በአዲስ አበባ ከተማ ሕጋዊ ሥርዓትን ያልተከተሉ የጅምላ እስሮች ቀጥለዋል - ኢሰመጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአዲስ አበባ ከተማ ሕጋዊ ሥርዓትን ያልተከተሉ እና አንዳንዶቹም አስገድዶ የመሰወር ባህርይ ያላቸው የጅምላ እስሮች መፈፀም መቀጠላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) አስታወቀ።
የሰብዓዊ መብት ተቋሙ ትናንት ቅዳሜ መስከረም 12/ 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ በአማራ ክልል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ ጋዜጠኞችንና ያለመከሰስ መብት ያላቸውን የምክር ቤት አባላት ጨምሮ መጠነ ሰፊ የጅምላ እስሮች መፈፀማቸውን አስታውሶ፣ የሚመለከታቸው አካላት እነዚህን ከሕግ አግባብ ውጭ የተፈፀሙ እስሮች ለማስቆም እርምጃ ባለመውሰዳቸው አሁንም የጅምላ እስሮች ቀጥለዋል ብሏል።
ኢሰመጉ ከታሳሪ ቤተሰቦች አገኘኋቸው ባላቸው መረጃዎች በመዲናዋ በርካታ ሰዎች ያለአግባብ እንደታሰሩ ገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ የሚታሰሩ ሰዎች በተገቢው ጊዜ ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ፣ የታሰሩ ሰዎች የት እንዳሉ በቤተሰቦቻቸው እንደማይታወቅ መረዳት እንደቻለ በሪፖርቱ አመልክቷል።
ለእነዚህ እስሮች በከተማዋ የሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች እንደማቆያነት እንደሚያገለግሉ የደረሳቸውን መረጃ ለማረጋገጥም አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮን፣ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን፣አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን በደብዳቤ ቢጠይቅም ይህን ሪፖርት እስካወጣበት መስከረም 12/ 2016 ዓ.ም. ድረስ ምላሽ አለማግኘቱን አስረድቷል።
አንዳንድ የእስረኞች ማቆያዎች ለዚህ ተግባር ያልተቋቋሙ እና በንጽሕና ያልተያዙ በመሆናቸው ታሳሪዎች ለከፍተኛ የጤና ቀውስ መዳረጋቸውንም ኢሰመጉ በሪፖርቱ ገልጿል።
ባለፉት ሳምንታት ከቱሉ ዲምቱ ከሚገኝ የእስረኞች ማቆያ ሥፍራ ወጡ የተባሉና ታሳሪዎች ለጤና ቀውስ ተዳርገው የሚያሳዩ ምስሎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ተጋርተው ታይተዋል።
ምስሎቹ በቢቢሲ አልተረጋገጡም። በሥፍራው አለ ስለተባለው ሁኔታም ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልተቻለም።
ሆኖም የአማራ ማኅበር በአሜሪካ የተሰኘው ድርጅት ተጠሪዎች አንዱ የሆኑት ሆነ ማንደፍሮ ምስሎቹ ከቱሉ ዲምቱ የጅምላ እስር ቤት የወጡ ስለመሆናቸው መረጃ እንዳገኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ታሳሪዎቹ ያለአግባብ ተይዘው ይገኙበታል ባሉት ሥፍራም የጤና ቀውስ እንደተከሰተና እና ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ሕይወት ማለፉን አቶ ሆነ ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, AA CITY PRESS SECRETARY
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ከትናንት በስቲያ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ባወጣው መግለጫም፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም መጠነ ሰፊ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እና የሰላማዊ ሰዎች እስር የተስተዋለበት ነው ብሏል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የሰብዓዊ መብት አያያዝ መርሆዎችን የጣሱ ድርጊቶች እየተፈፀሙ ስለመሆኑ ጥቆማዎች ደርሰውኛል ብሏል።
በአዲስ አበባ ፣ በአማራ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል ዜጎች ባልፈፀሙትና ተጠያቂ በማይሆኑበት ወንጀል መታሰራቸውን፣ በጸጥታ አካላትም ድብደባዎች፣ንብረቶችን መቀማት፣ ማንገላታት እና ማዋከብ በስፋት መፈፀሙን ገልጿል።
በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ጅምር የፋብሪካ መጋዘኖች “ ማጎሪያ” ሆነው እያገለገሉ ነው ሲልም አብን በመግለጫው ከስሷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የተቋቋመው ጠቅላይ መምሪያ ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫም፣ ያዘጋጃቸው የማቆያ ቦታዎች 5 ብቻ መሆናቸውን የገለጸ ሲሆን፣ እነዚህ በኮምቦልቻ፣ በጎንደር፣ ባሕርዳር፣ ሸዋ ሮቢት እና አዋሽ አርባ እንደሆኑ አስታውቋል።
