የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ እስረኞች የረሃብ አድማ መተዋል መባሉ ስጋት እንደፈጠረባቸው ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ

አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና ዶ/ር ካሳ ተሻገር
የምስሉ መግለጫ, አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና ዶ/ር ካሳ ተሻገር

በአማራ ክልል የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ተይዘው አዋሽ አርባ በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ በእስር ላይ የሚገኙት የምክር ቤት አባላት “የረሃብ አድማ ላይ ናቸው” መባሉ ስጋት እንደፈጠረባቸው ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ።

በአስር ላይ የሚገኙ በፌደራል መንግሥቱ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በአማራ ክልል ምክር ቤቶች አባላት ቤተሰቦች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ታሳሪዎቹ ያሉበትን ሁኔታ ባለማወቃቸው ደኅንነታቸው አሳስቧቸዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ዶ/ር ካሳ ተሻገር እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ዩሐንስ ቧያለውን ጨምሮ ሌሎች “የፖለቲካ” እስረኞች ከዛሬ መስከረም 21/2016 ዓ.ም. ጀምሮ የረሃብ አድማ መምታታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተጋርቷል።

በእጅ ተጽፎ የተጋራው ይህ ደብዳቤ እስረኞቹ “በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን በደል፣ በአዋሽ አርባ የሚደርስባቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በካምፑ ውስጥ የሚደርስባቸውን ማንነት ተኮር በደል እንዲሁም እስካሁን ፍርድቤት አለመቅረባቸውን” በመቃወም የረሃብ አድማ እንደመቱ ይገልጻል።

እስረኞቹ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ጀምሮ ስለሚገኙበት የጤንነት እና አያያዝ ሁኔታ በውል እንደማያውቁ የገለጹ የታሳሪ ቤተሰቦችም እነሱን በሚመለከት በማኅበራዊ ሚዲያ የተሰራጨው መረጃ ጭንቀት እንደፈጠረባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አዋሽ አርባ አካባቢ በሚገኘው የአገር መከላከያ ሚኒስቴር የምዕራብ ዕዝ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ካምፕ ውስጥ የምክር ቤት አባላቱን ጨምሮ 53 ታሳሪዎችን እንደጎበኘ መግለጹ ይታወሳል።

ከታሳሪዎቹ መካከል ጋዜጠኞች እና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትም ይገኙበታል።

ኢሰመኮ በዚህ ሪፖርቱ ብዙዎቹ ታሳሪዎች የአማራ ብሔር ተወላጅ እና የኦርቶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች መሆናቸውን፣ ለእስር የበቁትም በማንነታቸው ምክንያት መሆኑን እንደሚያምኑ እንደገለጹለት በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።

ወደ አዋሽ አርባ ከመወሰዳቸው በፊትና በቁጥጥር ሥር በሚውሉበት ወቅት ብሔር ተኮር ስድብ፣ ማጉላላት፣ ዛቻ እንደደረሰባቸው፤ ሆኖም በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከሆኑ በኋላ የተፈጸመ ድብደባ ወይም አካላዊ ጥቃት አለመኖሩን ገልጸውልኛል ብሏል ኮሚሽኑ።

ፖሊስ በበኩሉ የእስረኞቹ አያያዝ ሰብአዊ መብታቸውን የጠበቀ መሆኑን፣ ሕክምና በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ይህንኑ እንደሚያመቻች እና በቤተሰባቸው እንዲጎበኙ እንደሚያደርግ ገልጾልኛል ብሎ ነበር ኢሰመኮ።

ቤተሰቦቻቸው ግን እስረኞቹን በአካል ለመጎብኘት ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ ቢያቀርቡም አስካሁን ፈቃድ እንዳላገኙ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የአቶ ክርስቲያን ታደለ ባለቤት ናርዶስ አዲሴ፣ “ባለቤቴ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከተወሰደበት ነሐሴ 15/2015 ዓ.ም. በኋላ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርት እስካወጣበት ጊዜ ድረስ የት እንደተወሰደ አላውቅም ነበር” ብለዋል።

ሆኖም እዚያ መወሰዳቸው ከተገለጸ በኋላ አንድ ሦስት ጊዜ በስልክ እንዳገኟቸው፤ ነገር ግን ስላሉበት የጤንነት ሁኔታ በቂ መረጃ አለማግኘታቸውን፣ በአካል ለመጎብኘት ያቀረቡት ጥያቄም ምላሽ አለማግኘቱን ተናግረዋል።

“ቀድሞውንም ካለባቸው ከፍተኛ የጨጓራ ህመም ጋር ተደማምሮ በአካባቢው ያለው ከፍተኛ ሙቀት፣ በዚህም ላይ የረሃብ አድማ አድርገዋል መባሉ ጭንቀት ውስጥ ከቶናል” ብለዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል ሆኑት አቶ ዩሐንስ ቧያለው ባለቤት ሄዘር ሙሰማ በበኩላቸው ባለቤታቸው ወደ አዋሽ አርባ መወሰዳቸው ከተነገረ በኋላ በስልክም ሆነ በአካል አግኝተዋቸው እንደማያውቁ ገልጸዋል።

“ቢያንስ እንደሌሎች ቤተሰቦች በስልክ እንኳን ድምጹን ለመስማት ፌደራል ፖሊስ ገብቼ ብጠይቅም ‘ጠብቂ ይደውልልሻል’ ከሚል መልስ ውጪ ሌላ ነገር አላገኘሁም” ብለዋል።

