በኮሮናቫይረስ ዘመን ቤት ተዘግቶ መዋል እርግዝናን እንደቀነሰ ጥናት አመለከተ

ወረርሽኙ እርግዝና እንዲጨምር ምክንያት አልሆነም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ብዙዎች የእንቅስቃሴ ገደብ እርግዝናን እንደጨመረ ገምተው ነበር

በኮሮናቫይረስ ጊዜ ቤት ተዘግቶ መዋል የወሊድ ምጣኔን እንደቀነሰ አንድ ጥናት አመለከተ። 

በአውሮፓ ኮሮናቫይረስ ያስከተለው ቤት ተቀምጦ መዋል እርግዝና እንዲጨምር አላደረገም ተባሏል። 

በአውሮፓ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉ ምናልባትም የወሊድ ምጣኔን ሳይቀንሰው አልቀረም። 

ይህንኑ የተመለከተ አንድ ጥናት በጥር 2021 እና ከአንድ ዓመት በፊት በአውሮፓ የነበረን የወሊድ ምጣኔ በማወዳደር ምን እንደተፈጠረ ለመረዳት ሞክሯል። 

ይህ ጥናት እንዳመላከተው ዜጎች ቤት በዋሉበት ዓመት እርግዝና ይጨምራል ተብሎ ቢታሰብም በተቃራኒው ሆኗል።

ምክንያቱም ከ10 ወራት በኋላ የወሊድ ምጣኔ በ14 እጅ ቀንሶ ታይቷል። 

ይህ ጥናት ደረስኩበት እንደሚለው ሰዎች ቤት ለመዋል በተገደዱበት ወቅት የእርግዝና መጡን የቀነሰው በአንዳንድ ጥናቱ በተደረገባቸው አገሮች ነው።

ይህ አነስተኛ የወሊድ ምጣኔ በተለይ ደህየት ባሉና የጤና መሠረታቸው ዝቅ ባሉ የአውሮፓ አገራት ይበልጥ ጎልቶ ታይቷል።

ሉቲኒያና ሮማኒያ በዚህ ረገድ የወሊድ ምጣኔያቸው በ28 እና በ23 እጅ ቀንሶ ታይቷል። 

የእንቅስቃሴ ገደብ አያስፈልገንም ያለቸው ስዊድን በአንጻሩ የወሊድ ምጣኔዋ አልቀነሰም። 

በምዕራብ አውሮፓ በዕድሜ የገፉ ዜጎች ቁጥር ከፍ ያለ ሲሆን የዚህ የወሊድ ምጣኔ መቀነስ አገራቱን ወደፊት ሊጎዳቸው ይችላል ይላል ጥናቱ። 

ይህ ጥናት ዘለግ ያለ ቤት የመዋል ገደብ በነበረባቸው አገሮች እርግዝና የበለጠ ቀንሶ ታይቷል ብሏል።

አጥኚዎቹ እንደሚገምቱት ምናልባት ወረርሽኙ ሲከሰት የነበረ የጤና ፍርሃት እርግዝና እንዳይፈጠር ምክንያት ሳይሆን አልቀረም።

በዚህ ጥናት የተሳተፉ አንድ ሐኪም እንደሚገምቱት ደግሞ ጥንዶች በተለይ በወረርሽኙ መጀመርያ ጊዜያት መጠጋጋትና መቀራረብ የሚያስከትለውን የጤና ጣጣ በመፍራት እርግዝናን ማዘግየት መርጠው ይሆናል።

እንዲሁም ወረርሽኙ በዓለም የምጣኔ ሃብት ላይ የሚያደርሰውን የረዥም ጊዜ ምስቅልቅል በመፍራት ጥንዶች እርግዝና እንዳይከሰት አድርገው ይሆናል። 

ኢንግላንእ እና ዌልስ ለምሳሌ የወሊድ ምጣኔያቸው ከወረርሽኙ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ13 እጅ ወርዶ ታይቷል። 

ከወረርሸኙ 10 ወራት በኋላ በታየው የወሊድ ምጣኔ ስኮትላንድ 14 ከመቶ፣ ፈረንሳይ 14 ከመቶ እንዲሁም ስፔን 23 ከመቶ ቀንሰዋል።

ይሁንና በመጋቢት 2021 የወሊድ ምጣኔ ቀድሞ ከወረርሽኙ በፊት ወደነበረበት ተመልሷል። ይህም የእንቅስቃሴ ገደብ መነሳቱን ተከትሎ የሆነ ነው።