ሆኖም የእስረኞቹን አያያዝ እየተከታተለ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድ በአዲስ አበባም ጭምር የታሰሩ ሰዎች እንደሚገኙ ጠቁሟል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አዝመራው አንዴሞ ከሁለት ሳምንት በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈፃሚ ከሚሆንባቸው ቦታዎች ውጭ እስራቶች ተፈፅመዋል የሚል ጥቆማ እንደደረሳቸው ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በበኩሉ ባለፈው ሳምንት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ ክልል በሸገር እና ፍቼ ከተሞች እንዲሁም በአጠቃላይ በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ የማያውቀው የማቆያ ካምፕ እንዳሌለ አስታውቋል።
ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው መግለጫ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ገላን ክፍለ ከተማ በሚገኝ ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከል ውስጥ ተላላፊ በሽታ ተከስቶ 190 ሰዎች ሆስፒታል ገብተው የ3 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገልጿል።
ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች ተገድደው እንዲቆዩ በሚደረጉበት ‘ሲዳ አዋሽ’ ተብሎ በሚታወቅ አካባቢ በሚገኘው ማዕከል በተባይ የሚተላለፍ የተስቦ በሽታ ምክንያት፣ 190 ሰዎች ሆስፒታል ገብተው እንደነበረ እና 3 ሰዎች በጽኑ ታምመው ነበር ብሏል።
ኢሰመጉ በትናንቱ መግለጫው በአማራ ክልል ባለው ግጭት ተፈፅመዋል ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም አንስቷል።
በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት በክልሉ ሰብዓዊ ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማስከተሉን እንዲሁም በንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡን ያስታወሰው መግለጫው፣ ጥሪው ችላ በመባሉ በክልሉ ያለው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እየተባባሰ መጥቷል ብሏል።
በዚህም በርካታ ንጹሃን ሰዎች መሞታቸውን ፣ የንብረት ውድመት መድረሱን፣ በአካባቢው መንግሥት ባሰማራቸው የጸጥታ አካላት ከሕግ ውጭ የሚፈፀሙ ግድያዎች ስለመኖራቸውም ሪፖርቶች እንደደረሱት ገልጿል።
በመሆኑም በአዲስ አበባ የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት በከተማዋ የሚፈፅሙትን ሕግን ያልተከተለ የጅምላ እስር እንዲያቆሙና ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ ከመጠቀም እንዲቆጠቡ፣ ይህንን የሚፈፅሙ አካላትም በሕግ እንዲጠየቁ ኢሰመጉ ጠይቋል።
ከዚህም በተጨማሪ ያለ መከሰስ መብት ያላቸው የምክር ቤት አባላት በአስቸኳይ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ እና የአካልን ነጻነት መብታቸው እንዲከበር፣ የፌደራልና የአማራ ክልል ባለሥልጣናት የሰዎች በሕይወት የመኖር መብትን እንዲያከብሩ፣ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሥልጣንን ያለ አግባብ ለመጠቀም በር እንዳይከፍት አፈጻጸም በቅርበት እንዲከታተልና ቁጥጥር እንዲያደርግ፣ ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጠይቋል።
በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች መቀጠሉ እየተነገረ ነው።
ከሰሞኑ በምዕራብ ጎጃም ዞን ደምበጫ ከተማ ተፈፅመዋል በተባሉ የድሮን ጥቃቶች ቢያንስ 30 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች “የጦር መሳሪያ ደብቃችኋል አምጡ” በሚል በመንግሥት የጸጥታ አካላት ከፍርድ ውጭ ግድያዎች መፈጸማቸውንም ኢሰመኮ መስከረም 4/ 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ገልጿል
በክልሉ የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በመቋረጡ እንዲሁም ከሰሞኑ ተባብሶ የቀጠለውን ግጭት ተከትሎ በአንዳንድ አካባቢዎች የስልክ አገልግሎት በመቋረጡ ከአካባቢዎቹ መረጃ ለማግኘት አዳጋች ሆኗል።












