የዓለም ሕግን መሠረት ያደረገ ሥርዓት ''ከዚህ በኋላ የለም" ሲሉ የጀርመኑ መራሄ መንግሥት አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock
በሕጎች ላይ የተመሠረተው የዓለም ሥርዓት " ከእንግዲህ የለም " ሲሉ የጀርመን መራሄ መንግሥት አስጠነቀቁ።
ፍሬድሪክ መርዝ ዓመታዊውን የሙኒክ የጸጥታ ጉባኤ በንግግር ሲከፍቱ ለሌሎች የዓለም መሪዎች በኃያላን ፖለቲከኞች ዘመን "ነፃነታችን ዋስትና የለውም" ሲሉ ተናግረው አውሮፓውያን "መስዋዕትነት" ለመክፈል ዝግጁ መሆን አለባቸው ብለዋል።
በተጨማሪም "በአውሮፓና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ጥልቅ ክፍፍል መፈጠሩን" አምነዋል።
የጸጥታ ጉባዔው የሚካሄደው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን ለመጠቅለል ያላቸውን ፍላጎት በገለፁበት እንዲሁም ከአውሮፓ አገራት በሚመጡ ምርቶች ላይ ተጨማሪ ታሪፎች ላይ ለመጣል በዛቱበት ወቅት ነው።
በጉባዔው ላይ የተገኙት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የመርዝን ንግግር ያዳመጡ ሲሆን ቅዳሜ ዕለት ንግግራቸውን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቀደም ብሎ ስለ "ጂኦፖለቲካ አዲስ ዘመን" ተናግረዋል። በዚህ ጉባዔ ላይ ወደ 50 የሚጠጉ የዓለም መሪዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል።
ይህ ጉባዔ መካሄድ የጀመረው አሜሪካ ለሰሜን ቃልኪዳን ጦር የገባችውን ቃል መፈጸም አለመፈጸሟ ጥያቄ ውስጥ በገባበት ወቅት ነው።
ትራምፕ ግሪንላንድን ወደ ግዛታቸው ለማስገባት ያላቸው ፍላጎት በብዙ የአውሮፓ መሪዎች ዘንድ ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን መተማመን የሸረሸረ ጉዳይ ሆኗል።
ትራምፕ አርብ ዕለት ለጋዜጠኞች "ግሪንላንድ እኛን ትፈልጋለች... ከአውሮፓ ጋር በጥሩ ሁኔታ እንስማማለን። እንዴት እንደሚሄድ እናያለን። አሁን ለግሪንላንድ እየተደራደርን ነው" ብለዋል።
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት፣ በምዕራቡ ዓለም እና በቻይና መካከል ያለው ውጥረት፣ እንዲሁም የኢራን-አሜሪካ የኒውክሌር ስምምነት በዓመታዊ ስብሰባው ላይ አጀንዳዎች ሆነው ቀርበዋል።
የጀርመኑ መራሄ መንግሥት መርዝ በሕግ ላይ የተመሰረተው የዓለም ሥርዓት እየፈረሰ መሆኑን የሚገልጹ በርካታ ማስጠንቀቂያዎችን በመጥቀስ ለጉባዔው "ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ ማስቀመጥ አለብን ብዬ አስባለሁ። ይህ ሥርዓት ምንም ያህል ፍጹም ባይሆንም፣ አሁን ግን በዚያ መልኩ አይገኝም።" ብለዋል።
በተጨማሪም "በአውሮፓ እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል መለያየት፣ ጥልቅ ክፍፍል ተፈጥሯል። ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ይህንን ከአንድ ዓመት በፊት እዚህ ሙኒክ ውስጥ በግልጽ ተናግረዋል።"
መርዝ አክለውም "ትክክል ነበር። የማጋ [አሜሪካን እንደገና ታላቅ እናድርግ] ንቅናቄ የባህል ጦርነት እንቅስቃሴ የእኛ አይደለም። የመናገር ነፃነት እዚህ ጋር የሚያበቃው ያ ንግግር ከሰብዓዊ ክብር እና ከሕገ መንግሥቱ ጋር ሲጋጭ ነው። በታሪፍ እና በተከላካይነት አናምንም፣ በነጻ ንግድ እንጂ።" ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት ቫንስ የመናገር ነፃነትን እና የኢሚግሬሽን ፖሊሲዎችን በመቃወም አውሮፓን እና ዩናይትድ ኪንግደምን ሸንቁጠዋል። ንግግሩ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የትራንስ አትላንቲክ ውጥረት አስነስቷል።
ነገር ግን የጀርመኑ መራሄ መንግሥት መርዝ፣ ለአስርተ ዓመታት የዘለቀውን አጋርነት አልሰረዙም። ይልቁንም "የትራንስ አትላንቲክ እምነትን እንጠግን፤ እናድስ" በማለት በቀጥታ ለአሜሪካ ጥሪ አቅርበዋል።
የጀርመኑ መሪ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር የአውሮፓን የጋራ የኒውክሌር መከላከያ ለመፍጠር "ምስጢራዊ ውይይቶች" እየተካሄዱ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ግን አልሰጡም።
ፈረንሳይ እና ዩኬ በአውሮፓ ውስጥ የሚገኙ ሁለቱ የኒውክሌር ኃይል ያላቸው አገሮች ናቸው።
ነገር ግን ጀርመን እና ሌሎች በርካታ የአውሮፓ አገራት በተለምዶ በሰሜን አትላንቲክ ጦር ኃይሎች ውስጥ ያለውን የአሜሪካ የኒውክሌር ኃይል ለመከላከያ ኃይላቸው ይጠቀማሉ።
ማክሮን አርብ ዕለት በኮንፈረንሱ ላይ ንግግር ሲያደርጉ፣ በአዲሱ ዓለም አቀፍ ሁኔታ አውሮፓ "የጂኦፖለቲካዊ ኃይል ለመሆን መማር" አለባት ሲሉ ጥሪ በድጋሚ አቅርበዋል።















