ከሥልጣን የተወገዱት ባሻር አል-አሳድ "ሶሪያን ጥዬ ለመውጣት አላሰብኩም ነበር" አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው የሶሪያ ፕሬዝዳንት ባሻር አል-አሳድ ወደ ሩሲያ ለመሸሽ "አላሰብኩም ነበር" ሲሉ ተናገሩ።
አሳድ ከስምንት ቀናት በፊት ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት መግለጫ ነው ሶሪያን ለመልቀቅ እንዳላሰቡ የተናገሩት።
የአሳድ መግለጫ የሶሪያ መንግሥት ቴሌግራም ገጽ ላይ ነው የወጣው። መግለጫውን አሳድ ስለመጻፋቸውና አሁን የቴሌግራም ገጹን ማን እንደሚቆጣጠረው ግልጽ አይደለም።
በመግለጫው አሳድ እንደሚሉት የሶሪያ መዲና ደማስቆ በአማጺያን እጅ ስትገባ ላታኪያ ግዛት ወደሚገኝ የሩሲያ ወታደራዊ መቀመጫ ተጉዘዋል።
ወደ አካባቢው የተጓዙት "የውጊያ ኦፕሬሽን" ለመቆጣጠር እንደሆነና እዚያ ሲደርሱ ግን የሶሪያ ወታደሮች "ቦታውን ጥለው እንደወጡ" ተናግረዋል።
ሄሜሚም የተባለው የአየር ኃይል ወታደራዊ መቀመጫ "ከፍተኛ ድብደባና የድሮን ጥቃት" እንደደረሰበትም ተናግረዋል።
በዚህ ወቅት ሩስያውያን በአውሮፕላን ወደ ሞስኮ ሊወስዷቸው እንደወሰኑም አሳድ በአረብኛና እንግሊዘኛ ባወጡት መግለጫ ተናግረዋል።
"ከወታደራዊ መቀመጫው መውጣት የሚቻልበት መንገድ ስለሌለ የወታደራዊ መቀመጫው አዛዦች ወደ ሩስያ በአፋጣኝ እንድወሰድ ከሞስኮ ተጠየቀ " ብለዋል።
"ይህ የሆነው ደማስቆ ከተያዘችና የመጨረሻው ወታደራዊ ይዞታ ከስሞ የመንግሥት ተቋማት ከተሽመደመዱ ከአንድ ቀን በኋላ ነው" ሲሉም አክለዋል።
"በዚህ ሁሉ ወቅት ሥልጣኔን ለመልቀቅ ወይም ጥገኝነት ለመጠየቅ አላሰብኩም። እንዲህ ያለ ዕቅድ በግለሰብም በፓርቲም ደረጃም አልነበረም" ብለዋል አሳድ።
"አገሪቱ በሽብር እጅ ስትወድቅ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ማድረግ የሚቻልበት ዕድል ጠፋ። ማንኛውም ቦታ ዓላማ ቢስም ሆነ" ሲሉም አክለዋል።
የሶሪያ ከተሞች በአማጺያኑ ኤችቲኤስ እጅ ሲገቡ አሳድ ለ12 ቀናት አልታዩም።
ሆኖም ግን ስለመሸሻቸው ጭምጭምታ ተሰማ። አማጺያኑ ደማስቆ ሲገቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳድን ማግኘት አልቻሉም ነበር።
አሳድ በሩሲያ ጥገኝነት እንደተሰጣቸው የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ናቸው ይፋ ያደጉት።
በይፋ ግን ማረጋገጫ አልተገኘም።
አማጺያኑ የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ላይ ናቸው።
ኤችቲኤስ ኃያል የሶሪያ አማጺ ቡድን ነው።
እአአ በ2011 ጃባት አል-ኑስራ በሚል ስም ሲመሠረት ከአል-ቃይዳ ጋር ትስስር ነበረው። በ2016 ግን ከአል-ቃይዳ ተነጥሏል።
የተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካና ዩኬ ሽብርተኛ ቡድን ብለውታል።
መሪው አቡ መሐመድ አል-ጃውላኒ በሚል ስም የሚታወቀው አሕመድ አል-ሻራ ነው።
የተለያዩ ሃይማኖቶችና ቡድኖችን ያቀፈ አስተዳደር ለመመሥረት ቃል ገብቷል።












