ባርሴሎና፣ ቼልሲ እና አርሰናል በተጫዋቾች ዝውውር ከፍተኛ ኪሳራ ሲያስመዘግቡ ማድሪድ በገቢ ቀዳሚ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport
ባርሴሎና፣ ቼልሲ እና አርሰናል በተጫዋቾች ዝውውር ከፍተኛ ኪሳራ ሲያስመዘግቡ ማድሪድ በገቢ ቀዳሚ ሆኗል።
ባለፈው አስር ዓመት በተጫዋቾች ዝውውር ከፍተኛ ኪሳራ በማስመዝገብ ባርሴሎና፣ ቼልሲ እና አርሰናል ቀዳሚ መሆናቸው ተገለጸ።
ዘ ሲአይኢኤስ ኦብዘርቫቶሪ እአአ ከ2014 እስከ 2023 ያስፈረሙዋቸውንና የሸጧቸውን ተጫዋቾች ተመልክቷል። ይህ መረጃ ከቡድኖቹ አካዳሚዎች የተገኙ ተጫዋቾችን አይመለከተም።
ከቀዳሚዎቹ አስር ክለቦች መካከል ስድስት የእንግሊዝ ክለቦች ተካተውበታል።
በደረጃ ሰንጠረዡ ቼልሲ ሁለተኛ ሲሆን አርሰናል ሦስተኛ ሆኗል። ማንቸስተር ዩናይትድ (5ኛ)፣ አስቶን ቪላ (7ኛ)፣ ኤቨርተን (8ኛ) እና ሊቨርፑል (9ኛ) ሆነዋል።
ጥናቱ በኪሳራ እና በትርፍ ቀዳሚ የሆኑትን 50 ክለቦችንም ይፋ አድርጓል። በትርፋማነት ረገድ ብሬንትፎርድ (26ኛ) እንዲሁም ብራይተን (29ኛ) ደረጃን በመያዝ ከትርፋማ ክለቦች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ሆነዋል።
ስቶክ ሲቲ ከፕሪሚየር ሊጉ ከወረደ ስድስት ዓመታት ቢሆኑትም ኪሳራ ካስመዘገቡ ክለቦች 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ኪሳራ ካስመዘገቡ ክለቦች መካከል የቻይና ቡድኖችም ተካተዋል። እንደአል-ናስር፣ አል-ሂላል፣ አል-አህሊ እና አል-ኢትሃድ ያሉ የሳዑዲ ቡድኖችም እንደኔይማር እና ካሪም ቤንዜማ ያሉ ተጫዋቾችን ካስፈረሙ በኋላ ኪሳራ ዝርዝር ውስጥ ገብተዋል።
ባርሴሎና 1.2 ቢሊዮን ዩሮ ወጪ ሲያደርግ ያስገባው ደግሞ 613 ሚሊዮን ዩሮ ሆኗል። ቡድኑ በፊሊፔ ኩቲንሆ እና ኦስማን ዴምቤሌ ዝውውር ከፍተኛ ኪሳራ አስመዝግቧል።
ቼልሲ ደግሞ እንደ ክርስቲያን ፑሊሲች እና ጆርጊንሆን በመሳሰሉ ተጫዋቾች ዝውውር 482 ሚሊዮን ዩሮ ከስሯል።
ቡድኑ ሞሰስ ካሲዬዶ እና ኤንዞ ፈርናንዴዝን ጨምሮ ተጫዋቾችን ለማስፈረም 1.2 ቢሊዮን ዩሮ አፍሷል።
አርሰናል እንደነ ኒኮላስ ፔፔ ባሉ ተጫዋቾች ዝውውር 436 ሚሊዮን ዩሮ ከስሯል።
ሊል 386 ሚሊዮን ዩሮ ትርፍ አስመዝግቧል። በተለይ በ10 ሚሊዮን ዩሮ ያስፈረሙትን ቪክቶር ኦሲሜህን በ82 ሚሊዮን ዩሮ ለናፖሊ መሸጣቸው ትልቅ እገዛ አድርጓል።
አያክስ ደግሞ 317 ሚሊዮን ዩሮ ማስመዝገብ ችሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሌላ መረጃ ደግሞ ሪያል ማድሪድ ከፍተኛ ገቢ በማስገባት ደረጃውን ከማንቸስተር ሲቲ መረከቡን የዴሎይት ሪፖርት አስታወቀ።
ማድሪድ በ2022-23 ውድድር ዘመን 831 ሚሊዮን ዩሮ በማስገባት ቀዳሚ ሆኗል።
826 ሚሊዮን ዩሮ ማስገባት ቻለው ሲቲ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል።
ቀዳሚዎቹን ሃያ ደረጃዎች የያዙ ክለቦች ገቢያቸው 14 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
የእነዚህ ክለቦች አማካይ ገቢም ከ500 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ሆኗል።
ፓሪስ ሴንት ዠርሜን (802 ሚሊዮን ዩሮ)፣ ባርሴሎና (800 ሚሊዮን ዩሮ) እና ማንቸስተር ዩናይትድ (746 ሚሊዮን ዩሮ) በማስገባት እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
ሊቨርፑል በደረጃው ከፍተኛ ማሽቆልቆል አሳይቷል። 683 ሚሊዮን ዩሮ ያስገባው የመርሲ ሳይዱ ክለብ ባለፈው ዓመት ከነበረበት 3ኛ ደረጃ ዘንድሮ 7ኛ ሆኖ አጠናቋል።
ቶተንሃም (8ኛ)፣ ቼልሲ (9ኛ) እና አርሴናል (10ኛ) እስከ አስር ባለው ደረጃ ውስጥ ለማጠናቀቅ ችለዋል።
ኒውካስል እና ዌስት ሃም ደግሞ 17ኛ እና 18ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ሌስተር ሲቲ፣ ሊድስ ዩናይትድ እና ኤቨርተን ከቀዳሚዎቹ ሃያ ክለቦች ተርታ ለመውጣት ተገደዋል።
ዌስትሃም፣ ሊቨርፑል እና አትሌቲኮ ማድሪድ የገቢ ማሽቆልቆል አስመዝግበው ከቀዳሚዎቹ ሃያ ክለቦች ተርታ ለመሰለፍ የቻሉ ቡድኖች ሆነዋል።












