የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተጫዋቾች “ጨዋታ በዛብን” በሚል አድማ ይመቱ ይሆን? ሕጉስ ምን ይላል?

የማንቸስተር ሲቲው ስፔናዊ አማካይ ሮድሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የማንቸስተር ሲቲው አማካይ ሮድሪ ተጫዋቾች ጫና ስለበዛባቸው አድማ ለመምታት “ተቃርበዋል” ሲል ባለፈው ማክሰኞ ተናግሮ ነበር።

ስፔናዊው አማካይ ባለፈው የውድድር ዘመን ለአገሩ እና ለክለቡ 63 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን፣ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ጨምሮ ከሐምሌ 2015 እስከ ሐምሌ 2016 ባለፈው ጊዜ 6107 ደቂቃዎች ተጫውቷል።

የሊቨርፑሉ በረኛ አሊሰን በበኩሉ ተጫዋቾች የሚያነሱትን ቅሬታ የሚሰማ አልተገኘም በማለት የመርሃ-ግብር መጨናነቅ እንዳለ ተናግሯል።

በቅርቡ የወጣ አንድ ዘገባ እንደሚጠቁመው አንድ ተጫዋች በዕድሜው መሠረት በዓመት ከ50 እስከ 60 ጨዋታዎች በላይ ጨዋታዎች ካደረገ “ቀይ መስመር” ረግጧል ማለት ነው።

ጨዋታ በዛብን ያሉ ተጫዋቾች አድማ ይመቱ ይሆን? ሕጉስ ምን ይላል?

ዓለም አቀፉ የስፖርት ጥናት ማዕከል በቅርቡ ባወጣው ጥናት ከ12 ዓመት በፊት ከነበረው አንፃር ክለቦች ዘንድሮ ብዙ ጨዋታ እያደረጉ አይደለም ይላል።

ጥናቱ እንደሚጠቁመው 0.31 በመቶ ተጫዋቾች ከ61 በላይ ጨዋታዎች ሲያደርጉ 1.8 በመቶ የሚሆኑት ከ51 እስከ 60 ጨዋታዎች ላይ ተሳትፈዋል። 6.8 በመቶው ደግሞ ከ41 እስከ 50 ግጥሚያዎች አድርገዋል።

ከአውሮፓውያኑ 2012 እስከ 2024 ባለው ጊዜ የአንድ ቡድን አማካይ የውድድር ዘመን ጨዋታ 40 ነው ሲል 5 በመቶ የሚሆኑ ክለቦች ደግሞ 60 እና ከዚያ በላይ ጨዋታዎችን አድርገዋል።

በዚህ ጥናት ላይ የተካተቱት ከ40 ሊጎች የተውጣጡ ከ18 ሺህ እስከ 21 ሺህ የሚሆኑ ተጫዋቾች ሲሆኑ፣ በአማካይ 22.7 ጨዋታዎችን ማድረጋቸው ተዘግቧል።

ተጫዋቾች አድማ መምታት ይችላሉ፤ ፍላጎትስ አላቸው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በቅርቡ ወደ ፕሪሚዬር ሊጉ ያደጉት የሳውዝአምፕተን አሠልጣኝ ረስል ማርቲን ተጫዋቾቻቸው አድማ መምታት በሚለው ጉዳይ “ብዙም ደስተኛ” እንዳልሆኑ ይናገራሉ።

“ባለፈው የውድድር ዘመን 50 ጨዋታ ያለበት ሊግ ነበርን። አሁን ወደ 38 ዝቅ ብሏል። ሌሎች ጥቂት ጨዋታዎች ሊኖሩን ይችላሉ። እኔ ተጫዋቾቼ በዚህ ደስተኛ ይመስሉኛል” ይላሉ።

የሕግ ባለሙያው ሮስ ሜዶውስ ደግሞ ተጫዋቾች አድማ መምታት ከፈለጉ በፕሮፌሽናል የተጫዋቾች ማኅበር በኩል ነው ባይ ናቸው።

አድማ መምታት ማለት በጣም ትልቅ እርምጃ ስለሆነ መጀመሪያ ከተጫዋቾች ድምፅ መሰብሰብ ያስፈልጋል፤ ቀጥሎ ደግሞ ለእያንዳንዱ የፕሪሚዬር ሊግ ክለብ ማሳወቅ ግዴታ መሆኑን ያስረዳሉ።

የፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ማኅበር ብዙውን ጊዜ ከአድማ ይልቅ ችግሮችን በውይይት መፍታት የሚሻ ድርጅት ነው የሚሉት ሮስ አድማ ያልተለመደ እንደሆነ ይናገራሉ።

