ሞስኮ በአየር ክልሌ ሲበር የነበረን የዩክሬን ድሮን መትቼ ጣልኩ አለች

ሞስኮ በሩሲያ አየር ክልል ውስጥ ገብቶ የነበረን የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላን መትታ መጣሏን አስታወቀች።

የሩሲያ አየር መከላከያ በይፋዊ የቴሌግራም ቻናሉ፣ የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላን ወደ ሞስኮ ድንበር 400 ኪሎ ሜትር ያህል ዘልቆ ከገባ በኋላ ትናንት እሁድ ተመትቶ ወድቋል ብሏል።

የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላን ተመትቶ ሲወድቅ በተፈጠረው ፍንዳታ ቢያንስ ሦስት ሰዎች ተጎድተዋል በማለት እየዘገቡ ነው።

ዩክሬን ከዚህ ቀደም ሰው አልባ አውሮፕላኖቿ በሩሲያ የሚገኙ ሲቪል ተቋማት ዒላማ አድርገዋል የሚሉ ክሶችን ስታጣጥል የቆየች ሲሆን፣ ትናንት ተመትቶ ወድቋል ስለተባለው ድሮን እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም።

በተቃራኒው ሞስኮ ወደ ዩክሬን በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሮኖች አሰማርታለች።

የሩሲያ አየር ኃይል በአየር ክልሌ ሲበር የነበረውን ሰው አልባ አውሮፕላን መትቼ ስጥል በወደቀበት ኪሬዬቨስክ ከተማ ትልቅ ጉድጓድ ፈጥሯል ብሏል።

ተቀጣጣይ ነገሮችን ታጥቆ የነበረው ሰው አልባ አውሮፕላን ከሞስኮ 200 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ከተማ ተመትቶ ሲወድቅ በመኖሪያ አፓርታማዎች ላይ ጉዳት አስከትሏል ተብሏል።

የሩሲያ አየር መከላከያ በመግለጫው በአካባቢው የተከላቸው አየር መቃወሚያ ሚሳኤል እና ኤሌክትሮኒክ ሥርዓቶች ቀጠናውን ከመሰል አደጋ የሚጠብቁ ናቸው ብሏል።

አየር ኃይሉ ተግባራዊ ያደረጉት ፖል-21 የተባለ ሥርዓት የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላን የበረራ ሥርዓትን በማወክ ተመትቶ እንዲወድቅ አድርጓል ብሏል።

ከጥቂት ወራት በፊት ሞስኮ በኤንግልስ አየር ኃይል ጣቢያ አካባቢ የኪዬቭን ሰው አልባ አውሮፕላን መትታ ጥላ ነበር። ይህ ድሮን ተመትቶ ሲድቅ በስብርባሪው ሦስት የሩሲያ አየር ኃይል አባላት ሕይወታቸውን አጥተው ነበር።

ሩሲያ በተደጋጋሚ ከዚህ የአየር ጣቢያ በመነሳት በዩክሬን ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ስትሰነዘር ቆይታለች።