የቻይና ቀጣዩ የሕይወት ዘመን ፕሬዝዳንት የሚሆኑት ሰው ማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
20ኛው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ጉባኤ እሁድ ጥቅምት 06/2015 ዓ.ም. ይጀምራል።
ጉባኤው ዢ ጂንፒንግ እስኪሞቱ ድረስ የቻይና ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል።
ይኸው ጉባኤ እንደ ፈረንጆቹ በ2018 አዲስ ደንብ ማጽደቁ አይዘነጋም።
አዲሱ ደንብ በቻይና አንድ ፕሬዝዳንት ለሁለት ጊዜ ብቻ ነው ማገልገል ያለበት የሚለውን ሕግ የሻረ ነበር።
ይህን ደንብ ‘የዕድሜ ዘመን መሪ’ በሚል ተክቶታል።
ዢ ጂንፒንግ በ2012 (እአአ) ወደ መንበሩ ከመጡ በኋላ ቻይና ይበልጥ አምባገነን ሆናለች።
መንግሥትን የሚተች እንደ ዋዛ አይታለፍም።
ይህ ደግሞ ከባለሥልጣናት እስከ ቢሊዮነር ዜጎች ለሁሉም ይሠራል። ሙሰኛን ይሰቅላል።
ዢ ጂንፒንግ ከታላቁ ሊቀመንበር ማኦ ወዲህ የተከሰቱ ክንደ ብርቱው ፕሬዝዳንት ሆነዋል።
ዢ ጂንፒንግ ለቻይና አዲስ ዓይነት ተሃድሶ (re-education) ያስተዋወቁ ሰው ናቸው።
የቻይና ሙስሊሞችን ካምፕ ውስጥ አቆይተው፣ ኢሰብአዊ ድርጊት ፈጽመው አድሰው ማውጣት ያስጀመሩ ናቸው ተብለው ይወቀሳሉ።
የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች እና የዓለም መንግሥታት በዚህ ጉዳይ ብዙ ቢጮኹም፣ ታላቁ ዢ ግን ከቁብም አልቆጠሯቸው።
ከዚህ ሌላ የቀድሞ የእንግሊዝን ቅኝ ግዛት የነበረችውን ሆንግ ኮንግን በብርቱ ክንዳቸው ጸጥ ለጥ አድርገው በሩቅ መግዛት የቻሉ ናቸው።
ራስ ገዝ ነኝ ለምትለው ታይዋን ጥሩ እንቅልፍ እንዳትተኛ ያደረጉ ፕሬዝዳንት ናቸው፤ ዢ ጂንፒንግ።
አሁን ላይ እርሳቸው በፓርቲያቸው ላይ ያላቸው ተጽእኖ ወደር የለውም።
በ2017 የእርሳቸው አስተሳሰብ እና ፍልስፍና በሕገ መንግሥት እንዲካተት አድርገዋል።
ከእሳቸው በፊት ይህን ማድረግ የቻሉት ታላቁ ማኦ ዜ ዱንግ ብቻ ነበሩ።
ከጭሰኝነት ወደ ፕሬዝዳንትነት
ዢ የተወለዱት በቤይጂንግ ነው፤ የትውልድ ዘመናቸው በፈረንጅ 1953 ነው።
የተወለዱት ከፍተኛ መደብ ካለው ቤተሰብ ነበር።
አባታቸው አብዮተኛ ነበሩ። የኮሚኒስት ፓርቲን ከመሠረቱት ሰዎችም አንዱ ነበሩ።
ከገዥ መደብ ቤተሰብ የተገኙ የቻይና ቤተሰብ ልጆች እንደ ልዑላን ነው የሚታዩት።
ይሁንና ድንገት ከከፍተኛ መደብ የተገኙት ሰው ሕይወታቸው የጭሰኛ ሆነ።
ይህም በ1962 ተጠራጣሪው ታላቁ ማኦ ተቀናቃኝ ሊሆኑኝ ይችላሉ ያሏቸውን ሰዎች ዘብጥያ እንዲወርዱ ባዘዙበት ወቅት ነበር።
ከእነዚህ መካከል ደግሞ የዢ ጂንፒንግ አባት ነበሩበት።
በ1966 በቻይና የባሕል አብዮት ተቀጣጠለ።
ከፍተኛ ነውጥም ተከተለ።
የዢ ቤተሰብ በዚህ ወቅት ፍዳውን በላ። እህታቸው ሞት ተፈረደባት።
ምንም እንኳ በኋላ ላይ የተገኙ መረጃዎች ሞቱ ተፈጻሚ ሳይደረግባት ሕይወቷን አጥፍታለች ቢሉም።
ይህ በዢ ጂንፒንግ ታላቅ እህት ታሪክ ላይ እምብዛምም ለውጥ አያመጣም።
በዚህ ጊዜ ዢ ገና ትንሽ ልጅ ነበሩ። ሆኖም የከፍተኛው መደብ ከሚማርበት ትምህርት ቤት ተባረሩ።
ገና በ15 ዓመታቸው ከቤጂንግ ወደ ተሃድሶ ትምህርት ቤት ተላኩ።
ከዚያም ወደ ግዞት ተወረወሩ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ይህን ክፉ ጊዜ ያሳለፉት በሰሜን ምሥራቅ ሊያንጊያ በሚባል መንደር የጉልበት ሥራ ለሰባት ዓመታት በመሥራት ነበር።
