ጀርመን ሲጠበቅ የነበረውን ‘ሊዮፓርድ 2’ ታንክ ለዩክሬን ላከች

ዩክሬን በጥብቅ ስትፈልግ የነበረው የጀርመን ሊዮፓርድ 2 ታንክ ወደ ኪዬቭ መላኩን የጀርመን መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ጀርመን ለዩክሬን ወታደሮች ስልጠና ከሰጠች በኋላ እጅግ ዘመናዊ የሆኑትን 18 ታንኮች ለዩክሬን መላኳን ገልጻለች።

የጀርመን የመከላከያ ሚንስትር ቦሪስ ፒስቶሪየስ ታንኮቹ በጦር ቀጠና ላይ “ወሳኝ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ” እርግጠኛ ነኝ ብለዋል።

ከጀርመን ሊዮፓርድ 2 ታንኮች በተጨማሪ የዩናትድ ኪንግደም ቻሌንጀር 2 ታንኮች ዩክሬን ስለመድረሳቸው ከዩክሬን የሚወጡ ሪፖርቶች ጠቁመዋል።

ዩክሬን በሩሲያ የተፈጸመባትን ወረራ ለመከላከል ከጦር ጀት እስከ ተተኳሽ ድረስ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች እንዲሰጧት ምዕራባውያንን ስትወተውት ቆይታለች።

የዩክሬን ባለስልጣናት ሊዮፓርድ 2 ታንኮች ስለመረከባቸው እስካሁን ማረጋገጫ ባይሰጡም፤ የዩናይትድ ኪንግደም ቻሌንጀር 2 ታንኮችን ስለመቀበላቸው ግን አስታውቀዋል።

በጦር ግንባር ላይ የተሻለ ብቃት አላቸው የሚባሉት ሊዮፓርድ 2 ታንኮች በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት አባል አገራት የሚመረቱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 2ሺህ ሊዮፓርድ 2 ታንኮች ገደማ በአውሮፓ አገራት ባለቤትነት ተይዘዋል።

የጀርመን መካላከያ ሚንሰትር ቦሪስ ፒስትሮስ፤ “ቃል በገባነው መሠረት እና ጊዜውን ጠብቆ ታንኮቹ በወዳጅ ዩክሬናውያን እጅ ገብተዋል” ብለዋል።

ባለፉት በርካታ ሳምንታት ጀርመን ለዩክሬን ታንከኞች የተሻሸሉ ሊዮፓርድ 2 ታንኮች አጠቃቀም ላይ ስልጠና ስትሰጥ ቆይታለች።

ጀርመን ለዩክሬን የላከቻቸው ታንኮች ከሩሲያ ሰራሹ ቲ-90 ታንክ ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያሻሻለች ሲሆን፤ ታንኩ ከዚህ ቀደም ካሉ ስሪቶች ለጥገና ቀላል እና ነዳጅ ቆጣቢ እንዲሆን ተደርጎ ተሻሽሏል።

በሌላ በኩል የዩኬ ቻሌንጀር 2 ታንኮች “ዩክሬን ደርሰዋል” ሲሉ የዩክሬን መከላከያ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግረዋል።

የዩክሬን መከላከያ ሚንስትር ኦሌከሲ ሬዘኒኮቭ ደግሞ አገራቸው ከምዕራባውያን የተቀበለችውን ወታደራዊ ተሸከርካሪዎች በከፊል የሚያሳይ ምስል በፌስቡክ ገጻቸው አጋርተዋል።

የዩኬ መከላከያ ሚኒስቴር ቻሌንጀር 2 ታንኮችን ለዩክሬን ስለመላኩ እንዲያረጋግጥ ተጠይቆ ምላሽ ባይሰጥም፤ በዩኬ ስለታንኮቹ አጠቃቀም ስልጠና ሲወስዱ የቆዩት ዩክሬናውያን ስልጣና አጠናቀው ስለመመለሳቸው አስታውቆ ነበር።

ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ጦርነት ከገጠመች ወዲህ በርካታ ምዕራባውያን የተለያዩ ጦር መሳሪያዎችን በድጋፍ መልክ ለኪዬቭ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፖላንድ፣ ጀርመን እና ካናዳ ደግሞ ከፍተኛውን ወታደራዊ ድጋፍ የሰጡ አገራት ናቸው።