የአፍሪካ ዋንጫ፡ አልጄሪያ ስትሰናበት ካሜሮን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባስቆጠረቻቸው ጎሎች ጥሎ ማለፉን ተቀላቀለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአፍሪካ ዋንጫ አሁንም ያልተጠበቁ ውጤቶችን እያስመዘገበ የትም አይደርሱም የተባሉት ቡድኖች የዋንጫ ግምት የተሰጣቸውን አገራት በጊዜ እየሸኙ ነው።
ትልቅ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው አልጄሪያ ከውድድሩ በጊዜ መሰናበቷን ስታረጋጥ ካሜሮን ደግሞ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከምድቧ ማለፏን አረጋግጣለች።
የማይበገሩት አንበሶች በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ደካማ አቋም አሳይተው ነበር። ግብ ጠባቂውን አንድሬ ኦናናን ከቋሚ አሰላለፍ ውጭ አድርጋም ነበር ጨዋታውን የጀመሩት።
አጣብቂኝ ውስጥ የነበረችው ካሜሮን በቶኮ ኤካምቢ አማካይነት ቀድማ ጎል በማስቆጠር መምራት ችላ ነበር።
አብሊ ጃሎው ጋምቢያ አቻ ያደረገች ጎል ካስቆጠረ በኋላ ጨዋታው በአጫ ውጤት የሚጠናቀቅ መስሎ ነበር።
ኮሊ በ85ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ጎል አስቆጥሮ ጋምቢያን ቀዳሚ ማድረግ ቻለ።
ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ከጫፍ ደርሰው የነበሩት ጋምቢያዎች በጎሜዝ እና ዉህ በተቆጠሩባቸው ጎሎች 3 ለ 2 ለመሸነፍ ተገደዋል።
ጨዋታውን ኢትዮጵያዊው ዳኛ ባምላክ ተሰማ መርቶታል።
ከዚሁ ምድብ የተገናኙት ጊኒ እና ሴኔጋል ናቸው።
ጨዋታውን ሴኔጋል 2 ለምንም በማሸነፍ ምድቡን በቀዳሚነት ለማጠናቀቅ በቅታለች።
አብዱላዬ ሴክ እና ኢሊማን ንዲዬ ሁለቱን ጎሎች አስቆጥረዋል።
ሴኔጋል በዘጠኝ ነጥብ ካሜሮን እና ጊኒ ደግሞ በአራት ነጥብ በመያዝ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በምድብ አራት የተደለደለችው አልጄሪያ ደግሞ በጊዜ ከውድድሩ ውጭ ሆናለች።
ሞሪታንያ በተከላካዩ ያሊ ዴላሂ ጎል ከጨዋታው ሦስት ነጥቦችን ለማግኘት በቅታለች።
የ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ አልጄሪያ የመድቡ ግርጌ ላይ በመቀመጥ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ ከምድብ ድልድል ማለፍ ሳትችል ቀርታለች።
ብዙም ግምት ያልተሰጣት ሞሪታንያ በሦስት ነጥብ ወደ ጥሎ ማለፍ የማለፍ ዕድሏ በጣም ሰፊ ነው።
የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎቻቸውን በአቻ ውጤት ያጠናቀቁት አልጄሪያዎች ይህንንም ጨዋታ አቻ ቢለያዩ ወደ ጥሎ ማለፉን መቀላቀል ይችሉ ነበር።
መድቡን በበላይነት የሚመሩት አንጎላ እና ቡርኪናፋሶም ተገናኝተው ነበር።
ሁለቱም ቡድኖች ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ወደ ጥሎ ማለፉ ማለፋቸውን አረጋግጠው ነበር።
በጨዋታው ፓሴንሲያ እና ቻባካ ሳልቫዶር ባስቆጠሯቸው ጎሎች አንጎላ 2 ለ 0 ለማሸነፍ በቅታለች።
በዚህም ምድቡን በሰባት ነጥብ በመምራት ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋለች።












