የፓርላማ ንግግራቸው "በጠንካራ ጎናቸው ተወድሰው በደካማ ጎናቸው ተወቅሰው የሚቀያየሩ ሰዎች እንደሚኖሩ" የተናገሩ ሲሆን፤ በቅርቡ የፌደራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የጠየቁት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ከስልጣናቸው ስለመነሳታቸው ያሉት ነገር የለም።

ዐቢይ ለእጩዎች ጥቆማነት ያቀረቧቸውን መስፈርቶች የጊዜያዊ አስተዳደር ተግባራት በብቃት የሚወጡ እና የክልሉን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ "ይችላሉ ብላችሁ የምታምኗቸውን እጩዎች" ከዛሬ ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ኢሜይል በመላክ መጠቆም እንደሚቻል ጠቅሰዋል።

"የትግራይ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጥቆማ ጥሪ" በሚል ርዕስ በማህበራዊ ገጻቸው ላይ የወጣው ጥሪያቸው ጥቆማው ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ያለው ነገር የለም።

ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት የቋጨው የፕሪቶሪያ ግጭትን በዘላቂነት የማስቆም ስምምነት መሰረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋሙ ይታወሳል።

በፌደራሉ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እና ግጭትን ለማቆም በተደረገው ስምምነትን አንቀጽ 10 (1) መሰረት አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሟል። ይህ የፕሪቶሪያው ስምምነት ሁሉን አካታች የሆነ የትግራይ ጊዜያዊ ክልላዊ አስተዳደር የሚቋቋመው ህወሓት እና የፌደራሉ መንግሥት በሚያደርጉት ፖለቲካዊ ውይይት ይሆናል ይላል።

አስተዳደሩን ለማቋቋም የወጣው "የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 533/2015 "ርዕሰ መስተዳድሩ በሰላም ስምምነቱ መሠረት በሚደረግ የፖለቲካ ምክክር ተለይቶ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሾማል" ይላል። ዐቢይ ይህንን ደንብ በመጥቀስ የትግራይ ክልልን ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ኃላፊነት የሳቸው መሆኑን በዚሁ መልዕክታቸው አስፍረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣዩ ክልሉን የሚያስተዳድሩት ርዕሰ መስተዳድር ሹመት በተመለከተ በደንቡ እና በስምምነቱ መሰረት ከህወሓት ጋር ምክክር አድርገው እንደሆነ የተጠቀሰ ጉዳይ የለም።

የፕሪቶሪያ ስምምነት ሌላኛው ተፈራራሚ ህወሓት በጉዳዩ ላይ እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።

ዐቢይ በዚሁ ጥሪያቸው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሲቋቋም መሰረት ባደረገው አዋጅ መሰረት የሁለት ዓመት የቆይታ ጊዜው የተጠናቀቀው መሆኑን አስታውሰው፤ ተጨባጭ ምክንያት ካለ የጊዜያዊ አስተዳደር ሊራዘም እንደሚችል አስፍረዋል።

በዚህም መስረት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለሚቀጥለው አንድ ዓመት እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱት፣ ፌደራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ስርዓት ለመደንገግ የወጣው አዋጅ 359/1995ን ሲሆን፤ ይህም "ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ የሚቆየው ከሁለት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ነው።ሆኖም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የፌዴሬሸን ምክር ቤት የመቆያ ጊዜውን ከስድስት ወራት ላልበለጠ ጊዜ ለማራዘም ይችላል" ሲል ያትታል።

ዐቢይ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ስራውን በሁለት ዓመት ውስጥ አጠናቅቆ ኃላፊነቱን በህዝብ ለተመረጠው መንግሥት ማስረከብ እንደነበረበት በዚሁ መልዕክታቸው ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ቁልፍ ተግባራቶቹን በወቅቱ ማከናወን እንዳልቻለ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነዚህም መካከል ለምርጫ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም ምክንያት የህግ ማሻሻያ በማድረግ የጊዜያዊ አስተዳደሩን የስልጣን ጊዜ በአንድ ዓመት ማራዘም አስፈላጊ ሆኖ መንግሥታቸው እንዳገኘው ገልጸዋል።

መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የጊዜያዊ መንግሥቱን የስልጣን ዘመን በማራዘም ላይ እንዳለ በዚሁ ጥሪያቸው ገልጸው፤ ከዚህም ጋር ተያያይዞ አዲስ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት መሾም አስፈላጊ ነው ተብሏል።

የቆይታ ጊዜው የተጠናቀቀው የጊዜያዊ አስተዳደሩን በተመለከተ ዐቢይ በቅርቡ ባደረጉት የፓርላማ ማብራሪያ ለማስቀጠል አስፈላጊ የሕግ ማሻሻያዎች እንደሚከናወኑም አስታውቀው ነበር።

ዐቢይ ሐሙስ መጋቢት 11/2017 በፓርላማ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ የሚቀጥለው አስተዳደር እስከ ቀጣይ ምርጫ ድረስ እንደሚቆይ ተናግረዋል።

ይህንን ለማድረግ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው እና ምክትሎቻቸው ጄነራል ታደሰ ወረደ እና ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳይ ጋር ምክክር መደረጉን ገልጸዋል።

ዐቢይ፤ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ፓርቲዎች ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ መሰረት አስፈላጊው የሕግ ማሻሻያ ተደርጎ ለሚቀጥለው አንድ ዓመት ይቀጥላል ብለዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተጨማሪ ውጊያ እንዳይቀሰቀስ በማድረግ ረገድ ለሰራው ስራ መመስገን አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "የሰጠናቸው የሁለት ዓመት ጊዜ አብቅቷል። ተጨማሪ የሕግ ማሻሻያ የሚያስፈልገው ጉዳይ አለ፤ የሕግ ማሻሻያው ተገምግሞ እና መጠነኛ ማሻሻያ ተደርጎ በፕሪቶርያ ስምምነት መሰረት ጊዜያዊ አስተዳደሩ እስከ ሚቀጥለው ምርጫ ድረስ ስራውን እየሰራ ሕዝቡን ለምርጫ ማዘጋጀት እና ሕዝቡ የስልጣን ባለቤት መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል" ብለዋል።

ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት፤ ፓርቲው በሊቀመንበሩ ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረ ሚካኤል እና በምክትል ሊቀመንበሩ ጌታቸው ረዳ በሚመሩ ቡድኖች ተከፍሎ እየተወዛገበ ይገኛል።

ለወራት በገለልተኝነት ከቆዩት የትግራይ ሠራዊት አዛዦች መካከል አብዛኞቹ በደብረፂዮን ለሚመራው ወገን ድጋፍ መስጠታቸውን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ስጋት ተፈጥሯል።

በቅርቡ በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል መግለጫ የሰጡት አቶ ጌታቸው ወደ ትግራይ ይመለሱ እንደሆነ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ "አዎ እመለሳለሁ። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያለኝን ስበሰባ ማጠናቀቅ አለብኝ። በሚቀጥሉት ቀናት ሌሎች ስብሰባዎችም አሉኝ። በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ [ወደ ትግራይ] እመለሳለሁ። ዕቅዴ እሱ ነው" ብለው ነበር።

በትግራይ ለወራት የቆየው እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ያለው ውጥረት እና ፍጥጫ ከሁለቱ ዓመት የደም አፋሳሽ ጦርነት ባላገገመው ሕዘብ ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።