በወንዶች እና በሴቶች አእምሮ መካከል ልዩነት አለ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አእምሯችንን በአጉሊ መነጽር ብናየው ከብዙ የደም ስሮች እና ውስብስብ የሆኑ የነርቭ መስመሮች ውጪ ምንም የምናየው ነገር አይኖርም።
ሆኖም ግን አእምሯችን የማንነታችን፣ የአስተሳሰባችን እና የስሜታችን ሲያልፍም በምክንያት እና በውጤት የማመናችን ምንጭ ነው።
በዚህ ደግሞ ሁለቱም ጾታዎች የሚታሙ አይደሉም። ግን የዘርፉ ምሁራን የወንድ እና የሴት አእምሮ አንድ ነው ወይስ የተለያየ ሲሉ ይጠይቃሉ።
አእምሯችንን ከራስ ቅላችን አውጥተን ለአንድ ሰው ብናሳይ የወንድ ይሁን የሴት የሚለይበት መንገድ በጣም አነስተኛ ነው።
ተመራማሪዎች የወንድ እና የሴት አእምሮ የተለያየ ነው ወይስ አንድ ዓይነት የሚለው ላይ አሁንም ድረስ እንደተሟገቱ አሉ።
ይህንንም ለማወቅ ከሚያደርጓቸው ምርምሮች አንዱ የአእምሮን ትኩረት የሚጠይቁ ተግባራት የሁለቱም ጾታዎች እንዲከውኑ ማድረግ ነው።
በዚህም በአጠቃላይ በዓለም ላይ በተሰሩ ምርምሮች ወንዶች ካርታ አንብበው የአንድን ቦታ አቅጣጫ በማወቅ እና ቦታውን በማግኘት ከሴቶች 50 በመቶ በልጠዋል።
በሌላ ወገን ደግሞ ሴቶች በተወሰነ ሰዓት ውስጥ የተለያዩ ተግባራትን በመፈጸም ከወንዶች ልቀው ተገኝተዋል።
ተመራማሪዎች ይህንን ለማረጋገጥ የሙከራ ተሳታፊዎችን በስምንት ደቂቃ ውስጥ የተለያዩ ሦስት ተግባራትን እንዲፈጽሙ ማዘዛቸውን ይጠቅሳሉ።
ተግባራቱም የሒሳብ ቀመርን ማስላት፣ የካርታ ተሰጥቷቸው የአንድን ሆቴል አድራሻ መለየት እና መስክ ውሰጥ የጠፋ መፍቻን ፈልጎ ማግኘት ነበሩ።
በእነዚህ ሦስት ተግባራት መካከል ደግሞ ትኩረታቸውን ለማሳት ስልክ ይደወልላቸዋል።
በዚህ ምርምር ላይ ሴቶቹ በተሰጣቸው ደቂቃ ውስጥ ተግባራቱን መፈፀም ችለዋል።
ወንዶች ግን አንድን ቦታን ለማግኘት የተጠቀሙትን የካርታ ማንበብ ችሎታ ተጠቅመው የጠፋውን ቁልፍ ማግኘት ላይ አልተሳካላቸውም።
ከዚህ በተጨማሪ የሰውን ስሜት በመረዳት በኩልም ስንመጣ ሴቶች የተሻሉ እንደሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ።

የፎቶው ባለመብት, SPL
ልዩነቱ በትምህርት ወይስ በተፈጥሮ?