የቀድሞው የእንግሊዝ እና የማንቸስተር ሲቲው ግብ ጠባቂ ጆ ሀርት ሁለቱ ተጫዋቾች አድማ ስለመምታት ያወሩት “እንዲሁ ጥያቄ ለመመለስ እንጂ የታሰበበት አይመስለኝም” ይላል።

በዩናይትድ ኪንግደም የሥራ እና አሠሪ ሕግ መሠረት አድማ መምታት ቀላል ነገር አይደለም የሚሉት የሕግ ባለሙያው፤ ነገር ግን ተጫዋቾቹ ሕጉን ካሟሉ አድማ የመምታት እና ያለመጫወት መብት እንዳላቸው ያስረዳሉ።

ምንም እንኳ አንድ ክለብ አድማ የመታን ተጫዋች ኮንትራት ጥሷል በሚል መክሰስ ቢችልም፤ ይህ እንዳልተለመደ የሚናገሩት ሮስ በአድማው ወቅት ግን ክለቦች ደመወዝ ላይከፍሉ እንደሚችሉ ይናገራሉ።

“አድማው ሕግን ያልተከለተ ከሆነ ግን ተጫዋቾች ሊቀጡ አሊያም ሊባረሩ ይችላሉ።”

ነገር ግን ማንቸስተር ሲቲ ሮድሪን ይቀጣል አሊያም ያባርራል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው የሚሉት ሮስ ክለቦች ተጫዋቾቻቸውን ሊደግፉ እንደሚችሉ ይገምታሉ።

ብዙውን ጊዜ ተጫዋቾች ክለቦች የሚገቧቸው ስምምነቶች ለተጫዋቹ አድማ አሊያም ሥራ አለመሥራት ወይም ደግሞ አልጫወትም የማለት መብትን የሚሰጡ አይደሉም።

የሊቨርፑሉ ግብ ጠባቂ አሊሰን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ተጫዋቾች በቂ እረፍት ያገኛሉ? ገንዘብ ቢቀነስባቸውስ?

የቢቢሲ ስፖርት ፀሐፊው ሳይመን ስቶን በዘመናዊ እግር ኳስ አድማ ያልተለመደ ነው፤ በቅርቡ የምናየውም አይመስለኝ ይላል።

ነገር ግን የትኛው ውድድር በዚህ የአድማ ጉዳይ ዒላማ ሊሆን ይችላል? ሲል ይጠይቃል። ፕሪሚዬር ሊግ? ኢኤፍኤል ዋንጫ (ካራባዎ) ወይስ ቻምፒዮንስ ሊግ?

ምንም እንኳ ሮድሪ በዓመት ከ60 በላይ ጨዋታዎችን እያደረገ ቢሆንም በአውሮፓ ውድድሮች ላይ የማይሳተፉ አሊያም በአገር ውስጥ ውድድር ብዙ የማይዘልቁ ክለቦች በዓመት ቢበዛ 40 ጨዋታ ነው የሚያደርጉት።

በዚህ ምክንያት ሳይመን ተጫዋቾች የጋራ መግባባት ላይ ደርሰው አድማ ይመታሉ ብሎ አያምንም።

ተጫዋቾቻቸው በቂ እረፍት እያገኙ እንዳልሆነ የማይክዱት የሳውዝአምፕተኑ አሠልጣኝ “ከእግር ኳስ ውጪ ሕይወት የላቸውም” ይላሉ።

የቀድሞው የሲቲ ግብ ጠባቂ ጆ ሀርትም በዚህ ይስማማል። ነገር ግን ዘመናዊው እግር ኳስ ተጫዋቾች ያላቸውን ሁሉ አውጥተው ሜዳ ላይ እንዲያሳዩ የሚጠይቅ መሆኑን ይናገራል።

እርግጥ ሮድሪም ሆኑ ሌሎች ተጫዋቾች የጨዋታ ጊዜው ተቀንሶ በተመሳሳይ ደመወዛችሁ ቢቀነስ ተብለው አልተጠየቁም። ለዚህ ጥያቄ ምላሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል አይደለም።

ያም ሆነ ይህ የሮድሪ እና አሊሰን አስተያየት የሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኗል። በማኅበራዊ ሚድያዎች አስተያየታቸውን እየሰጡ ያሉ እግር ኳስ ተመልካቾችም ለሁለት የተከፈሉ ይመስላሉ። ግማሹ “ይህ ሁሉ ብር የሚከፈላቸው ለዚህ ነው” ይላሉ። ሌሎች ደግሞ በተጫዋቾቹ ሐሳብ ይስማማሉ።