ለራስዎ ያለዎ ግምት አናሳ ነው? ‘ይህ አይገባኝም’ ብለው ያስባሉ? እነዚህን ስድስት መላዎች ይሞክሩ

አንዲት ሴት ደረጃ ወደላይ ስትወጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

“እስካሁን እንዴት እንዳላባረሩኝ አላውቅም። ለዚህ ሥራ እንደማልመጥን ይታወቃል። መቼም በዕድል ነው እዚህ ያለሁት። . . .”

ይህንን ዓይነት ንግግር ከራስዎ ጋር አድርገው ይሆናል። በሥራ ሕይወትዎ እንዲህ ዓይነቱን ስሜት አስተናግደው ያውቁም ይሆናል።

ይህ ስሜት የሚሰማዎ እርስዎ ብቻ አይደሉም። ‘ኢምፖስተር ሲንድረም’ ሊኖርብዎት ይችላል።

“ኢምፖስተር ሲንድረም ማለት ሰዎች ለራሳቸው ያላቸው ግምት ያነሰ ነው ማለት ነው። ሰዎች ምን ይሉኛል የሚል ፍራቻ አለባቸው። ይህ ነገር አይገባኝም ብለው ያስባሉ። ሰዎች ባስቀመጡኝ ቦታ አልተገኘሁም የሚል ጭንቀት ይይዛቸዋል።”

ይህን ትንታኔ ለቢቢሲ የሰጡት የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ዶሎሪስ ሊሪያ ናቸው።

ኑሮ ሳይንስ ያጠኑት ሌላኛዋ የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ማር ማርቲኔዜ ሪካርት ይህ ምልክት የሚታየው “የምንፈልገውን ነገር አውቀን ነገር ግን የምንፈልገው ነገር ሊሳካልን ሳይችል ሲቀር ነው። እንዲያውም ከምናስበው በታቸው ሆነን እንገኛለን።”

ይህ ደግሞ በተራው “ያለንን አቅም እንዳናውቅ ያደርገናል። ያሳካነው ነገር ቢኖር እንኳ ደስተኛ አንሆንበትም” ይላሉ በሳይኮሎጂ የዶክትሬት ድግሪ ያላቸው ኢሳቤል አራንዳ።

በእንግሊዝኛው ‘ኢምፖስተር ሲንድረም’ የምንለው ስሜት ያለባቸው ሰዎች ይህንን ስሜታቸውን ለማካካስ ከአቅማቸው በላይ ይሠራሉ፤ ይህ ደግሞ ጤናቸው ላይ ቀውስ ያመጣል። ወደ ጭንቀት እና ድባቴ ሊከታቸው ይችላል።

በአውሮፓውያኑ 1978 ኢምፖስተር ሲንድረም የሚለውን መጠሪያ ያወጡት የሥነ ልቦና ባለሙያዎቹ ፖሊን ሮዝ ክላንስ እና ሱዛን ኢሜስ ናቸው።

ይህ ስሜት ያለባቸው ሰዎች የአእምሮ በሽታ አለባቸው ማለት አይደለም። ነገር ግን ከልጅነታቸው ጀምሮ ያዳበሩት ቢሆንም ሊቀለበስ የሚችል ነው ይላሉ የዘርፉ ሰዎች።

ማንኛውም ሰው ይህ ስሜት ሊሰማው ይችላል። ነገር ግን በሴቶች ዘንድ እጅግ የተለመደ ነው።

ባለሙያዎች የሚሉት ይህ የሆነው ሞዴል የሚሆኑ ሰዎች በመጥፋታቸው፣ የፆታ መድልዎ እና በጭፍን አስተሳሰብ ምክንያት ነው። የትምህርት ሥርዓቱ ደግሞ ሴቶች ያነሰ ሥር እንዲሠሩ የሚያበረታታ በመሆኑ ነው ይላሉ።

“ለሥራው የምንመጥን መሆናችንን ለማሳየት ብዙ እንጥራለን” የሚሉት ሪካርት “ዘ ኢምፖስተር ሲንድረም” የተባለ አማካሪ ድርጅት አላቸው።

ሦስቱ የሥነ ልቦና ሙያተኞች ይህ ዓይነት ስሜት የሚሰማቸው ሰዎች የባለሙያ እርዳታ ማግኘት አለባቸው ይላሉ። ለዚህ መፍትሄ እነሆ በራሳችን ልንሞክራቸው የሚገቡ መላዎች፡

አንዲት ሴት ላፕቶፕ ስትጠቀም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

1. ችግሩን መለየት

እርግጥ ነው ይህን ምክር ማንም ሊለግሰን ይችላል። ባለሙያዎቹ ግን አትኩሮት ይሰጡታል። የትኛው ስሜታዊ ችግር የሚከፋው ከራሳችን ጋር ስለማንመክር ነው። ቁጭ ብሎ አስቦ ችግሩን መለየት እጅግ አስፈላጊ ነው የሚል ምክር ይለግሳሉ።