በሁለቱ ጾታ መካከል ያለው ልዩነት የመጣው በጾታቸው የተነሳ ነው ብለን ከመደምደማችን በፊት በማስረጃ ማስደገፍ ይኖርብናል።
ይህንን ለመረዳት የሁለቱን ጾታዎች የአእምሮ መዋቅር ማወቅ እና መተንተን ጠቃሚ ነው።
ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ይህ ልዩነት በተፈጥሮ ከሆነ በአእምሯችን መዋቅር ላይ ልዩነት መታየት ይኖርበታል።
በአማካኝ የወንድ የአንጎል ክብደት የሴትን በ10 በመቶ ይበልጣል።
ሆኖም ግን የክብደት ልዩነቱ ከሰው ሰውም የተለያየ ሊሆን ይችላል።
ማለትም የአንድ ሴት አንጎል የሌላ ወንድን አንጎል ክብደት የሚበልጥበት ጊዜ ይኖራል ማለት ነው።
በተጨማሪም ወንዶች በአካል ሴቶችን ስለሚበልጡ አንጎላቸው ከፍ ብሎ ቢመዝን አያስደንቅም።
ሆኖም ተመራማሪዎች እንደሚስማሙበት ከሆነ ይህ የአንጎል ክብደት መለያየት ከችሎታ ወይም ከጉብዝና ጋር ምንም ግንኙነት የለውም
በሴት እና በወንድ አንጎላ መካከል የመዋቅር ልዩነት አለ የሚሉት ፕሮፌሰር ኬቨን ሚሼል በደብሊን ዩኒቨርስቲ የኒውሮ ባዮሎጂ ተመራማሪ ናቸው።
እንደ እርሳቸው ገለጻ ይህ ልዩነት፣ የጾታዎችን የመራባት ባህሪ የሚቆጣጠር ነው።
ከአእምሯችን ክፍል ሀይፖተላመስ ተብሎ የሚጠራው በሴቶች እና በወንዶች ላይ የተለያየ ነው።
ይህ ክፍል በአጉሊ መነጽር ሲታይ የወንዱ ከሴቷ በ6 በመቶ ይበልጣል።
ሆኖም ይህ የምናየው ልዩነት ከአንድ የወንድ ወይንም የሴት ባህሪይ ጋር በቀጥታ ላይገናኝ ይችላል ይላሉ ፕሮፌሰር ኬቨን።
ለምሳሌ ወንዶች የበላይነት ባህሪይን የሚያሳዩት ቀደምት አባቶቻችን ለመራባት (አጋራቸውን ለማግኝት) መወዳደር ስለነበረባቸው ሊሆን ይችላል።
በቀደመው ጊዜ ሴትን ለማግኘት ሌሎች ወንዶችን በልጠው መገኘታቸው የግድ ነበር።
ይህም አሁን ባለንበት ዘመናዊ ዓለም ውስጥ በተለያዩ ጉዳዮች ውስጥ ተገልጦ ልናይ እንችላለን።
በሌላ በኩል ከአንጎላችን መዋቀር ሂፖካምፐስ (hippocampus) የሚባለው የሴቷ የወንዱን ይበልጣል።
ይህ የጭንቅላት ክፍል አንድን ነገር ከማስታወስ ችሎታ ጋር የተያያዘ ቢሆንም፣ በሴት እና በወንድ ላይ ግን ምንም ልዩነት አላመጣም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀኝ እና ግራ የአእምሮ ክፍሎች
በአሜሪካ ፔንሲልቬኒያ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሚሰሩ የአእምሮ ሳይንቲስቶች እድሜያቸው ከ8 እስከ 22 ያሉ 900 የሴት እና የወንድ አንጎልን በማይክሮስኮፕ በመመልከት ውጤቱን በምስል ለማየት ሞክረዋል።
በዚህ ጥናት ላይ ከተሳተፉት መካከል አንዷ ዶ/ር ረጂና ቨርማን “ባገኘነው ውጤት ተደነቅን” ይላሉ።
የቀኝ እና የግራ የአእምሮ ክፍሎች የተለያዩ ተግባራት ያሏቸው ሲሆን፣ በሴት እና በወንድ መካከል ልዩነት ያሳዩ እንደሆን ነው ለማወቅ የሞከሩት።