የአሁኑ ፕሬዝዳንት ለዓመታት ጭሰኛ ነበሩ የሚባለውም ለዚሁ ነው።
የሚደንቀው ግን ይህን ሁሉ መከራ ያበላቸውን ኮሚኒስት ፓርቲ ከመጥላት ይልቅ ተቀበሉት።
ፓርቲው ውስጥ አባል ለመሆን ብዙ ተጉ። አልተሳካላቸውም። ያልተሳካላቸው በአባታቸው ታሪክ የተነሳ ነበር።
በመጨረሻም በ1974 ፓርቲው ተቀበላቸው። በሒቤይ አውራጃ አስተዳደር ውስጥ መሥራት ጀመሩ።
በ1989 ዕድሜያቸው 35 ሲደርስ የደቡብ ፉጃን አውራጃ የኒንዴ ከተማ የፓርቲ አለቃ ሆኑ።
በ2008 ቻይና የበጋ ኦሊምፒክን በዢ አመራርነት አዘጋጀች።
ለዓለም ታላቅ አገር መሆኗንም አሳየች።
ዢ ጂንፒንግ ዓይን ውስጥ ገቡ።
የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የፖሊት ቢሮ አባል ሆኑ።
በ2012 ደግሞ የቻይና ፕሬዝዳንት ተደርገው በፓርቲው ተመረጡ።
ዢ እና ባለቤታቸው ፔንግ ሊዩዋን በሚዲያ ተወዳጅ ባልና ሚስት ሆነው መታየት ጀመሩ።
ይህ በቻይና ብዙም የተለመደ አልነበረም።
ባለቤታቸው ስመ ጥር ዘፋኝ ናቸው።
ዢ ጂንፒንግ እና ባለቤታቸው አንዲት ሴት ልጅ አለቻቸው።
ይሁንና ሐርቫርድ ከፍተኛ ትምህርቷን ስለመከታተሏ ከመታወቁ ውጭ ሌላ ስለርሷ ብዙ የሚታወቅ ነገር የለም።

የቻይና ሕልም
ቻይና አሁን ከአሜሪካ ቀጥላ የዓለማችን ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላት አገር ናት።
አሜሪካንን ትንፋሽ እያሳጣች ያለች አገር ናት።
በሁሉም መስክ ከፍተኛ ግስጋሴ እያሳየች ያለች አገር ናት።
ዢ ጂንፒንግ የቻይናን አዝጋሚ የምጣኔ ሃብት ዕድገትን ማርሽ የቀየሩ ሰው ናቸው።
የአካባቢ ብክለት ላይም ብዙ ጥረዋል። ቻይናን ከተቀረው ዓለም በመሠረተ ልማት የሚያስተሳስረው ‘ወጥ የመሠረተ ልማት ቀለበት’ ፕሮጀክት መሪ እና አስፈጻሚም ናቸው።
በእርሳቸው ዘመን የቻይና እጅ ረዝሟል።
በዓለም ላይ የቻይና ተጽእኖ እያየለ መጥቷል።
በደቡብ ቻይና ባሕር እና በተቀረው እስያ እንዲሁም በአፍሪካ ቻይና የኃያልነት ቦታን ይዛለች።
በከፊል ራስ ገዝ የምትተዳደረው ሆንግ ኮንግ በተቃውሞ ስትናጥ ቆይታ ብትቆይም ዢ ጸጥ ረጭ አድርገው በእንደራሴ እያስተዳደሯት ነው።
ታይዋንንም አስፈላጊ ከሆነ በኃይል እንጠቀልላታለን እያሉ እየዛቱባት ነው።
አሁን ትልቁ የቻይና ፈተና ከአሜሪካ ጋር የገባችው የንግድ ጦርነት ነው።
በ2020 ዢ ጂንፒንግ አዲስ የብሔራዊ ደኅንነት ሕግ አጽደቀው ፊርማቸውን አኑረውበታል።
በዚህ ሕግ መሠረት ማንኛውም ከውጭ ኃይል ጋር በትብብር የሚሠራ፣ ተቃውሞ አሰማለሁ የሚል ቡድን ወይም ዜጋ ላይ እስከ ዕድሜ ልክ እስር የሚያስፈርድ ነው።
ይህን ሕግ ተከትሎ የመብት ተሟጋቾች በስፋት ተለቅመው ታስረዋል።
በቀድሞዋ የብሪታኒያ ቅኝ ግዛት ሆንግ ኮንግ የነበሩትን ‘አፕል ዴይሊ’ እና ‘ስታንድ ኒውስ’ ጋዜጦችም ተዘግተዋል።
አዲሱ ማኦ እየተባሉ የሚጠሩት የ69 ዓመቱ ዢ ጂንፒንግ አሁን አንድ የሚቀራቸው ሥራ ቢኖር ታይዋንን በኃይል መጠቅለል ነው።
ይህ ደግሞ በሕይወት ዘመን ፕሬዝዳንትነታቸው የሚያሳኩት ተግባር ሊሆን ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።
ለማንኛውም ከሰሞኑ ሦስተኛውን የፕሬዝዳንትነት በትረ ሥልጣን ይረከባሉ፤ ቻይናንም ምናልባትም በሕይወት እስካሉ ድረስ ይመራሉ።
ለጊዜው የማይታወቀው እስከ መቼ ድረስ በሕይወት ይኖራሉ የሚለው ነው።
















