አውስትራሊያዊው የሆኪ ተጫዋች በኦሊምፒክ ለመሳተፍ ሲል ጣቱን አስቆረጠ

ማት ዳውሰን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አንድ የአውስትራሊያ የሆኪ (የገና ጨዋታ ዓይነት ስፖርት) ተጫዋች በፓሪስ ኦሊምፒክ ለመወዳደር ሲል የጣቱን የተወሰነ ክፍል እንዲቆረጥ ማስደረጉ ተነገረ።

ማት ዳውሰን ከሁለት ሳምንት በፊት ፐርዝ ውስጥ ቡድኑ ልምምድ በሚያደርግበት ወቅት የቀኝ እጁ ጣት ክፉኛ ከመሰበሩም በላይ ከቀዶ ጥገናው ለማገገም ወራትን ይወስድ ነበር ተብሏል።

የ30 ዓመቱ ተጫዋች ግን ለሦስተኛ ጊዜ በኦሊምፒክ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ሲል ጣቱ መገጣጠሚያው ላይ እንዲቆረጥ መወሰኑ የቡድን አጋሮቹን እና አሠልጣኙን አስደንግጧል።

ጉዳት ከደረሰበት ከ16 ቀናት በኋላም ቅዳሜ ዕለት አርጀንቲናን ሲገጥሙ አውስተራሊያን ወክሎ ወደ ሜዳ ይመለሳል።

ዳውሰን ጉዳቱ በጣም መጥፎ ከመሆኑ የተነሳ ጣቱን በመልበሻ ክፍል ውስጥ ሲያየው ራሱን ስቶ እንደነበር ለመገናኛ ብዙኃን ተናግሯል። በፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ የመሳተፍ ህልሙ ያከተመም መስሎት ነበር።

በአስቸኳይ ከቀዶ ህክምና ሐኪም ጋር ተማከረ። በቀዶ ህክምና ጣቱን ለማስተካከል ቢሞከር ረዥም ያለ የማገገሚያ ጊዜ ከማስፈለጉም በላይ ሙሉ በሙሉ እንደበፊቱ ላይሆን ይችላል ተባለ። ከተቆረጠ ግን በ10 ቀናት ውስጥ ተመልሶ መጫወት እንደሚችል ተነገረው።

ዳውሰን ምንም ዓይነት “ፈጣን ውሳኔ” እንዳይወሰን ባለቤቱ ብታስጠነቅቀውም ባገኘው “መረጃ ተደገፎ” ውሳኔውን የዚያኑ ዕለት ከሰዓት በኋላ ማሳወቁን ተናግሯል።

“በስፖርቱ ያለኝ ጉዞ እየተጠናቀቀ እንጂ እየጀመረ አይደለም። ማን ያውቃል ይህ መጨረሻዬ [ኦሊምፒክ] ሊሆን ይችላል። አሁን በጥሩ አቅም መሳተፍ እንደምችል ከተሰማኝ ማድረግ ያለብኝ እሱን ነው” ሲል ለፓርሌዝ ቫውስ ሆኪ ፖድካስት ተናግሯል።

“የጣቴን ጫፍ መቆረጥ ከሆነ መክፈል የነበረብኝ ዋጋ፤ ይህንን ነው የማደርገው” ብሏል።

የቡድኑ አምበል የሆነው አራን ዛሌቭስኪ በበኩሉ ውሳኔው በቡድኑ ዘንድ ድንጋጤን ቢፈጥርም ዳውሰንን ደግፈዋል ሲል ገልጿል።

“በእርግጥ ምን እንደምናስብ አናውቅም ነበር። ሆስፒታል ሄዶ ጣቱን እንደቆረጠ ሰማን። ይህም በጣም አስገራሚ ነገር ነው። በኦሊምፒክ ለመሳተፍ ሰዎች እጅ፣ እግር እና ጣት እንደሚያጡ አውቃለሁ” በማለት በፓሪስ በተደረገ መግለጫ ላይ ተናግሯል።

“በከፍተኛ ደረጃ ለመወዳደር ስትመርጥ እና መስዋዕትነት ስትከፍል ይህ ቀላል ውሳኔ ነው።”

አሠልጣኝ ኮሊን ባች በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ዳውሰን ከቡድኑ ጋር ልምምድ መጀመሩን ተናግረዋል።

“ማት ክብር ይገባዋል። እሱ በፓሪስ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ቆርጧል። እኔ ይህንን ስለማድረጌ እርግጠኛ አይደለሁም፤ እሱ ግን አድርጎታል። በጣም ጥሩ ነው” ሲሉ ለአውስትራሊያ ሰቭን የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ዳውሰን ከባድ ጉዳት ሲያስተናግድ የመጀመሪያው አይደለም። ከ2018ቱ የኮመንዌልዝ ጨዋታዎች በፊት በሆኪ ዱላ ከተመታ በኋላ የዐይን ብርሃኑን ሊያጣ ተቃርቦ ነበር።

ሆኖም በውድድር ተሳትፎ ወርቅ አግኝተዋል። በቶኪዮ ኦሊምፒክ ደግሞ ከቡድኑ ጋር የብር ሜዳሊያ ማሳካት ችሏል።