ሌላኛው የዚህ ጥናት ባልደረባ በስተግራ የሚገኘው የአእምሮ ክፍል ቋንቋ የሚማረው እና መረጃን የሚያብላላ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር ሩበን ጉር።
ቀኙ የጭንቅላታችን ክፍል ደግሞ ከስሜታችን ጋር የተያያዙ ነገሮችን እንደሚከውን ጨምረው ያስረዳሉ።
በዚህ ሁኔታ የሴቶች አእምሮ ውስጥ የሚገኙት የነርቭ ስሮች ከቀኝ ወደ ግራ የተሳሰሩ ናቸው።
ይህም ሴቶች ከንግግር፣ ከስሜት እና ከትንተና የሚመጡ መረጃዎችን ከወንዶች በበለጠ እንደሚቀበሉ ያሳያል።
በዚህም የተነሳ ሴቶች ሁለቱንም የአእምሮ ክፍሎች እንደሚጠቀሙ ተመራማሪዎቹ መረዳታቸውን ይናገራሉ።
በወንዶች ጭንቅላት ውስጥ ደግሞ የነርቭ ሐረጎቹ በቀኙም በግራውም የአእምሮ ክፍል ውስጥ ከኋላ ወደፊት ነው የተሳሰሩት።
ፕሮፌሰር ሩበን እንደሚሉት ይህ የኋለኛው የጭንቅላት ክፍል ያየውን መረጃ ከአብላላ እና ከተነተነ በኋላ ወደ ፊተኛው የአንጎል ክፍል ይልካል።
የፊተኛው የአንጎል ክፍል ደግሞ ይህንን መረጃ በመጠቀም አንድን ነገር ለመተግበር ይወስናል።
ለምሳሌ ወንዶች ለአደን በሚወጡበት ጊዜ የሚያድኑትን አውሬ ሲያዩ ውሳኔ የሚወስኑት አእምሯቸው አሁን ባልነው መንገድ መረጃን ከተገነዘበ በኋላ ነው።
ይህ በሴቶች እና በወንዶች መካከል የታየው ልዩነት በወንድ እና በሴት ህጻናት መካከል ግን አልታየም።
ልዩነቱ መታየት የጀመረው ልጆች 13 ዓመት ከሞላቸው በኋላ ነው።
ስለዚህ ሳይንቲስቶቹ ይህ ልዩነት የመጣው በትምህርት ወይንም ደግሞ በአካባቢ ተጽእኖ ሊሆን እንደሚችል ይጠረጥራሉ።
በሌላ መልኩ በዩናይትድ ኪንግደም አስተን ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር ጊና ሪፖን፣ አእምሮ ላይ በወንዶች እና በሴቶች መካከል የሚታየው ልዩነት በአስተዳደግ እና ባህል ልዩነት የሚመጣ እንጂ የወንድ እና የሴት ጭንቅላት የሚባል ነገር የለም ይላሉ።
ፕሮፌሰሯ እንደሚሉት ጭንቅላታችን ከአካባቢው በሚወስደው ነገር የሚያድግ እና የሚሰለጥን ነገር ነው።
ስለዚህ በሴት እና በወንድ አእምሮ መካከል ከሚታየው ልዩነት ይልቅ በግለሰቦች መካከል፣ ጾታ ሳይለይ የሚታየው ልዩነት ይበልጣል።
በቅርቡ ተመራማሪዎች የማግኔቲክ ሬዞናንስ ኢሜጂንግን (ኤምአርአይ) በመጠቀም በሺህ የሚቆጠሩ የሴቶች እና የወንዶች አእምሮን ለማየት ሞክረዋል።
በዚህም የጥናት ውጤት በሁለቱ ጾታዎች መካከል የታየው ልዩነት በጣም ትንሽ ነው።
የወንድ አንጎል በክብደት ሲበልጥ የሴት የውጫዊ የአንጎል ክፍል ደግሞ ከወንዱ ወፍራም ሆኖ ተገኝቷል።
በአጠቃላይ በሴቶች እና በወንዶች አንጎል አወቃቀር ላይ ትልቅ ልዩነት ያገኙትም ይሁን፣ የሴት ወይንም የወንድ አንጎል የሚባል ነገር የለም ይላሉ።
የአእምሮ መዋቅር ከወንዶች ባህሪይ እና ችሎታ ጋር በቀጥታ ስለመገናኘቱ አሁንም መደምደሚያ ላይ አልደረሱም።












