የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ በአማራ ክልል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ውሳኔ ይሰጣል

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የፎቶው ባለመብት, hopr/fb

የምስሉ መግለጫ, የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

በእረፍት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን መርምሮ ለመወሰን ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ ያደርጋል።

በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት እና የፀጥታ መደፍረስ ከክልሉ መንግሥት አቅም በላይ በመሆኑ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ በቀረበው ጥያቄ መሠረት እንደ አስፋለጊነቱ በመላው አገሪቱ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በክልሉ ላይ መጣሉ ይታወቃል።

የአገሪቱ ከፍተኛው የሥልጣን አካል የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተደነገገበት ጊዜ በእረፍት ላይ ጊዜ በማወጁ፣ በሕጉ መሠረት በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ ውሳኔ መስጠት ይጠበቅበታል።

ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 በሚል በሚኒስትሮች ምክር ቤት በተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ለመወሰን ባለፈው ሳምንት የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባ፣ ለዛሬ ነሐሴ 8//2015 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ ጠርተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ከሰዓት በኋላ በሚያካሂደው አስቸኳይ ስብሰባው ላይ በአማራ ክልል ላይ የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርምሮ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።

በተጨማሪም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በምክር ቤት አባልነታቸው በቁጥጥር ስር ያለመዋል ሕጋዊ መብታቸው ሳይነሳ በቁጥጥር ስር በሚገኙት የምክር ቤቱ አባል ያለመከሰስ መብት ጉዳይ ላይም ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚችል አንድ የምክር ቤቱ አባል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ በቁጥጥር ስር ያለመዋል እና ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ አስቸኳይ አዋጁ በተደነገገበት ዕለት ተይዘው አሁንም ድረስ በእስር እንደሚገኙ ይታወቃል።

ይህ በእንዲህ እናዳለ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ለመወሰን አስቸኳይ ስብሰባ ለተጠራው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰብአዊ መብቶች ትንታኔ እና ምክረ ሐሳቦችን ማቅረቡን ከቀናት በፊት አሳውቋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚቆይበት ጊዜን ማሳጠር

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአስቸኳይ አዋጁ ላይ ለመምከር እና ለመወሰን በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ፣ በአዋጁ የተጣሉ ክልከላዎች እና ግዴታዎች፣ ለመንግሥት የተሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣንን እንዲያጤን ባቀረበው ምክረ ሃሳብ ጠይቋል።

በተጨማሪም የአዋጁ አስፈላጊነት፣ ተመጣጣኝነት እና ሕጋዊነት እንዲሁም አዋጁ ተፈጻሚ የሚሆንበት አካባቢ እና የጊዜ ወሰን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና የዳኞችን ያለምክር ቤቱ ውሳኔ አለመያዝ እና ያለመከሰስ ልዩ መብት እና ሌሎችም ሊገደቡ ስለማይችሉ መብቶች ጥበቃን አንዲመረመር ለምክር ቤቱ ሃሳብ አቅርቧል።

ኮሚሽኑ እንዳለው በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ውስጥ ተከስቶ የነበረው ችግር ተወግዶ መደበኛ እንቅስቃሴዎች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው መመለስ መጀመራቸው በመንግሥት በመገለጹ፣ ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያጸድቀው ከሆነ ተፈጻሚነቱ ከአንድ ወር ወይም ከተወሰኑ ሳምንታት እንዳይበልጥ ጠይቋል።

ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 ለስድስት ወራት የሚቆይ ነው። ነገር ግን የሁኔታዎች መሻሻልን በመመልከት በአጭር ጊዜ ቀሪ የሚደረግ ሲሆን፣ ያጋጠመው ችግር መፍትሄ ካላገኘ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲራዘም ሊደረግ ይችላል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚፈጸበት ቦታ እንዲወሰን

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት እና የፀጥታ ችግር ምክንያት አድርጎ የተጣለ ቢሆንም፣ ግን እንደ አስፈላጊነቱ በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ተፈጻሚ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።