ለራሳችን የምንለው ነገር እና እንዴት ነው የምናደርገው የሚለው ወሳኝ ነው። “ለራሳችን በቂ ቦታ አንሰጥም፤ ለስኬታችን እራሳችንን ‘ጎበዝ’ ማለት አንችልም፤ ስኬት የሚገባንም አይመስልንም” ይላሉ አራንዳ።

ሪካርት ደግሞ “ለዚህ ስኬት አልገባም” የሚለው የሚጮህ ድምፅ በሕይወታችን ቢያንስ አንድ ጊዜ መምጣቱ አይቀርም። እርግጥ ነው ይህ ድምፅ አንዳንድ ጊዜ ሊጠቅመን ይችላል የሚሉት ሪካርት፤ ነገር ግን ወደፊት እንዳንጓዝ እንዳያግደን ልንጠነቀቅ ይገባሉ ባይ ናቸው።

“ይህ ችግር ከየት ነው የሚመነጨው የሚለውን ለይቶ መጋፈጥ እና እንዴት ልንቆጣጠር እንደምንችል ማወቅ ወሳኝ ነው” የሚሉት ዶሎሪስ ሊሪያ ናቸው።

2. ስኬትዎን ያስታውሱ

አንዳንድ ጊዜ የሆነ አንዳች የሚያስጨንቅ ጉዳይ ሲገጥም ነገሮችን የምናይበትን መነፅር ማስተካከል ተገቢ ነው። ይህ የሚጠቅመን ካለንበት ስሜታዊ ክስተት ወጥተን በእርጋታ በማሰብ ጠቃሚ ነገር ማድርግ እንድንችል ነው።

ዶሎሪስ ሊሪያ የሚመክሩት ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ስንሆን እንዴት ነው የተወጣነው የሚለውን ማሰብ አስፈላጊ እንደሆነ ነው።

አንዳንድ ጊዜ ያሳካናቸውን ነገሮች በጽሑፍ ማስቀመጥም እጅግ ጠቃሚ ነው ይላሉ።

ማር ራትክሊፍ ይህ መንገድ “የስኬት ዛፍ” ይሉታል። ያሳካናቸውን ነገሮች የረሳን ሲመስለን ይህን በማስታወስ ከራሳችን ጋር መታረቅ እንችላለን።

አንዲት ሴት መስታወት ስትመለከት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ስኬታችንን መለየት እና በእሱ ላይ እራስን መገንባት

3. ስኬትዎን ያጣጥሙ

“አንድ ነገር ሲሳካልዎ ያን ሳያጥጥሙ ወደ ሌላ ተግባር ይጓዛሉ። ስኬትዎን ለማጣጣም ጊዜ አይኖርዎትም። ለራስዎ ጊዜ አይሰጡም” ይላሉ ሪካርት።

ለዚህ ነው ስኬትን ማጣጣም አስፈላጊ ነው የሚሉት። አሁንን ይኑሩ፤ ከስኬትዎ ጋር ግንኙነት ይኑርዎት። ትንሽም ይሁን ትልቅ ስኬት፣ ስኬት ነው ያላሉ ባለሙያዋ።

“ምክንያቱም ያንን ለማሳካት ዋጋ ከፍለዋል፤ ደክመዋል። ስኬትዎን ይኑሩት። ዘና ይበሉ። ይህን ካላደረጉ ስኬትዎ እንደሌለ ነው የሚቆጠረው።”

“አደረግኩት! ደስ ብሎኛል፤ ከዚህ ሁሉ ድካም በኋላ ይገባኛል” ማለትን ይመክራሉ።

አክለውም “ያደረግነው ምንም ይሁን ምን ስኬት የሚገባን ሰዎች እንደሆንን ራሳችንን ልናስታውስ ይገባል” የሚል ምክር ይለግሳሉ።

ኢሳቤል አራንዳ በዚህ ይስማማሉ። ይህ ማለት “አንዳች ኃይል ይርዳን ማለት አይለም” የሚሉት የዘርፉ ሰዎች “የሚገባን እና ዋጋ ያለን” መሆናችንን ለራሳችን የምንናገርበት መንገድ ነው ባይ ናቸው።

4. ሌሎች ለእኛ ያላቸው አመለካከት

የኢምፖስተር ሲንድረም አንድ መገለጫ እኛ ለራሳችን ያለን አመለካከት እና ሌሎች ለእኛ ያላቸው አመለካከት መካከል ያለው ክፍተት ነው።

ለዚህ ነው “ራሳችንን በሌሎች መነፅር ማየት” ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው የሚሉት አራንዳ ናቸው።

