በዩክሬን የኦርቶዶክስ መነኮሳት የኪዬቭ ገዳምን ጥለን አንወጣም አሉ

ምንም እንኳን የዩክሬን መንግሥት በዋና መዲና ኪዬቭ ገዳም በመቶዎች የሚቆጠሩ ቀሳውስትን፣ መነኮሳትን እና ተማሪዎችን ለማስወጣት ቢያቅድም የኦርቶዶክስ ክርስትያን አባቶች እዚያው ታሪካዊ ገዳም ውስጥ እንደሚቆዩ ተናገሩ።

የፔቸርስክ ላቭራ ገዳም ባለፈው ዓመት ሩሲያ ወረራ ከፈፀመች በኋላ ከሞስኮው ፓትሪያርክ ተለይታ የወጣች የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መቀመጫ ናት።

የዩክሬን ባለሥልጣናት የተወሰኑት ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው የኃይማኖት አባቶች ሞስኮ ከሚገኘው ቤተክርስትያን ጋር ግንኙነት እንደፈጠሩ ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ቤተክርስትያኗ ግን ይህ ሐሰት ነው ብላለች።

የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንም ቀሳውስቱ ረቡዕ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላልፋለች።

በዲኒፕሮ ወንዝ አቅራቢያ በ11ኛው ክፍለዘመን የተገነባውን ሰፊ ገዳምን የሚያስተዳድረው የዩክሬን መንግሥት ውሳኔው የተላለፈው፣ ኮሚሽኑ በዩኔስኮ የተመዘገበው ቅርስ የኪራይ ስምምነት ውስጥ በርካታ ጥሰቶች በማግኘቱ ነው ብሏል።

ይሁን እንጂ የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የፕሬስ ቢሮ ኃላፊ ሜትሮፖሊታን ክሌመንት በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የተገለጸውና ገዳሙን ጥለው እንዲወጡ የተላለፈው ትዕዛዝ ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት የለውም ብለዋል።

"መንግሥት በሕገ ወጥ መንገድ እንድንወጣ ካደረገን አምባገነንነት ነው” ሲሉ ኃላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ እንዲህ ዓይነት አገርም ሆነ መንግሥት አንፈልግም። ሕገ መንግሥትና ሕግ አለን። ሌላ ምክንያቶችን አንቀበልም” ብለዋል።

የዩክሬን ባለሥልጣናት ምንም እንኳን የተወሰኑ መሪዎች የሩሲያን ወረራ ቢያወግዙም የተወሰኑ የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን አባላትን በጦርነቱ ወቅት ሞስኮን ደግፈዋል ሲሉ ይከሳሉ።

ባለፈው ዓመት የዩክሬን የደኅንነት አገልግሎት ላቭራ እና የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ንብረት የሆኑ ሕንጻዎች ላይ ከበባ ፈፅሞ የነበረ ሲሆን በርካታ የሃይማኖት አባቶችም በአገር ክህደት እና ከሩሲያ ጋር አብራችኋል በሚል ታስረዋል። ሆኖም የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ክሱን የሚደግፍ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም ብላለች።

ከዚህም በተጨማሪ ባለፈው ዓመት የሩሲያን ፕሮፓጋንዳ የሚደግፍ እና እናት አገር ሩሲያን ስለማንቃት የሚያወሳ የዝማሬ ቪዲዮ መውጣቱን ተከትሎ የወንጀል ክስ ተከፍቶ የነበረ ሲሆን በማዕከላዊ ዩክሬን ቪኒይሺያ አካባቢ የሃይማኖታዊ ፍርድ ቤት ኃላፊም የሩሲያን ወረራ በመደገፍ በራሪ ወረቀቶችን አዘጋጅተዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር።

ረቡዕ ዕለት ጠዋት በመቶዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ለቅዳሴ በገዳሙ ተሰባስበው ነበር። ከቅርብ ቀናት ወዲህ እየሆነ እንዳለውም ፖሊስ በአካባቢው የሚወጡ እና የሚገቡ መኪናዎችን ሲፈትሽ ነበር። ይሁን እንጅ ሁኔታው የተረጋጋ ነበር።

ቀሳውስት ገዳሙን ጥለው እንዲወጡ የተላለፈው ትዕዛዝ በዩክሬን ኦርቶዶክስ ክርስቲያን መካከል መከፋፈል ፈጥሯል።

በርካቶች ገለልተኛ የሆነችውንና በ2019 ነጻነቷን ያወጀችውን የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን የተቀላቀሉ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ለዘመናት በሞስኮ ሥር በነበረችው እና ባለፈው ግንቦት ወር ከሞስኮ የተገነጠለችውን ቤተክርስቲያን ይከተላሉ።

የ60 ዓመቱ ዘማሪ ሉቦቭ ባንክ ላለፉት ሦስት ቀናት በላቭራ ተቃውሞዋን ስታሰማ መቆየቷን ገልጻ፣ የገዳሙን ነዋሪዎች ለማስወጣት ተላለፈው ውሳኔው ፖለቲካዊ ነው ብላለች።

“ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን አይከተልም። መነኮሳት እውናዊ መላዕክት ናቸው። ባለሥልጣናት ይህንን አንዲያደርጉ አልፈልግም” ብላለች ባንክ።

የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን አካባቢውን ለቃ ካልወጣች ምን ሊፈጠር እንደሚችል እስካሁን ግልጽ አይደለም።

ይሁን እንጂ የዩክሬን የባህል ሚኒስትር ኦሌክሳንድር ትካቸንኮ ባለሥልጣናት መነኮሳትን ለማስወጣት ኃይል አይጠቀሙም ብለዋል።

የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በዩክሬን ለተቀሰቀሰው ጦርነት እንደ ምክንያት የክሬሚሊንን ንግግሮች ስታስተጋባ ቆይታለች።

ፓትሪያርክ ኪሪል በስብከታቸው ላይ ስለወደፊቱ የክርስትና እምነት ትክክለኛ የሆነ ጦርነት እንደሆነ ገልጸው በዩክሬን የሰላማዊ ሰዎችን መገደል ግን በግልጽ አላወገዙም።