ከዚህ አንጻርም ኢሰመኮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አካባቢያዊ ተፈጻሚነቱ “ልዩ አደጋው ተከስቶበታል በተባለው የአማራ ክልል ውስጥ ብቻ የተገደበ እንዲሆን” እንዲደረግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ምክረ ሐሳብ ጠይቋል።

በዚህም በአገሪቱን ሕገ መንግሥት እና በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች እና የሰብአዊ መብቶች መርሆዎችን መሠረት በማድረግ ለምክር ቤቱ ባቀረበው ትንታኔ፣ አዋጁ የሚጸድቅ ከሆነ “ለትርጉም አሻሚ የሆኑ እና ተለጥጠው በመተግበር ተገቢ ላልሆነ አፈጻጸም እና ለሰብአዊ መብቶች አደጋ ሊሆኑ የሚችሉ ድንጋጌዎች” ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል።

ኢሰመኮ ቀደም ሲል በአገሪቱ ውስጥ ተደንግገው በነበሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ተግባራዊነት ወቅት ባደረጋቸው ክትትል እና ምርመራ ወቅት የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውን አመልክቶ፣ አሁን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው ምክረ ሃሳብም እንዲህ አይነቶች የመብት ጥሰቶች እንዳደገሙ ለማድረግ ነው።

ኮሚሽኑ ጨምሮም ልዩ የሥራ እና የኃላፊነት ነጻነትን ከመጠበቅ አንጻር ለሚመነጩ ልዩ መብቶች እና ጥበቃዎች መታገዳቸው የምክር ቤት አባላት እና የዳኞችን ያለ ምክር ቤቱ ውሳኔ ያለመያዝ እና ያለመከሰስ መብቶችን ጭምር አላግባብ ለማገድ በር ይከፍታል ብሏል።

ይህም “በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ሊታገድ የማይችለውን የዳኝነት ዋስትና እና በነጻነት ላይ የተመሠረተ የፍትሕ አስተዳደርን የሚያግድ፣ እንዲሁም በተለይም በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ሊደረግ የሚገባውን የምክር ቤት የክትትል መርህን ተፈጻሚነት ሊያደናቅፍ የሚችል ነው” ሲል አሳስቧል።

የሚጠበቀው የምክር ቤቱ ውሳኔ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል ክልል የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በተመለከተ ያዘጋጀውን ይህንን ባለ 26 ገጽ ዝርዝር የሰብአዊ መብቶች ትንታኔ እና ዝርዝር ምክረ ሐሳቦች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡን ያሳወቀው ምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባ ሊያደርግ በተዘጋጀበት ጊዜ ነው።

ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል ውስጥ በታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ሲያጋጥም የቆየው ግጭት ክልሉን ከባድ ቀውስ ውስጥ የከተተው በሐምሌ ወር ማብቂያ ላይ ነበር።

የክልሉ መንግሥትም ያለውን ቀውስ እና ግጭት በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር አለመቻሉን በመግለጽ፣ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጎ የፌደራሉ ሠራዊት በክልሉ ውስጥ መሰማራቱ ይታወቃል።

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከሰኔ ወር ማብቃት በኋላ በየዓመቱ በእረፍት ላይ የሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕጉ መሠረት በሁለት ሳምንት ውስጥ መርምሮ ውሳኔ መስጠት ይጠበቅበታል።

በዚህም መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ አንድ ሳምንት ያለፈውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን መርምሮ ውሳኔ ለማሳለፍ ለአባላቱ የአስቸኳይ ስብሰባ ጥሪ ለዛሬ ሰኞ ነሐሴ 08/2015 ዓ.ም. ከቀኑ ስምንት ሰዓት አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም (ኢሰመኮ) ይህ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ከመደረጉ ቀደም ብሎ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ያዘጋጀውን የሰብአዊ መብቶች ትንታኔ እና ዝርዝር ምክረ ሐሳቦች ማቅረቡን አሳውቆ፣ ምክረ ሐሳቦቹን በጥንቃቄ አጢኖ ተግባራዊ እንዲያደርጋቸው ጠይቋል።