ሌሎች ሰዎችን ጥያቄ ከመጠየቅ ባለፈ ሰዎች ስለእኛ ምን እንደሚሉ መዝግቦ ማስቀመጥ ጠቃሚ ነው ይላሉ። “ሰዎች ሲያደንቁን መዝገበን ማስቀመጥ አለብን። ሰዎች ስለእኛ ሥራ ያሉትን ነገር መርሳት የለብንም።”

አክለውም በሥራ ቦታችን የራስ መተማመን የማይሰማን ከሆነ አንድ ቀላል መላ ልጠቁም ይላሉ ዶሎሪስ፤ የሰዎችን አስተያየት መጠየቅ።

“ሰዎች አስተያየት እስኪሰጡን መጠበቅ የለብንም። ውስጣችን ጥርጣሬ ካለ ከመጠበቅ ይልቅ ወይ አለቃዎቻችን አስተያየት መጠየቅ እንችላለን።”

የሥራ ባልደረቦች ሲያጨበጭቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሥራ ቦታ የባልደረቦቻችንን አስተያየት በመጠየቅ ስጋታችንን መስወገድ

5. ከእኛ ምን ይጠበቃል?

በየትኛውም ዓይነት ግንኙነት ከሁለቱም ወገን የሚጠበቁ ነገሮች አሉ። የሥራ ቦታ ግንኙነትም እንዲሁ ተመሳሳይ ነው። ከሁለቱም ወገን የሚጠበቅ ነገር አለ።

ወደ ኢምፖስተር ሲንድረም ስንመጣ የሚያስቸግረው የምንጠብቀው ከሥራቸን ሳይሆን ከራሳችን መሆኑ ነው።

ይህ ሚዛናዊ ሊሆን ይገባል።

“ለዚህ ሥራ አሊያም ቦታ ብቁ አይደለንም ሲባል ምን ማለት ነው? ራሳችንን እንዴት ነው የምናየው? ያለንበትን ቦታ እንዴት ነው የምንመለከተው?”

ባለሙያዎቹ እንደሚመክሩት ከራሳችን የምንጠብቀው ነገር ልክ ያጣ አሊያም የማይሆን መሆኑን ማወቅ አለብን። ይህ ከሆነ የስኬት ፍራቻ ቢያድርብን የሚገርም አይሆንም። አንድ ቀላል ምሳሌ እንውሰድ፣ ዛሬ ልምምድ ጀምረን በአራት ወር ጊዜ ውስጥ ማራቶን መሮጥ አንችልም።

ይህ ሲሆን ከእኛ በላይ ያለ ሰው ከእኛ ምንድነው የሚጠበቀው የሚለውን ሊያሳወቀን ይገባል።

ደስተኛ ሴት ስልኳን እያየች ፈገግ ስትል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በራስ መተማመናችንን በመገንባት ስኬታችንን አስተማማኝ ማድረግ እንችላለን

6. ራስን መንከባከብ እና አዘኔታ

ራስን መንከባከብ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን የዘርፉ ሰዎች ያሳስባሉ።

ስፖርት ለዚህ አጋዥ ሊሆን ይችላል። “ስሜታችንን ለመቆጣጠር ሊያግዘን ይችላል። ነገር ግን ግዴታ ጂም መግባት አለብን ማለት አይደለም። እንቅስቃሴ ማድረግ በራሱ መልካም ነው። ‘ዎክ መብላት’ አሊያም መደነስ ሊሆን የችላል” ይላሉ ሊሪያ።

ያም ሆነ ይህ እኛን ሊያረጋጋን የሚችል አንቅስቃሴ መልካም መሆኑንም ያስታውሳሉ።

“ረጋ፤ ዘና እንድንል የሚያግዙንን ዘዴዎችን መቀየስ። ስፖርት፣ መዝፈን፣ መደነስ፣ ከምናምነው ሰው ጋር ማውጋት ሊሆን ይችላል።”

ከሥራ ተላቀን ከቤተሰብ እና ከጓደኞቻችን ጋር ጊዜ ማሳለፍ ጥሩ ነው።

ሊሪያ ሁሌም ልናደርጋቸው የምንችላቸው ቀለል ያሉ ተግባራትንም ይመክራሉ።

“ሕይወት ከባድ ሊሆን ይችላል። ሥራም ሊከብደን ይችላል። ነገር ግን አንዳንድ ቀላል ተግባራት ከጭንቀት ሊገላግሉን ይችላሉ።”

ሁሌም ትችት ከሚሰነዝርብን ድምፅ በመራቅ በራስ መተማመን ማዳበር ይቻላል። “ለራሳችን አዘኔታ ሊኖረን ይገባል” ይላሉ ማር ማርቲኔዝ ሪካርት።

“አዘኔታ ልናዳብር ግድ ነው። ራሳችንን ፍቅር በተሞላበት መንገድ ማየት አለብን።”