በሶማሊ እና ኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ግጭት ነዋሪዎች መጎዳታቸውን ኢሰመኮ ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, ehrc
በሶማሊ እና በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይሎች መካከል በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ በተከሰተ ግጭት ምክንያት በሰዎች ላይ የደረሰው የሞት እና የአካል ጉዳት አንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።
የሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ በሆነው እና ከባቢሌ አቅራቢያ በሚገኝ ስፍራ ሰኞ መስከረም 07/2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ እና በሶማሊ ክልል የፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት በአካባቢው የተጠለሉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በክልሎቹ ኃይሎች መካከል በተከሰተው ግጭት ቆሎጂ በሚባለው የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ “ቢያንስ ስድስት ተፈናቃዮች ተገድለዋል፣ በርካታ ሰዎች ቆስለዋል” ያለው ኮሚሽኑ፣ በተጨማሪም በሌሎች የአካባቢው ሲቪል ሰዎች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱን ገልጿል።
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በግጭቱ ሳቢያ ቀደም ሲል ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለዓመታት በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ “የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ለሞት እና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸው አሳሳቢ ነው” ብለዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ያጋጠመውን ይህንን ግጭት በተመለከተ ኢሰመኮ ተጎጂዎችን፣ የቆሎጂ መጠለያ ሠራተኞችን፣ የሆስፒታል ባለሞያዎችን እና የክልሎቹን የፀጥታ ኃይሎች ማነጋገሩን አመልክቷል።
ስለተከሰተው ግጭቱም ሆነ ስለደረሰው ጉዳት የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የኦሮሚያ እና የሶማሊ ክልሎች አስካሁን ያሉት ነገር የለም።
ኢሰመኮ ግጭቱን በተመለከተ ሰኞ መስከረም 21/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ ሁለቱ ክልሎች ለተከሰተው ግጭት ምክንያት ለሆኑ ጉዳዮች ሰላማዊ መፍትሔ በጋራ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም ክልሎቹ ለግጭቱ ትኩረት ሰጥተው የነዋሪዎችን እና የተፈናቃዮችን ደኅንነት በዘላቂነት የማረጋገጥ ሥራ እንዲሠሩ፣ ለደረሰው ጉዳት ተጎጂዎችን እንዲካሱ እንዲሁም የሚጠበቅባቸውን ባለማድረግ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ባደረጉ የፀጥታ ኃይሎች ላይ ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ያስፈልጋል ብሏል።
ኢሰመኮ በመግለጫው ለዚህ ለሰዎች ሕይወት መጥፋት እና ጉዳት እንዲሁም መፈናቀል ሰበብ ለሆነው ግጭት መነሻው ምክንያት ምን እንደሆነ ያለው ነገር የለም።
የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ ጭምረውም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በአካባቢው በተፈጠረው ግጭት ወቅት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደነበረባቸው በመጥቀስ አስፈላጊው ተግባር አለመከናወኑን አመልክተዋል።
በሶማሊ እና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባበቢዎች በተለያዩ ጊዜያት ግጭቶች ያጋጠሙ ሲሆን፣ ከነዋሪዎች በተጨማሪ የየክልሎቹ የፀጥታ ኃይሎች በግጭቶቹ ውስጥ መሳተፋቸው ሲዘገብ ቆይቷል።
ከአምስት ዓመታት በፊት በተመሳሳይ በክሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረ ግጭት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለው ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ተከስቶ እንደነበረ ይታወሳል።












