እንግሊዝ እና ፈረንሳይ መካከል የስደተኞች ጀልባ ሰጥማ ቢያንስ 6 ስደተኞች ሞቱ

የስደተኞች ጀልባ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከፈረንሳይ ወደ አንግሊዝ ለመሻገር በአነስተኛ ጀልባ ሲጓዙ የነበሩ ስደተኞች አደጋ ገጥሟቸው ቢያንስ 6ቱ ሕይወታቸው አለፈ።

የፈረንሳይ የባሕር ድንበር ጥበቃ ስደተኞችን የጫነችው ጀልባ ከፈረንሳይ ካሌ አቅራቢያ ባለው የባሕር ክፍል ላይ ችግር ያጋጠማት ቅዳሜ ጠዋት ነው ብሏል።

በጀልባዋ ተሳፍረው የነበሩት አብዛኛዎቹ የአፍጋኒስታን ዜጎች ቢሆንም የሱዳን ዜጎችም እንደሚገኙበት ተዘግቧል።

አደጋ ካጋጠማት ጀልባ ላይ የፈረንሳይ እና የእንግሊዝ የባሕር ድንበር ጥበቃ ሠራተኞች የ49 ስደተኞች ሕይወትን መታደግ መቻላቸውን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ አድራሻቸው ያልተገኙ ሁለት ስደተኞችን የማፈላለጉ ጥረት እንዲቆም ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

በአደጋው ሕይወታቸው ያለፉት በሙሉ በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወንዶች የሆኑ የአፍጋኒስታን ዜጎች ስለመሆናቸው የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ የአገሪቱን ባለስልጣን ጠቅሶ ዘግቧል።

የፈረንሳይ የባሕር ድንበር ጥበቃ ኃላፊዎች ከአቅም በላይ በርካታ ሰዎችን ጭና የነበረችው ጀልባ ችግር እንደገጠማት አንድ በአካባቢው እያለፈ የነበረ መርከብ ጥቆማ ከሰጠ በኋላ የፈረንሳይ የአደጋ ግዜ ሠራተኞች መሰማራታቸውን አስታውቀዋል።

የፈረንሳይ የሕይወት አድን ጀልባዎች በስፍራው ሲደርሱ ባሕር ውስጥ ሆነው የድረሱልን ጥሪ የሚያሙ ሰዎች ነበሩ ተብሏል።

በሕይወት አድን ስራው የተሰማራው ጄን-ፒዬር ፊኖት ጀልባዋ ከአቅሟ በላይ በመጫኗ ወደፊት መጓዝ አቅቷት ነበር ይላል።

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በዚህ ሳምንት ብቻ ስደተኞችን ከባሕር ላይ ያወጡት ይህ ለሰባተኛ ግዜ መሆኑን ጠቅሰው ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች የሚያዘዋውሯቸው ስደተኞች ቁጥር በመጨመሩ ሳቢያ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ጀልባዎችን እየተጠቀሙ ነው ብለዋል።

የፈረንሳይ ባለስልጣናት የስደተኞችን ማንነት ለማወቅ እንዲሁም ስለ ሕገ-ወጥ ጉዟቸው ዝርዝር መረጃ ለመሰብሰብ ለስደተኞቹ ቃለ መጠይቅ ማድረግ መጀመሩን ገልጿል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ቃል አቀባይ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ዘመድ ወዳጆች መጽናናትን እንመኛለን ካሉ በኋላ አደጋው ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ኢንግሊሽ ቻናል የሚባለውን የውሃ አካል በአስተኛ ጀልባ ማቋረጥ ምን ያክል አደገኛ እንደሆነ ያሳያል ብለዋል።

ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ ከ1ሺህ ያላነሱ ሰዎች ደቡባዊ እንግሊዝን ከሰሜን ፈረንሳይ የሚለየውን የውሃ ክፍል አቋርጠው እንግሊዝ መግባታቸውን አሃዞች ያሳያሉ።

ከእአአ 2018 ጀምሮ ከ100ሺህ ያላነሱ ስደተኞች ይህን የውሃ አካል አቋርጠው እንግሊዝ ገብተዋል።

የዩኬ መንግሥት የስደተኞችን ፍልሰት ለመቀነስ በሚል ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ አገሪቱ የሚደርሱ ሰዎችን ወደ ሌላ ሦስተኛ አገር አዘዋውሮ የጥገኝነት ጥያቄያቸውን በሦስተኛው አገር ሆነው እንዲከታተሉ አድርጋለሁ ብሏል።