ጋዛ 'እውነተኛ ረሃብ' ላይ መሆኑን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናገሩ

እሁድ ዕለት ጋዛ ደረሱት እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በአብዛኛው በረሃብ በተጎዱ ፍልስጤማውያን መዘረፋቸውን የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ ተናግረዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, እሁድ ዕለት ጋዛ ደረሱት እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በአብዛኛው በረሃብ በተጎዱ ፍልስጤማውያን መዘረፋቸውን የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ ተናግረዋል

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በጋዛ ረሃብ የለም ካሉ በኋላ ዶናልድ ትራምፕ በጋዛ "እውነተኛ ረሃብ" አለ ብለዋል።

ኔታኒያሁ እስራኤል በጋዛ ረሃብን እያባባሰች ነው መባሉን "ድፍረት የተሞላበት ውሸት" ነው ካሉ በኋላ በጉዳዩ ላይ ይስማማሉ ወይ ተብለው የተጠየቁት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት፤ "አላውቅም። . . .እነዚያ ሕፃናት በጣም የተራቡ ይመስላሉ። . . . ይህ እውነተኛ የረሃብ ጉዳይ ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ከዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታይመር ጋር በስኮትላንድ በነበራቸው ንግግር "በዚያ ማንኛውም ሰው የሰራው ትልቅ ነገር የለም። ሙሉ አካባቢው የተበላሸ ነው። . . . ለእስራኤል ምንአልባት ነገሮችን በተለየ መንገድ መስራት እንዳለባቸው ነግሬያቸዋለሁ" ብለዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር እሁድ ዕለት እስራኤል በጋዛ ሆን ብላ ንፁሃን ሰዎችን እያስራበች ነው መባሉን መሰረተ ቢስ ነው ብለዋል።

"እንዴት ያለ ድፍረት የተሞላበት ውሸት ነው። በጋዛ የማስራብ ፖሊሲ የለም። እናም በጋዛ ረሃብ የለም" ብለዋል።

የትራምፕ አስተያየት የተሰማው የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ ረሃቡን ለመቀልበስ "በጣም ብዙ" ምግብ ያስፈልጋል ማለታቸውን ተከትሎ ነው።

የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ ቶም ፍሌቸር እስራኤል በጋዛ በአየር የሚወረወር እርዳታ እንዲደርስ እና ምግብ የጫኑ ተሽከርካሪዎች እርዳታ ፈላጊዎች ላይ እንዲደርሱ የጦር እንዲቅስቃሴ እንዲገታ መፍቀዷን እንደሚቀበሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ከሚያስፈልገው እርዳታ እስካሁን የደረሰው "ከውቅያኖሱ በጭልፋ" እንደሆነ ጠቁመዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"የመጀመሪያው ነው፤ ነገር ግን የሚቀጥሉት ቀን መውጫ አሊያም መሰበሪያ ናቸው። በጣም በስፋት ማድረስ ይኖርብናል። በጣም ከፍተኛ መጠን የአየር ተወርዋሪ እርዳታ በፍጥነት ያስፈልገናል" ሲሊ ለቢቢሲ ራዲዮ ተናግረዋል።

እስራኤል እሁድ ዕለት ለ10 ሰዓታት በተደረገው የወታደራዊ እንቅስቃሴ "ስልታዊ አፍታ" 120 ጭነት የጫኑ ተሽከርካሪዎች መሻገራቸውን እና ዮርዳኖስ፣ አሜሪካ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች 28 የታሸጉ የምግብ ከረጢቶችን ከአየር መወርወራቸውን አስታውቃለች።

የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ ከተናገሩ ከሰዓታት በኋላ በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚነስቴር በ24 ሰዓታት ውስጥ ተጨማሪ 14 ሰዎች ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ማለፉን ገልጿል።

ይህም ጦርነቱ ከተጀመረ እ.አ.አ ከጥቅምት 2023 ወዲህ ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎችን ቁጥር 147 አድርሷል። ከእነዚህም ውስጥ 88ቱ ሕፃናት መሆናቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ይጠቁማል።

የጋዛን የአቅርቦት በሮች የምትቆጣጠረው እስራኤል በጋዛ ረሃብ መኖሩን በመካድ ለምግብ እጥረቱ ኃላፊነቱን እንደምትወስድ የቀረበባትን ውንጀላ ውድቅ አድርጋለች።

እሁድ ዕለት የእስራኤል ጦር በጋዛ "የሰብዓዊ ምላሽ አሰጣጥን" ያሻሽላል ያለውን እና "ሆን ተብሎ ረሃብ ፈጥሯል የተባለውን የሐሰት ውንጀላ" ለማስተባበል እርምጃ መውሰድ ጀምሯል።

አገሪቱ በሦስት የጋዛ አካባቢዎች በየቀኑ ለ10 ሰዓታት የሚቆይ የወታደራዊ እንቅስቃሴ ገደብ እንዲሁም እርዳታ ለጫኑ ተሽከርካሪዎች አስተማማኝ መንገዶችን እንደምትመድብ አስታውቃለች።

የእስራኤል ጦር የሰብዓዊ ድርጅቶች አደገኛ እና ውጤታማ ያለሆነ መንገድ ያሉትን እርዳታ የውጭ አገራት ከአየር መወርወር እንዲቀጥሉ ፈቅዷል።

የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ በአካባቢው ያሉ ሰራተኞች የእስራኤል ጦር እንቅስቃሴ ለአንድ ሳምንት ገደማ ብቻ እንደሚቆይ እምነት እንዳላቸው ጠቁመው፤ ይህም በ21ኛው ክፍለ ዘመን እየታየ ላለው አረመኔያው ድርጊት በቂ እንዳልሆነ አስምረዋል።

የእስራኤል ጦር እ.አ.አ ጥቅምት 7/2023 ሐማስ በከፈተው ጥቃት 1,200 ሰዎች መገደላቸውን እና 251 ሰዎች ደግሞ ታግተው መወሰዳቸውን ተከትሎ ዘመቻ ከፍቷል።

በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ እስካሁን በጋዛ 59,821 ሰዎች በእስራኤል ጦር ተገድለዋል።