በምን ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ባላወቁበት ሁኔታም የረሃብ አድማ መትተዋል መባሉ የበለጠ ስጋት እንደፈጠረባቸውም ገልጸዋል።

“በድብቅ አዲስ አበባ መጥተው መታከማቸውን ሰምተናል”

የአቶ ዩሐንስ ቧያለው ባለቤት የሆኑት ሄዘር፣ ባለቤታቸው እንደታመሙ የሚወጡ መረጃዎችን እንደሚሰሙ እና መላ ቤተሰቡ በጭንቀት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ባለቤታቸው ቀድሞውንም የከፋ የጨጓራ ህመም እንዳለባቸውና ያገኙትን ምግብ መመገብ እንደማይችሉ የሚናገሩት ሄዘር፣ ከቤተሰብ በብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው ብለዋል።

እስረኞቹ ወደ አዋሽ አርባ መወሰዳቸው በኢሰመኮ ሪፖርት ከተገለጸ በኋላ፣ ለሕክምና አዲስ አበባ መጥተው እንደነበር መስማታቸውንም ሄዘር ጨምረው ተናግረዋል።

“ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ገብተዋል ተብሎ እዚያ ሄድን። እዚያ የሉም ተባለ። ፌደራል ፖሊስ ናቸው ተባለ። እዚያም ሄድን። በኋላ አንድ የፌደራል ፖሊስ አባል ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ አስገብተው ሕክምና ሲሰጧቸው እንደነበር እና ወደ አዋሽ መልሰው እንደወሰዷቸው ነገረን” ብለዋል።

ያሉበት ድረስ ሄደው በአካል ለመጎብኘት እንዲመቻችላቸው ኢሰመኮን እንደጠየቁ የሚያስታውሱት ሄዘር፣ ራሳቸው እስረኞቹ “ለቤተሰባችን ደኅንነት ስለምንሰጋ እንዲመጡ አንፈልግም” ማለታቸው እንደተገለጸላቸው አስረድተዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ “የባለቤቴን ድምጹን እንኳን መስማት አልቻልኩም” ብለዋል ሄዘር።

የአቶ ክርስቲያን ታደለ እና የዶ/ር ካሳ ተሻገር ቤተሰቦችም ተመሳሳይ ስጋት ነው ያላቸው።

የዶ/ር ካሳ ተሻገር ባለቤት የሆኑት ይቻሉ ዘላለም “ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ አልቻልንም። በስልክም ውስን ደቂቃ ስለሚሰጧቸው ስላሉበት ሁኔታ ጠይቀን መረዳት የምንችልበት ዕድል የለም” በማለት የባለቤቶቻቸው ጤና እና ደኅንነት እንደሚያሳስባቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“ክስም አልተመሰረተባቸውም፤ ፍርድቤትም አልቀረቡም”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሕገ መንግሥቱ መሠረት ያለመከሰስ መብት ያላቸው የምክር ቤት አባላቱ ከተያዙ ሦስት ወር ገደማ ቢሞላቸውም እስካሁን በምን ተጠርጥረው እንደተያዙ አልተገለጸም፤ ፍርድ ቤትም አልቀረቡም።

የዮሐንስ ባለቤት ሄዘር፣ ባለቤታቸው ነሐሴ 9/2015 ዓ.ም. በፀጥታ ኃይሎች ከባሕር ዳር ከተያዙ በኋላ ለሦስት ቀናት የት እንደተወሰዱ ሳያውቁ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እንደሆኑ መስማታቸውን አስታውሰው፣ ከዚያ በኋላ ግን ባለቤታቸውን በስልክም ሆነ በአካል አግኝተዋቸው እንደማያውቁ ተናግረዋል።

“በምን ምክንያት እንደተያዘ አናውቅም፤ ፍርድ ቤትም እስካሁን አልቀረበም” ብለዋል።

ከምክር ቤት አባላቱ ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉ፣ የምክር ቤት አባላቱ ያለ መከሰስ መብታቸው ሳይነሳ መታሰራቸው ሕጋዊ አይደለም በማለት አካልን ነጻ የማውጣት ክስ መሥርተው ጉዳዩን እየተከታተሉ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።

እንደ ጠበቃው ከሆነ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አሳሪው አካል ተጠርጣሪዎችን ፍርድ ቤት የማቅረብ ግዴታ የለበትም።

ሆኖም ፍርድ ቤት ቢያቀርባቸውም፣ ባያቀርባቸውም በእስር ላይ እስካሉ ድረስ በጠበቃ እንዲሁም በቤተሰባቸው የመጎብኘት መብት አላቸው ብለዋል።

በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ከተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ በመዲናዋ አዲስ አበባ እና በሌሎች አካባቢዎች ሕጋዊ ሥርዓትን ያልተከተሉ የጅምላ እስሮች አሁንም መቀጠላቸውን የሰብዓዊ መብት ተቋማት እየገለጹ ነው።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ባለፈው ሳምንት ባወጣው ሪፖርት የሚታሰሩ ሰዎች በተገቢው ጊዜ ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ፣ የታሰሩ ሰዎች የት እንዳሉ በቤተሰቦቻቸው እንደማይታወቅ መረዳት እንደቻለ አመልክቷል።